Sunday, August 30, 2015

ማሳሰቢያ፤ ለማስታወቂያ ሠሪዎች

በዚህ ሰሞን በሬዲዮና በቴሌቪዥን እየቀረበ ያለ አንድ ማስታወቂያ አለ፡፡የማስታወቂያው ባለቤት ብሔራዊ ሎተሪ ሲሆን፣ ጳጉሜን 6 ቀን የሚወጣውን ”እንቁጣጣሽ ሎተሪ”ን ለማስተዋወቅ የተሠራ ነው፡፡ በማስታወቂያው ላይ ባልና ሚስት በእንቁጣጣሽ ዕለት የአገር ባሕል ልብሳቸውን ለብሰው ድፎ ዳቦ ቆርሰው ለመብላት እየተዘጋጁ ሳለ ”አበባየሆሽ” የሚጨፍሩ ልጃገረዶች ወደቤታቸው መጥተው፡
”ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን፤
ስድስት ሚሊየን ይዘን…፡፡”
እያሉ ሲያዜሙና ጥንዶቹም ድፎ ዳቦና ለሎተሪ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጥተው ሲሸኟቸው ያሳያል፡፡
የማስታወቂያው ዓላማ ለአዲስ ዓመት መግቢያና መቀበያ የተዘጋጀውን ሎተሪ ማስተዋወቅ እንደመሆኑ በዓል በዓል የሚሸት ትዕይንት መያዙ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ነገር ግን የማስታወቂያው አዘጋጆች አንድ ትልቅ ነገር ረስተዋል፣ የጊዜ ቅደም-ተከተልን፡፡ ልብ በሉ! የሎተሪው ዕጣ የሚወጣው ጳጉሜን 6፣ የበዓል መስተንግዶውና አበባየሆሹ የሚደረገው ከዕጣው መውጫ (የእንቁጣጣሽ ዋዜማ) እና ከበዓሉ ቀናት በፊት፡፡
ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው አበባየሆሽ በነሐሴ የሆነው? በየትም አገር የበዓል አከባበር የበዓል ድግስ በዋዜማውም ሆነ አስቀድሞ ባለ ቀን አይበላም፣ አይጠጣም፡፡ የግድ ሎተሪውን ከበዓሉ ጋር ለማገጣጠም ሲባል ብቻ ነገሮችን ያለጊዜው ማምጣት አግባብ አይደለም፡፡ የዚህ ማስታወቂያ አዘጋጆች ጊዜ ወስደው ቢያስቡበት ኖሮ እንቁጣጣሽ ሎተሪን ከእንቁጣጣሽ ጋር የሚያያይዙ ብዙ ትዕይንቶችን መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ ከዓመት በዓል ሸመታ ጋር፣ ከበዓል ስጦታ ጋር፣ ከዋዜማ ምሽት የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት ልውውጥ ጋር፣ ወዘተ ማገናኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የይድረስ ይድረስ ሥራ ሆነና የማይመስል ማስታወቂያ ተሠራ፣ ብሔራዊ ሎተሪም ያለበቂ ግምገማ ”ይሁን” ብሎ አቀረበልን፡፡
ማስታወቂያ ግነትን እንጂ ውሸትን አይፈልግም፡፡ ከእውነታ ጋር የተጋጨ ማስታወቂያ ውሸት እንጂ ሌላ ምንም ስም የለውም፡፡ የማስታወቂያ አዘጋጆች ገንዘብን ብቻ እያያችሁ ያለዕውቀትና ያለጥንቃቄ የተሠራን እውነት ያልሆነ ድራማ ”ማስታወቂያ ” እያላችሁ እባካችሁ አትቀልዱብን፡፡ ባለማስታወቂያዎችም በግዴለሽነት የተሠራላችሁን ማስታወቂያ ሳትገመግሙ እያሳለፋችሁ ሥርዓት አታፍርሱ፡፡ ሚዲያዎችም ብትሆኑ ገና ለገና ”ሳንሱር ቀርቷል” ብላችሁ የመጣላችሁን ማስታወቂያ ሁሉ ሳትፈትሹ አትልቀቁ፡፡ የሚታዘብ ሕዝብ፣ የሚያድግና የሚማር ትውልድ አለና!

Wednesday, August 12, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፫

በክፍል ሁለት ጽሑፌ ቴሌቪዥንን አብዝቶና ያለምርጫ መመልከት በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ አስመልክቶ ሳይንሳዊ ጥናቶች የደረሱበትን ድምዳሜ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ ጥናቱ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት የሆናቸው ሕጻናት ከቴሌቪዥን ጋር ባላቸው ቆይታ ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች እንደሚደርሱባቸው ያመለከተ ሲሆን አብዛኞቹ ተጽዕኖዎች አሉታዊ መሆናቸውን ከጥናቱ ውጤት ለማየት ተችሏል፡፡
ይህ ጥናትም ሆነ ሌሎች ጥናቶች በርከት ያሉ ጎጂ ተጽዕኖዎችን የዘረዘሩ ቢሆንም፣  ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚቀርቡት ጉዳቶች ባለፈው ጽሑፍ ላይ ተጠቃለው የቀረቡት በመሆናቸው በዚሁ እናቁመውና በዚህኛው ጽሑፍ ለልጆቻችን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ የሚጠቅሙ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንቃኛለን፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
ሲንዲ ስሚዝ የተለያዩ ባለሙያዎችና ተቋማት ወላጆች የልጆቻቸውን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ ለማረጋገጥ ያግዟቸዋል በማለት ካስቀመጧቸው የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበዋቸዋል፡፡
1.    የቴሌቪዥን መመልከቻ ሰዓትን መወሰን፡- ሕጻናት እንደ ዕድሜያቸው የተለያየ የቴሌቪዥን መመልከቻ የሰዓት ገደብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ድሜ ላይ ያሉ ልጆች ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት አይገባቸውም፡፡ ስለዚህም፡-
 
ሀ. ከ2 ዓመት በታች፡- የአሜሪካ የሕጻናት ሕክምና ማኅበር (American Association of Pediatrics) እና በርካታ ኤክስፐርቶች ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በጭራሽ ቴሌቪዥን መመልከት አይኖርባቸውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጨቅላ ሕጻናት አዕምሮ በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጡ ምስሎችና ንግግሮችን ለማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ የተዋቀረ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ የዕድሜ ክልል ተብለው የሚዘጋጁ ዲቪዲዎች ቢኖሩም እንኳ አንድ ሕጻን የግንኙነትና የተግባቦት ክህሎቱን ሊያዳብር የሚችለው ከሌሎች ጋር አብሮ በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ በዲቪዲው ዕይታ ምክንያት አይደለም ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡
ለ. ከ2 እስከ 3 ዓመት፡- በብሪታኒያ የታወቁት የንግግርና የቋንቋ ቴራፒስት ዶ/ር ሳሊ ዋርድ በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናት የቴሌቪዥን መመልከቻ ጊዜ በቀን ለግማሽ ሰዓት ብቻ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ሐ. ከ3 እስከ 5 ዓመት፡- እንደባለሙያዎቹ ለዚህ የዕድሜ ክልል በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ቴሌቪዥን መመልከት በቂ ነው፡፡

2.   ቴሌቪዥንን በማይታይበት ጊዜ ማጥፋት፡- በቤታችሁ ውስጥ ቴሌቪዥን ተከፍቶ የሚመለከተው ሰው ከሌለ አጥፉት፡፡ ከቴሌቪዥኑ የሚወጣው ድምጽ ትኩረትን የሚሠርቅ ስለሆነ ልጆቻችሁ በሌሎች ጠቃሚ ነገሮች (ለምሳሌ የወላጆች ድምጽ) ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከሰዎች ጋር የግንኙነት መዘግየት ችግር ላለባቸው ልጆች ይህ ጠቃሚ መፍትሄ ነው ይላሉ ባለሙያዋ፡፡

3.   ተስማሚ ፕሮግራሞችን መምረጥ፡- ልጆቻችሁ የሚወዷቸውን፣ ነገር ግን ለዕድሜና የዕድገት ደረጃቸው የሚመጥኑና የአዋቂ ይዘት(adult theme) የሌላቸውን ፕሮግራሞች እንዲመለከቱ ፍቀዱላቸው፡፡  በተለይ ልጆቻቸሁ በወደፊት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚገጥሟቸው ተሞክሮዎች ጋር የተገናኙ ፕሮግራሞች ተመራጭ ናቸው፡፡

4.   ፕሮግራሞችን አብሮ መመልከትና መወያየት፡- በተቻላችሁ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመመልከት ሞክሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በፕሮግራሙ እየተደረገ ስላለው ነገር አብዝታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ፡፡ ሁልጊዜ አብራችሁ ለመመልከት ካልቻላችሁ የፕሮግራሙን ተስማሚነት አስቀድማችሁ አረጋግጡ፡፡ ለሕጻናት በሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ የተለመዱት ገጸ-ባሕርያት ተወዳጅ ቢሆኑም፣ አስፈሪ የሆኑትን ግን እንዳይመለከቱ ተጠንቀቁ፡፡
 
5.   አማራጮችን ማሰብ፡- ቴሌቪዥንን አብዝተው የሚመለከቱ ልጆች አልፎ አልፎ የንባብ ችሎታ ማነስ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ንባብ በልጆች የወደፊት የትምህርት ስኬት ላይ ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ልጆቻችሁን በትንሽነት ዕድሜያቸው ከመጻሕፍት ጋር እንዲላመዱ ጥረት አድርጉ፡፡ ልጆች በጨቅላነታቸው ጊዜ ማንኛውንም ዕቃ (አሻንጉሊቶቻቸውን ጨምሮ) የመወርወር፣ ከግድግዳ ጋር የማጋጨት፣ እና ለማኘክ የመሞከር ልምድ ስላላቸው በዚህ ዕድሜያቸው የምትገዙላቸው መጻሕፍት የጠንካራ ፕላስቲክ፣ የጨርቅ፣ ወይም የካርድቦርድ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ከመጻሕፍት ጋር የተዋወቁ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር መጻሕፍትን አብሮ ማንበብን ይወዳሉ ሲሉ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡
በአጠቃላይ ቴሌቪዥን መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት በኩል ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት የመገናኛ መሣሪያ ቢሆንም፣ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት በልጆች አስተሳሰብ ላይ ከፍ ያለ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መረዳት ይገባናል፡፡ ወላጆች ”ቴሌቪዥን ልጆቻችንን አበላሸ” ከሚል ጭፍን አመለካከት ወጥተው የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መንገድ ለመወጣት ቢሞክሩ ለልጆቻቸው ጤናማ አስተዳደግ መሠረት ስለሚጥሉ ከኃላፊነት መሸሹን ትተው የወላጅነት ግብራቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል እላለሁ፡፡

 

Thursday, August 6, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፪



ልጆች እና ቴሌቪዥንን አስመልክቶ ብዙ ስለማይነገርለት የወላጆች ኃላፊነት ሐሳቦችን መሰንዘር ጀምሬ ነበር፡፡ የአገራችን ወላጆች (ሁሉም ባይሆኑ አብዛኛው) በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በልጆቻቸው ባሕሪና አስተሳሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ጊዜ ወስደው ለማሰብ የሚጨነቁ አይመስለኝም፡፡ በቅርበት ከማውቃቸው ወላጆች መካከል በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው የልጆቻቸውን የቴሌቪዥን ዕይታ የሚከታተሉና ጥንቃቄ የሚያደርጉት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግድ ከማጣት በተጨማሪ አለማወቅም ነው ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፌ ቴሌቪዥን በልጆች ላይ ስለሚያስከትለው ተጽዕኖ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
የሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የቴክኖሎጂ አብዮት ካፈራቸው ግኝቶች መካከል አንዱ የሆነው ቴሌቪዥን የዕድሜ ታላቁ የሆነው ሬዲዮ ለሰው ልጅ ከሰጠው መረጃን በድምጽ የማስተላለፍ ዕድል አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ምስልን በማከል በአካል ልንገኝባቸው በማንችላቸው ሥፍራዎች ሁሉ እንድንገኝ አስችሎናል፡፡ የመረጃ፣ የመማሪያና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ ከዘመን ዘመን እያደገና እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ከቴክኖሎጂው መዘመን ጋር ተያይዞ በእጃችን መዳፍ ላይ እስከመገኘት ድረስ ተራቋል፡፡
 በዚህ ዘመን የቴሌቪዥን ቻናሎች በጣም በዝተዋል፡፡ ብዛታቸው የፈጠረው ውድድር ቀደም ባለው ጊዜ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ የነበረው የአየር ላይ ቆይታቸው ወደ ሃያ አራት ሰዓታት እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ድሮ በባለዘንግ አንቴና በየቤታችን ይደርስ የነበረው የቴሌቪዥን ስርጭት ዛሬ በዲጂታል ስርጭት መቀበያ ሳህን (dish) እና የስርጭት መቀበያ መሣሪያ (decoder) እየመጣ ፣ ከሁለትና ሦስት ቻናሎች በላይ የማይታዩበት ጊዜ ቀርቶ በሺ የሚቆጠሩ ቻናሎችን በቴሌቪዥናችን መስኮት እየተመለከትን ነው፡፡ 
ይህ የቻናሎችና የፕሮግራሞቻቸው መብዛት አማራጭ በመስጠት በኩል ጥሩ የሚባል ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ተመልካቾች እንደምርጫና ፍላጎታቸው የተለያዩ ቻናሎችን እያማረጡ መመልከት መቻላቸው መረጃ በማግኘት፣ በመማር፣ እና በመዝናናት ረገድ እርካታቸው ጨምሯል፡፡ በሌላ በኩል ግን በጊዜ ያልተገደበ እና ምርጫ-አልባ የሆነ ቴልቪዥን የመመልከት ልምድ ቀላል ያልሆነ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥን መመልከት የጤናና የሥነ-ልቡና ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ ጉዳት የቅርብ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ላይ ብቻ ሳይሆን በአዋቂዎችም ላይ የሚደርስ እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሌላው የቴሌቪዥን ጉዳት የሚቀርቡት ፕሮግራሞች በተመልካቾችን አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በማስተማር፣ በማሳወቅ፣ መረጃ በመስጠት እና በማዝናናት ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በተለይ ደግና ክፉውን ለይቶ ለማወቅ ገና የሆኑት ሕጻናትና ታዳጊዎች ሊመለከቷቸው የሚገቡትን ፕሮግራሞች መርጦ እንዲመለከቱ ማድረግ ካልተቻለ በወደፊት ባሕሪያቸው ላይ አደገኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡
ጥናቶች ምን ይላሉ?
ለመሆኑ ቴሌቪዥን በሕጻናት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን እንኳን ይህንን ስለመሰለው ጉዳይ ቀርቶ በጣም አንገብጋቢ ስለሆኑ ጉዳዮቻችን ጥልቅ ጥናቶች አይደረጉም፣ ቢደረጉም እንኳን በተሟላ ሁኔታ ተደራጅተው ስለማይቀመጡ አግኝቶ መጠቀሙም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ጽሑፍ የምንመለከታቸው ጥናቶች ባደጉት አገሮች የተደረጉትን ይሆናል፡፡ የእነዚህ ጥናቶች ውጤት በተወሰነ መልኩ ከአገራችን ሁኔታ የሚለይባቸው መልኮች ቢኖሩትም፣ መነሻው ግን ተመሳሳይ ስለሆነ ከጥናቶቹ በመነሳት ለእኛ የሚሆነውን ድምዳሜ መውሰድ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ቴሌቪዥን በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ የሚደረጉ ጥናቶች የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ፡-
1.       ልጆች በቀን ለምን የህል ሰዓታት ቴሌቪዥን ይመለከታሉ? እና
2.     በጨቅላነት ዕድሜ ቴሌቪዥን መመልከታቸው ምን ዓይነት ውጤት ያስከትላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞከራል፡፡
ሲንዲ ስሚዝ የተባሉ የንግግር ነክ ሕመሞች ተመራማሪ (speech pathologist) “Television Watching: Practical Advice for Parents of Young Children” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ወላጆች ለምን ልጆቻቸው ቴሌቪዥን እንዲመለከቱ እንደሚያደርጉ ከልምዳቸው ተነስተው ሲያብራሩ ”አንዳንዶቹ ‘ልጄ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ስለሚወደው፣’ ወይም ‘ ፊደላትን ስለሚማርበት’፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘ልጄ ምግብ አማርጣ የምትመገብ ናት፤ ቴሌቪዥኑ ከተከፈተ ግን እየበላች እንደሆነ ስለማታስተውለው ያለምርጫ ትመገባለች፣’ ወይም ‘እኔ እራት ሳዘጋጅ ልጄ ቴሌቪዥን በማየት ስለምትጠመድ አትረብሸኝም’ የሚሉና መሰል ምክንያቶችን ይሰጣሉ” ይላሉ፡፡
ባለሙያዋ በጥናታቸው ቴሌቪዥን ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት ድረስ በሆኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ተመልክተዋል፡፡ የጥናታቸው ትኩረት ሕጻናትና ታዳጊዎች በቀን ውስጥ ለስንት ሰዓታት ቴሌቪዥን እንደሚመለከቱ የሚፈትሽ ሲሆን፣ በተገኘው ውጤት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ልጅ በአማካይ በቀን ከ4 ሰዓታት በላይ ቴሌቪዥን የሚመለከት ሲሆን፣ በካናዳ እና አውስትራሊያ በቀን ከ2 ሰዓታት በላይ፣ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ከ2 ሰዓት ተኩል በላይ ልጆች ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ”አንድ ልጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በክፍል ውስጥ ካሳለፈው ጊዜ ይልቅ በቴሌቪዥን ፊት ተቀምጦ ያሳለፈው ጊዜ ይበልጣል” ይላል ጥናቱ፡፡
ይህ የልጆች የቴሌቪዥን ልምድ ታዲያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናቸው ሲንዲ ስሚዝ፡፡ ጉዳቶቹ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተመድበዋል፡፡
1.      አካላዊ ጤና፡- በምዕራባዊያን አገሮች ለሕጻናት ውፍረት በዋነኛነት ምክንያት ተደርገው ከሚወሰዱት ነገሮች መካከል አንዱ ልጆች ቴሌቪዥን፣ ቪዲዮና ዲቪዲ ለመመልከት፣ እንዲሁም የኮምፒዩተር ጌም ለመጫወት ሲሉ በርካታ ሰዓታትን ተቀምጠው ማሳለፋቸው ነው (ይህ ልምድ ወደ አገራችንም በአሁኑ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህም የተነሳ የልጆች የአካል እንቅስቃሴ ልምድ ቀላል በማይባል ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል፡፡
2.     ሥነ-ባሕሪያዊ ጤና፡- እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ አንዳንድ ለሕጻናት ተብለው የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች በአማካይ በሰዓት 20 የሚደርሱ የግጭት/ረብሻ ትዕይንቶችን የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ትዕይንቶች በካርቱን ፊልሞች ላይ ከሚታየው የገጸ-ባሕርያት የእርስ በርስ መጋጨት አንስቶ በእውነተኛ ገጸ-ባሕርያት ከሚተወኑ የረብሻ (violence) ድርጊቶች ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የሕጻናትና ታዳጊዎች የቴሌቪዥን ዕይታ ድርጊቶችን መሞከር፣ ፍርሃትን፣ እና ችግሮችን በኃይልና በጉልበት የመፍታት ዝንባሌን ያዳብራሉ ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
3.     ቋንቋ እና አጠቃላይ ትምህርት፡- ይህንን ክፍል አስመልክቶ በርካታ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ውጤታቸው የተለያዩ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን ”ዜናው ጥሩ አይደለም” ይላል የስሚዝ ጽሑፍ፡፡ እንደነዚህ ጥናቶች ከሆነ ለማስተማሪያ ተብለው የሚዘጋጁት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ በጨቅላ ሕጻናት የቋንቋ ትምህርት ብቃት ላይ መቀነስን አስከትለዋል፡፡
(ይቀጥላል)


Tuesday, July 21, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፩


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት ከምንሰማቸው ጉዳዮች መካከል ”ፊልም፣ ቴሌቪዥን፣ እና ሕጻናት” አንደኛው ነው፡፡ የዚህ ጉዳይ ዋነኛ መነሻ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች እና ፊልሞች በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ይመስለኛል፡፡ ወቅቱ ክረምት ነውና ሕጻናት እና ታዳጊዎች ከእነዚህ ፊልሞች እና ፕሮግራሞች ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፋቸው (በአብዛኛው ካለወላጅ እና አሳዳጊ ክትትል) አሳሳቢነቱ አያጠያይቅም፡፡
መወያየቱ፣ መመካከሩ፣ እና መፍትሄ መፈለጉ የሚደገፍ ነው፤ ሆኖም የውይይቱና የክርክሩ ተሳታፊዎች ብዙውን ጊዜ ሲያነሱት የማልሰማው አንድ ጉዳይ ቢኖር የወላጅ/አሳዳጊ ኃላፊነት ነው፡፡ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ስለሚመለከቷቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ምን ያህል ያውቃሉ?  የሚመለከቱትን ፕሮግራም እንዴት መቆጣጠር ይችላሉ? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን አንስቶ የሚወያይና የሚያወያይ፣ የሚያጠናና የሚመራመር አካል (ባለሙያ ወይም ተቋም) እስካሁን ድረስ አላጋጠመኝም፡፡ በአብዛኛው ተወቃሽ ተደርገው የሚነሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ናቸው፡፡ ስለወላጆችና አሳዳጊዎች ድርሻ ግን ምንም ነገር ሲነገር አልሰማሁም፣ የተጻፈም ነገር እስካሁን ድረስ አላገኘሁም፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ከጀመርኩ ከአሥር ዓመታት በላይ አልፏል፣ ይህ ጽሑፍ ከተጀመረ ደግሞ ሁለት ዓመት ሊሆን ነው፡፡ ነገር ግን ርዕሰ-ጉዳዩ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ጊዜ ወስዶ ማሰብ ስላስፈለገኝና መጠነኛ ስንፍናም ተጨምሮበት ጽሑፉ እስካሁን ድረስ ከአንድ አንቀጽ በላይ ሳይሄድ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ እንደአዲስ ይህንን ጉዳይ እንድመለስበት ያደረገኝ በልጆች አስተዳደግ ላይ በቅርባችን የማያቸው ነገሮች የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ሆነው ስላገኘኋቸው ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት ”ቴሌቪዥን፣ ልጆች፣ እና የወላጅ ኃላፊነት” ስለሚለው ጉዳይ ማሰብ ከጀመርኩ ቆይቷል (በትክክል ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነው)፡፡ የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት በአገር ውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ”ቲቪ አፍሪካ” የተባለ ቻናል ታስታውሱታላችሁ፡፡ በወቅቱ ይህ ቻናል ለብዙ ተመልካቾች የመረጃና የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ የተወዳጅነቱን ያህል ብዙ ትችቶችንም አስተናግዷል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ”ቲቪ አፍሪካ ልጆቻችንን እያበላሸ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱት ይሰማ ነበር- በጊዜው፡፡
ከእነዚህ ትችቶች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን የሳበውንና ስለወላጅ ኃላፊነት እንዳስብ ያደረገኝን ሐሳብ የሰማሁት በ1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ በአንድ ስብሰባ ላይ አንድ ዕውቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የትውልዱን ሥነ-ምግባር አስመልክተው  ሲናገሩ ”አኔ እኮ ዛሬ ልጆቼን አላሳድግም፣ ልጆቼን የሚያሳድግልኝ ቲቪ አፍሪካ ነው” ብለው ነበር፡፡ ይህ አባባል የስብሰባውን ተሳታፊዎች ፈገግ አሰኝቶ ነበር፣ እኔንም አስቆኛል፣ ከሳቁ በኋላ ግን ቀደም ብሎ ከሰማኋቸው ትችቶችና ወቀሳዎች ጋር ተዳምሮ ነገሩ ከነከነኝ፡፡ ”የቴሌቪዥናቸውን አንቴናና የቲቪ አፍሪካን ፍሪኩዌንሲ አስተካክለው ቤታቸው ያስገቡት እራሳቸው ወላጆች ሆነው ሳለ ቻናሉን ለምን ይተቻሉ? ስለሚተላለፉት ፕሮግራሞች የሚሰጠውን ማሳሰቢያስ ለምን አይከታተሉም?” ብዬም ጠየቅሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቲቪ አፍሪካ ፕሮግራሞች ይዘትና የስርጭት መርሐ-ግብር ምን እንደሚመስል ማወቅ ስለፈለግሁ የቲቪ አፍሪካን ድረ-ገጽ ጎበኘሁ፡፡  
በኢቲቪ-2 የሚተላለፈው የቲቪ አፍሪካ ስርጭት ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ እኩለ-ሌሊት ድረስ የሚዘልቅ ቢሆንም፣ ቲቪ አፍሪካ ግን ለ24 ሰዓታት የተለያዩ ፕሮግራሞችን (ዜና፣ ድራማ፣ ሶፕ ኦፔራ፣ ፊልም፣ ሙዚቃ፣…) የሚያቀርብ ነጻ ቻናል መሆኑን ከድረ-ገጹ ላይ ለመረዳት ቻልኩ፡፡ በድረ-ገጹ ላይ የተቀመጠው የፕሮግራሞች ዝርዝር የእያንዳንዱን ፕሮግራም ዓይነትና ይዘት፣ እንዲሁም የተመልካቾች የዕድሜ ገደብ የሚገልጽ አጭር መግለጫ የያዘ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የፕሮግራሞች የዕድሜ ገደብ መግለጫ በተለይ ፊልሞችና ድራማዎች በቴሌቪዥን መቅረብ ከመጀመራቸው በፊት በግልጽ ቋንቋ ለተመልካቾች ይገለጽ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የወላጆችን ኃላፊነት አስመልክቶ ማሰብ የጀመርኩት፡፡ የቴሌቪዥን ቻናሉ ”የማስተላልፈው ፕሮግራም ከዚህ ዕድሜ በላይ ላሉ ተመልካቾች የሚሆን ነው” ብሎ ካሳወቀ፣ ቀሪው ኃላፊነት የወላጅ፣ የቤተሰብ፣ የአሳዳጊ ወይም የሞግዚት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ወላጅና ቤተሰቦች፣ ቻናሉን ጥፋተኛ አድርገው ለመውቀስ የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሥራቸውን አልሰሩማ!      


(ይቀጥላል)                                              

Sunday, July 12, 2015

ኃላፊነትን አለመውሰድ- አደገኛው ገዳይ!

ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የሸገር ኤፍ.ኤም. 102.1 ”የዓርብ ልዩ ወሬዎች” ላይ ከቀረቡት ዜናዎች መካከል አንዱ ታላላቅ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኢንተርኔት አገልግሎት እየተቋረጠባቸው መቸገራቸውን የሚያትት ነበር፡፡ በተለይም ከሰኞ ሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ ለአሥር ቀናት ያህል በከተማዋ በሚስተናገደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የአንዲት አፍሪካዊት አገር ፕሬዚዳንት ባረፉበት ሆቴል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ ከሹሞቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ በእፍረት መግለጻቸው የወሬው መነሻ ነበር፡፡ በዘገባው ላይ የሆቴሎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ የችግሩን ስፋትና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ መሆናቸውን እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ሆቴል የደረሰውን ችግር በማሳያነት አቅርበው በምሬት ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡
መቼም በእኛ አገር አንድ ችግር ሲያጋጥም ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ማግኘት (በተለይ አሁን አሁን) ብርቅ እየሆነብን ነው፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ችግሩን እንዲፈታ የሚጠበቀው አካል ለችግሩ መፈጠር ወይም ለመፍትሄው በቶሎ አለመምጣት የሚደረድረው ሰበብና ምክንያት ዓይነት ነው፡፡ ስለተፈጠረው ችግር መንስኤውን አጣርቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠትና ለችግሩም መፈጠር ይቅርታ መጠየቅን የማይደፍሩ አገልግሎት ሰጪዎች በዝተዋል፡፡ እንዲያውም የችግሩን መነሻ ወደሌላ አካል ማላከክ ይቀናቸዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ላይ አገልግሎት ሰጪው የሰጠው ምላሽም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ይህ ዜና በቀረበ በማግሥቱ (ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን) ኢትዮ ቴሌኮም በሰጠው ምላሽ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የተፈጠረው የኢንተርኔት መቋረጥ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት የተፈጠረ መሆኑንና የሆቴሉ ጄኔሬተር በራሱ አለመነሳቱን ባለሙያዎቹ አረጋግጠው ጄኔሬተሩ ሲስተካከል ኢንተርኔቱም ሥራውን መቀጠሉን አስረድቷል፡፡ አያይዞም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ባለስም ሆቴሎች መካከል አብዛኞቹ የኢንተርኔት አግልግሎት እንደሌላቸው በጥናት በመረጋገጡ እንዲያስገቡ በተገለጸላቸው መሠረት አራቱ ብቻ እስካሁን ድረስ ማስገባታቸውን በመግለጽ ችግሩ የሆቴሎቹ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ እኔን ፈጽሞ አላሳመነኝም፡፡ እስቲ አስቡት! ኢንተርኮንቲኔንታልን የሚያክል ትልቅ ሆቴል ኤሌክትሪክ ሲቋረጥበት ሳያውቅ ሲቀር፡፡ መብራቶች ሲጠፉ፣ ሊፍቶች ሥራ ሲያቆሙ፣ ኤሌክትሪክ ጠፍቶ ጄኔሬተሩ እንዳልተነሳ ሲያይ ጄኔሬተሩን የማይፈትሽ የሆቴል አስተዳደር አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ እንኳን ሆቴልን ያህል ተቋም በየቤታችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሲቋረጥ ቀድመን የምናየው ቆጣሪውን ነው፡፡ ምናልባት ከቆጣሪው ጠፍቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት ያለኤሌክትሪክ እንደማይሠራ ማንም የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚስተው አይመስለኝም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ሆቴሉ ይህንን ሁሉ ”አያውቅም ነበር” እያለን ነው፡፡ እንዲያውም ”ችግሩን እኔ ስለደረስኩበት ልመሰገን እንጂ ልወቀስ አይገባኝም” ዓይነት ምላሽ ይመስላል የሰጠው፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ የገመድ-አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት (wi-fi service) በሚቋረጥበት ጊዜ መልሶ ለማስጀመር የሚደረገው የኢንተርኔት ማገናኛ መሣሪያውን (router) አጥፍቶ እንደገና ማብራት ነው፡፡ ሆቴሉ መብራት ጠፍቶበት እንደገና ሲመጣ ይህንን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም ለማለት ይከብደኛል፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ እንደተረዳሁት ችግሩ ከአንድ ቀን በላይ የቆየ እንደሆነ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ችግር እንዴት አድርጎ ነው ከኤሌክትሪክ መቋረጥ ጋር ብቻ ሊያያዝ የሚችለው?
ጉዳዩ ቴክኒካዊ ስለሆነ ምናልባት እኔን ያልገባኝ ሙያዊ ነገር ካለ እታረማለሁ፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በትልልቅ ሆቴሎች ብቻ ሳይሆን የዋይ-ፋይ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አነስተኛ ካፌዎች እና ቢሮዎችም ጭምር በዚህ ሰሞን እያጋጠመ ያለ ችግር ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ይህንን ሁሉን አቀፍ ችግር ከግምት አስገብቶ የተሰጠ አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ኩባንያው ችግሩን ወደሌላ አካል የመግፋት ዓይነት አካሄድ ተከትሏል ባይ ነኝ፡፡ በሌላ አነጋገር ከተጠያቂነት ሽሽት ነው፡፡

መቼ ይሆን ስህተትንና ጥፋትን አምኖ ኃላፊነትን መውሰድ የምንለምደው? እርግጥ ነው! በግለሰብ ደረጃ ይህ ዓይነት ችግር የብዙዎቻችን ባሕርይ ነው (እኔም አንዱ የዚህ ባሕርይ ተሸካሚ መሆኔን እዚህ ላይ ማመን ይኖርብኛል)፡፡ ተቋማት ይህንን ግለሰባዊ ባሕርይ ወርሰው ግትር ሲሆኑ ግን ደስ አይልም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት የሚወስድ በጠፋ ቁጥር ለመፍትሄ መትጋት አይኖርም፡፡ ለመፍትሄ ካልተጋን ደግሞ መሻሻል እንደናፈቀን ይቀራል፡፡ ኃላፊነትን አለመውሰድ የአገር በሽታ እየሆነብን ይመስለኛል፤ አደገኛ ገዳይ፡፡  በጊዜ እናክመው!

Wednesday, May 20, 2015

A Tale of Two Dishes

A sub-article that I recently read on the November 2014 edition of the National Geographic Magazine took me by surprise. A study conducted by the U.S. Department of Agriculture indicated that 21% of food at the consumer level went uneaten in 2010. In other words, this food is dumped to the garbage can. The number may seem less, but here is another set of comparisons: A year’s food loss accounts for a loss of 2.5% of U.S. energy consumption, over 25% of all fresh water used for agriculture in the U.S., 300 million barrels of oil, and $115 billion.  That’s HUGE!
The USDA defines food loss as the “loss of edible food, postharvest, that is available for human consumption but is not consumed.” This definition might work better for those nations that are capable of producing food that is way more enough to feed their population, and even provide the entire world with the much-needed food supply. Having enough food on your plate, and leaving the rest for the dumping can, that’s kind of awry!
This is the case of the developed world. On the other side of the coin, the scenario is quite the opposite for the “developing” one. In this part of the world, dumping food is a luxury people cannot afford. Places where food is at scarce (especially those which became war zones or drought-prone), are battlefields where people became monsters to put their hands of what appears to be a “pearl in the desert.” Even for those who can afford to put bread on their tables, the primal issue is having something to eat, not ‘how much.’
Ironically, the “developing” world is a place that covers a large sum of cultivated land, home to various edible substances, and where the majority of the population is employed in the agricultural sector. However, it is also a playground for hunger, malnutrition, drought and famine. Of course, an ensemble of reasons can be associated with these problems. But the thing is, the world is unfair when it comes to wealth distribution.
Why do people waste food? Is it because they don’t know their limits while buying their groceries? Or is it just habitual for them to stack their refrigerators with plenty of food stuffs? I don’t get what the people of the west, who are highly private, with families shrunk in size, think when they go to the supermarkets. The food stocks a single family purchases for a week could feed around five to ten families here in Ethiopia.
Don’t get me wrong here. I’m not trying to compare the level of access to food between the two worlds. I understand there are a number of reasons associated with this phenomenon, and it’s a whole different issue not to be addressed by a “passer-by blogger” like myself. The reason that I’m commenting on this issue is the shocking disparity that our world is currently hosting is something of a ringer for contemplation.

The tale of the two dishes is an issue that calls for a wide range of discussions, and I may get back to it in the future. As a last word, though, I would like to point out one factor that, in my opinion, contributes to this unfair distribution of food throughout the world- politics. Ideological differences between nations have deprived the transfer of extra food to the less fortunate parts of the earth. When the worst famine in Ethiopian history took its stall in 1985, the UK has produced a huge surplus of wheat that was believed to feed the entire population of the East African nation, but its government has decided to dump that extra wheat to the sea. Prime Minister Margaret Thacther was asked on why her administration came to that decision, and she answered that it was because the UK “doesn’t want to hand over any assistance to a country under the leadership of a communist government.” What angers me upon reading such stories is that these people are the same ones that categorize Africans “uncivilized,” since they are the ones who failed to distinguish politics from humanity. Let’s hope such cruel and misguided perceptions would not prevail ever again.

Wednesday, May 6, 2015

ሐውልትና አዲስ አበባ- ፪



በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ማብቂያ ላይ የአገራችንን ሐውልት ነክ ጉዳዮች አስመልክቶ ካሉኝ በርካታ ሐሳቦች መካከል ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት በማቆም ጉዳይ ላይ እንደማተኩር ገልጬ ነበር፡፡ ይህንን ነጥብ ለማስተንተን አንድ የከተማችንን አደባባይና በአደባባዩ ላይ የቆመውን ሐውልት እንመልከት፡፡       
በአዲስ አበባ እምብርት ላይ ከለገሐር እስከ ፒያሳ በተዘረጋው የቸርችል ጎዳና ላይ የሚገኘው አደባባይ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት (ወቅቱን ካልተሳሳትኩ በ1950ዎቹ መጨረሻ) በአፄ ቴዎድሮስ ስም እንዲሰየም ሲደረግ ሐውልታቸው በሂደት እንደሚቆምበት ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለአርባ ዓመታት ገደማ ይህ ሐሳብ ወደተግባር ሳይቀየር ቆይቶ በ1995 ዓ.ም. ላይ ዘንድሮ የቦብ ማርሌን ሐውልት በቀረጸው ብዙነህ ተስፋ አማካይነት የሐውልቱ ዲዛይንና ቴክኒካዊ ፕሮፖዛል ተዘጋጀ፡፡ ይህም ዕቅድ በአካባቢው በሚገኙ ድርጅቶች ድጋፍ አግኝቶ ለከተማዋ አስተዳደር ከቀረበና ፍቃድ ካገኘ በኋላ ሥራው ሊጀመር ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ”የአፄ ቴዎድሮስን ሐውልት የማቆም ሥራውን መሥራት ያለብኝ እኔ ነኝ” በሚል አንድ ተቋም በቀረበ ጥያቄ መሠረት ለፕሮጀክቱ የተሰጠው ፍቃድ ተሰርዞ ለአዲሱ ጠያቂ ድርጅት ተሰጠ፡፡ ድርጅቱም ”ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቼ ደረጃውን የጠበቀ ሐውልት እስካስቀርጽ ድረስ…” በማለት የሴባስቶፖልን መድፍ ሐውልት በአደባባዩ ላይ አቆመ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ “The Way I See It…” በተሰኘው የራሴ ብሎግ ላይ “Whom are We Treasuring?” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ (asnakesinesibhat.blogspot.com/2012/06/whom-are-we-treasuring.html) ሐሳብ ሰጥቼ ነበር፡፡ ዛሬስ?
የሴባስቶፖል ሐውልት በቴዎድሮስ አደባባይ ከቆመ አሥራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይወጣል የተባለው ዓለም አቀፍ ጨረታ አልወጣም፤ አይደለም ጨረታው፣ የዚህን ሥራ ኃላፊነት የወሰደው ድርጅትም ዛሬ ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥም ”ኧረ ይህ ነገር ከምን ደረሰ?” የሚል ጠያቂም አልተገኘም (ቢያንስ እኔ አልሰማሁም)፡፡ ብቻ ነገሩ ”ሾላ በድፍን” ሆኖ ቀርቷል፡፡
ይህ ነገር በቴዎድሮስ አደባባይ በማልፍበት ጊዜም ሆነ በአደባባዩ ላይ ቆሞ የሚታየውን መድፍ በአካልም ሆነ በምስል በማይበት ጊዜ ሁሉ ይከነክነኛል፡፡ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት የማቆም ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው፡፡ የአደባባዩ ስም ”ቴዎድሮስ”፣ አደባባዩ ላይ የቆመው ”ሴባስቶፖል”፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስንወያይ ”ሴባስቶፖል ከቴዎድሮስ ራዕዮች መካከል አንዱና የተሳካው ስለሆነ ሐውልቱ በስማቸው በተሰየመው አደባባይ ላይ መቆሙ ልክ ነው” ይላሉ፡፡ እኔ ግን በዚህ አልስማማም፡፡ ”ባለራዕዩ በመልክ የሚታወቅ ሆኖ እያለ ራዕዩ ለምን ሐውልት ይቆምለታል? ፍጡርን ከፈጣሪው ማስቀደምስ ትክክል ነው ወይ?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህም አልፎ ሴባስቶፖል ሙከራ እንጂ ስኬት ያልሆነ፣ እንዲያውም የከሸፈ ሙከራ ነው ባይ ነኝ፡፡ ታዲያ ለክሽፈት ሐውልት ማቆም ምን ማለት ነው?
ለእኔ፣ ሴባስቶፖል የሽንፈት ምልክት ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ከውጭ አገራት ለመግዛት እንኳ የዘመናቸው ኃያላን መንግሥታት እንቅፋት በሆኑበት ወቅት ”አገሬ የራሷን መሣሪያ ራሷ ማምረት መቻል አለባት” ብለው ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በእስረኝነት በያዟቸው አውሮፓዊያን ያሠሩት የመጀመሪያ መድፋቸው ለመቅደላው ጦርነት መድረሱ አንድ ስኬት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ ሴባስቶፖል አንድ ጊዜ ብቻ ተተኩሶ ብትንትኑ የወጣ መድፍ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ያ ጦርነት የቴዎድሮስ ፍጻሜም ሆኗል፡፡ ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አንድ ባለአጭር ዕድሜ መድፍ የበዙ ራዕዮች ባለቤት የሆኑትን ንጉሠ-ነገሥት ይወክላል ተብሎ ሐውልት የሚቆምለት? ለምንስ ነው ሽንፈትን እንደድል የምናከብረው?
ሐውልቱ የ”ጊዜያዊ”ነት ጊዜውን ከጨረሰ ቆይቷል (ጊዜያዊነት 12 ዓመት ማለት ካልሆነ በስተቀር)፡፡ የባለአደባባዩን ሐውልት ለማቆም አሁንም አልረፈደም፡፡ አስቸጋሪው ነገር ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ የቴዎድሮስን ሐውልት መቅረጽ የሚችሉ ባለሙያዎች አላጣንም፣ ሐውልቱን መቅረጽ ያልተሞከረ አዲስ ሥራ አይደለም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት በጎንደር ከተማ በዋናው አደባባይ (ፒያሳ) እና በአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ጊቢ ውስጥ ቆሟልና፡፡ ለራሳችን ታሪክ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣት አያስፈልገንም፡፡ ሁሉ ነገር እያለን እሁንም ድረስ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት አላቆምንም፡፡ የጎደለን ምንድን ነው?
እንደኔ እምነት ችግራችን ግዴለሽነት ነው! ”ታሪክ ዳቦ አይሆንም” በሚባልበት ዘመን ላይ የቴዎድሮስን ሐውልት ማቆም አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ባይታይ ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናውን ባለታሪክ ረስተን፣ ያልተሳካውን ራዕይ ሐውልት አቁመንለት ለመጪው ትውልድና ለውጭ ጎብኚዎች ምን ብለን እንደምናስረዳ አለማሰባችን ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በዚህ ምክንያት የእኛ ታሪክ የሌሎች መኩሪያ ሆናል፡፡ ዳንኤል ክብረት ”የሁለት ሐውልቶች ወግ እና ሌሎች” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ባካተተው ”የመቅደላው ጌታ” የተሰኘው ወግ ላይ ለንደን የሚገኘውን የጄኔራል ናፒየርን ሐውልት ሲመለከት የተሰማውን ስሜት እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡
”…ከሐውልቱ ሥር የተጻፈውን ጽሑፍ ለማየት ዝቅ ስል ‹‹ጄኔራል ናፒየር፣ የመቅደላው ጌታ Lord of Magdala›› ይላል፡፡ ይህ መዓርግ የናፒየር የልጅ ልጆች ሁሉ የሚጠሩበት መዓርግ ሆኗል፡፡ ልቤ በሐዘን ተመታ፡፡ ‹‹የመቅደላው ጌታ›› መቅደላ ላይ ተኝቷል፡፡ መቅደላን የመረጣት፣ ያከበራት እና ታሪክ የሠራባት የመቅደላው ጌታ እንደ ተራ ሰው መቅደላ ላይ ተኝቷል፡፡ እንግሊዞች ግን ሌላ የመቅደላ ጌታ ሰይመው እርሱንም አክብረው፣ ለልጅ ልጆቹም መጠሪያውን ሰጥተው ሐውልቱን መሐል ለንደን ላይ አቁመውለታል፡፡ አዲስ አበባ ግን የመቅደላው ጌታ ሐውልቱ የላትም፡፡”
የሁላችንም ቁጭት ይህ መሆን አለበት፡፡ የመቅደላውን ጌታ የሚያሳይ ሐውልት በከተማችን አለማቆማችን ሳያንስ፣ እርሱን የማይወክል ሐውልት አስቀምጠን ባለታሪኩን ታሪክ አልባ ማድረጋችን ሊያመን ይገባል፡፡ እናም ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት እናቁም!