በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ማብቂያ ላይ የአገራችንን ሐውልት ነክ ጉዳዮች አስመልክቶ ካሉኝ በርካታ ሐሳቦች መካከል
ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት በማቆም ጉዳይ ላይ እንደማተኩር ገልጬ ነበር፡፡ ይህንን ነጥብ ለማስተንተን አንድ የከተማችንን
አደባባይና በአደባባዩ ላይ የቆመውን ሐውልት እንመልከት፡፡
በአዲስ አበባ እምብርት ላይ ከለገሐር እስከ ፒያሳ በተዘረጋው የቸርችል ጎዳና ላይ የሚገኘው አደባባይ በአፄ ኃይለሥላሴ
ዘመነ-መንግሥት (ወቅቱን ካልተሳሳትኩ በ1950ዎቹ መጨረሻ) በአፄ ቴዎድሮስ ስም እንዲሰየም ሲደረግ ሐውልታቸው በሂደት እንደሚቆምበት
ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ለአርባ ዓመታት ገደማ ይህ ሐሳብ ወደተግባር ሳይቀየር ቆይቶ በ1995 ዓ.ም. ላይ
ዘንድሮ የቦብ ማርሌን ሐውልት በቀረጸው ብዙነህ ተስፋ አማካይነት የሐውልቱ ዲዛይንና ቴክኒካዊ ፕሮፖዛል ተዘጋጀ፡፡ ይህም ዕቅድ
በአካባቢው በሚገኙ ድርጅቶች ድጋፍ አግኝቶ ለከተማዋ አስተዳደር ከቀረበና ፍቃድ ካገኘ በኋላ ሥራው ሊጀመር ጥቂት ጊዜ ሲቀረው
”የአፄ ቴዎድሮስን ሐውልት የማቆም ሥራውን መሥራት ያለብኝ እኔ ነኝ” በሚል አንድ ተቋም በቀረበ ጥያቄ መሠረት ለፕሮጀክቱ የተሰጠው
ፍቃድ ተሰርዞ ለአዲሱ ጠያቂ ድርጅት ተሰጠ፡፡ ድርጅቱም ”ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቼ ደረጃውን የጠበቀ ሐውልት እስካስቀርጽ ድረስ…”
በማለት የሴባስቶፖልን መድፍ ሐውልት በአደባባዩ ላይ አቆመ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ “The Way I See It…” በተሰኘው የራሴ ብሎግ
ላይ “Whom are We Treasuring?” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ (asnakesinesibhat.blogspot.com/2012/06/whom-are-we-treasuring.html)
ሐሳብ ሰጥቼ ነበር፡፡ ዛሬስ?
የሴባስቶፖል ሐውልት በቴዎድሮስ አደባባይ ከቆመ አሥራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይወጣል የተባለው ዓለም አቀፍ
ጨረታ አልወጣም፤ አይደለም ጨረታው፣ የዚህን ሥራ ኃላፊነት የወሰደው ድርጅትም ዛሬ ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት
ውስጥም ”ኧረ ይህ ነገር ከምን ደረሰ?” የሚል ጠያቂም አልተገኘም (ቢያንስ እኔ አልሰማሁም)፡፡ ብቻ ነገሩ ”ሾላ በድፍን” ሆኖ
ቀርቷል፡፡
ይህ ነገር በቴዎድሮስ አደባባይ በማልፍበት ጊዜም ሆነ በአደባባዩ ላይ ቆሞ የሚታየውን መድፍ በአካልም ሆነ በምስል
በማይበት ጊዜ ሁሉ ይከነክነኛል፡፡ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት የማቆም ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው፡፡ የአደባባዩ ስም
”ቴዎድሮስ”፣ አደባባዩ ላይ የቆመው ”ሴባስቶፖል”፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስንወያይ ”ሴባስቶፖል ከቴዎድሮስ ራዕዮች መካከል አንዱና የተሳካው ስለሆነ
ሐውልቱ በስማቸው በተሰየመው አደባባይ ላይ መቆሙ ልክ ነው” ይላሉ፡፡ እኔ ግን በዚህ አልስማማም፡፡ ”ባለራዕዩ በመልክ የሚታወቅ
ሆኖ እያለ ራዕዩ ለምን ሐውልት ይቆምለታል? ፍጡርን ከፈጣሪው ማስቀደምስ ትክክል ነው ወይ?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህም አልፎ
ሴባስቶፖል ሙከራ እንጂ ስኬት ያልሆነ፣ እንዲያውም የከሸፈ ሙከራ ነው ባይ ነኝ፡፡ ታዲያ ለክሽፈት ሐውልት ማቆም ምን ማለት ነው?
ለእኔ፣ ሴባስቶፖል የሽንፈት ምልክት ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ከውጭ አገራት ለመግዛት
እንኳ የዘመናቸው ኃያላን መንግሥታት እንቅፋት በሆኑበት ወቅት ”አገሬ የራሷን መሣሪያ ራሷ ማምረት መቻል አለባት” ብለው ባደረጉት
ያላሰለሰ ጥረት በእስረኝነት በያዟቸው አውሮፓዊያን ያሠሩት የመጀመሪያ መድፋቸው ለመቅደላው ጦርነት መድረሱ አንድ ስኬት ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን፣ ሴባስቶፖል አንድ ጊዜ ብቻ ተተኩሶ ብትንትኑ የወጣ መድፍ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ያ ጦርነት የቴዎድሮስ ፍጻሜም ሆኗል፡፡
ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አንድ ባለአጭር ዕድሜ መድፍ የበዙ ራዕዮች ባለቤት የሆኑትን ንጉሠ-ነገሥት ይወክላል ተብሎ ሐውልት የሚቆምለት?
ለምንስ ነው ሽንፈትን እንደድል የምናከብረው?
ሐውልቱ የ”ጊዜያዊ”ነት ጊዜውን ከጨረሰ ቆይቷል (ጊዜያዊነት 12 ዓመት ማለት ካልሆነ በስተቀር)፡፡ የባለአደባባዩን
ሐውልት ለማቆም አሁንም አልረፈደም፡፡ አስቸጋሪው ነገር ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ የቴዎድሮስን ሐውልት መቅረጽ የሚችሉ ባለሙያዎች
አላጣንም፣ ሐውልቱን መቅረጽ ያልተሞከረ አዲስ ሥራ አይደለም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት በጎንደር ከተማ በዋናው አደባባይ (ፒያሳ)
እና በአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ጊቢ ውስጥ ቆሟልና፡፡ ለራሳችን ታሪክ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣት አያስፈልገንም፡፡ ሁሉ ነገር
እያለን እሁንም ድረስ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት አላቆምንም፡፡ የጎደለን ምንድን ነው?
እንደኔ እምነት ችግራችን ግዴለሽነት ነው! ”ታሪክ ዳቦ አይሆንም” በሚባልበት ዘመን ላይ የቴዎድሮስን ሐውልት ማቆም
አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ባይታይ ላያስደንቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናውን ባለታሪክ ረስተን፣ ያልተሳካውን ራዕይ ሐውልት አቁመንለት
ለመጪው ትውልድና ለውጭ ጎብኚዎች ምን ብለን እንደምናስረዳ አለማሰባችን ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በዚህ ምክንያት የእኛ ታሪክ የሌሎች
መኩሪያ ሆናል፡፡ ዳንኤል ክብረት ”የሁለት ሐውልቶች ወግ እና ሌሎች” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ባካተተው ”የመቅደላው ጌታ” የተሰኘው
ወግ ላይ ለንደን የሚገኘውን የጄኔራል ናፒየርን ሐውልት ሲመለከት የተሰማውን ስሜት እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡
”…ከሐውልቱ ሥር የተጻፈውን ጽሑፍ ለማየት ዝቅ ስል ‹‹ጄኔራል ናፒየር፣ የመቅደላው ጌታ Lord of
Magdala›› ይላል፡፡ ይህ መዓርግ የናፒየር የልጅ ልጆች ሁሉ የሚጠሩበት መዓርግ ሆኗል፡፡ ልቤ በሐዘን ተመታ፡፡ ‹‹የመቅደላው
ጌታ›› መቅደላ ላይ ተኝቷል፡፡ መቅደላን የመረጣት፣ ያከበራት እና ታሪክ የሠራባት የመቅደላው ጌታ እንደ ተራ ሰው መቅደላ ላይ
ተኝቷል፡፡ እንግሊዞች ግን ሌላ የመቅደላ ጌታ ሰይመው እርሱንም አክብረው፣ ለልጅ ልጆቹም መጠሪያውን ሰጥተው ሐውልቱን መሐል ለንደን
ላይ አቁመውለታል፡፡ አዲስ አበባ ግን የመቅደላው ጌታ ሐውልቱ የላትም፡፡”
የሁላችንም ቁጭት ይህ መሆን አለበት፡፡ የመቅደላውን ጌታ የሚያሳይ ሐውልት በከተማችን አለማቆማችን ሳያንስ፣ እርሱን
የማይወክል ሐውልት አስቀምጠን ባለታሪኩን ታሪክ አልባ ማድረጋችን ሊያመን ይገባል፡፡ እናም ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት እናቁም!
No comments:
Post a Comment