ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የሸገር ኤፍ.ኤም.
102.1 ”የዓርብ ልዩ ወሬዎች” ላይ ከቀረቡት ዜናዎች መካከል አንዱ ታላላቅ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኢንተርኔት አገልግሎት እየተቋረጠባቸው
መቸገራቸውን የሚያትት ነበር፡፡ በተለይም ከሰኞ ሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ ለአሥር ቀናት ያህል በከተማዋ በሚስተናገደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ
ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የአንዲት አፍሪካዊት አገር ፕሬዚዳንት ባረፉበት ሆቴል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ ከሹሞቻቸው
ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ በእፍረት መግለጻቸው የወሬው መነሻ ነበር፡፡ በዘገባው ላይ የሆቴሎች ማኅበር
ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ የችግሩን ስፋትና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ምላሽ
ለመስጠት ዳተኛ መሆናቸውን እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ሆቴል የደረሰውን ችግር በማሳያነት አቅርበው በምሬት ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡
መቼም በእኛ አገር አንድ ችግር ሲያጋጥም ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ማግኘት (በተለይ አሁን አሁን) ብርቅ እየሆነብን ነው፡፡
ይበልጥ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ችግሩን እንዲፈታ የሚጠበቀው አካል ለችግሩ መፈጠር ወይም ለመፍትሄው በቶሎ አለመምጣት የሚደረድረው
ሰበብና ምክንያት ዓይነት ነው፡፡ ስለተፈጠረው ችግር መንስኤውን አጣርቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠትና ለችግሩም መፈጠር ይቅርታ መጠየቅን
የማይደፍሩ አገልግሎት ሰጪዎች በዝተዋል፡፡ እንዲያውም የችግሩን መነሻ ወደሌላ አካል ማላከክ ይቀናቸዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የኢንተርኔት
አገልግሎት መቋረጥ ላይ አገልግሎት ሰጪው የሰጠው ምላሽም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ይህ ዜና በቀረበ በማግሥቱ (ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን) ኢትዮ ቴሌኮም በሰጠው ምላሽ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል
የተፈጠረው የኢንተርኔት መቋረጥ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት የተፈጠረ መሆኑንና የሆቴሉ ጄኔሬተር በራሱ አለመነሳቱን ባለሙያዎቹ አረጋግጠው
ጄኔሬተሩ ሲስተካከል ኢንተርኔቱም ሥራውን መቀጠሉን አስረድቷል፡፡ አያይዞም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ባለስም ሆቴሎች መካከል አብዛኞቹ
የኢንተርኔት አግልግሎት እንደሌላቸው በጥናት በመረጋገጡ እንዲያስገቡ በተገለጸላቸው መሠረት አራቱ ብቻ እስካሁን ድረስ ማስገባታቸውን
በመግለጽ ችግሩ የሆቴሎቹ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ እኔን ፈጽሞ አላሳመነኝም፡፡ እስቲ አስቡት! ኢንተርኮንቲኔንታልን የሚያክል ትልቅ ሆቴል ኤሌክትሪክ
ሲቋረጥበት ሳያውቅ ሲቀር፡፡ መብራቶች ሲጠፉ፣ ሊፍቶች ሥራ ሲያቆሙ፣ ኤሌክትሪክ ጠፍቶ ጄኔሬተሩ እንዳልተነሳ ሲያይ ጄኔሬተሩን የማይፈትሽ
የሆቴል አስተዳደር አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ እንኳን ሆቴልን ያህል ተቋም በየቤታችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሲቋረጥ ቀድመን
የምናየው ቆጣሪውን ነው፡፡ ምናልባት ከቆጣሪው ጠፍቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት ያለኤሌክትሪክ እንደማይሠራ
ማንም የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚስተው አይመስለኝም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ሆቴሉ ይህንን ሁሉ ”አያውቅም ነበር” እያለን ነው፡፡ እንዲያውም
”ችግሩን እኔ ስለደረስኩበት ልመሰገን እንጂ ልወቀስ አይገባኝም” ዓይነት ምላሽ ይመስላል የሰጠው፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ የገመድ-አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት (wi-fi service) በሚቋረጥበት ጊዜ መልሶ ለማስጀመር
የሚደረገው የኢንተርኔት ማገናኛ መሣሪያውን (router) አጥፍቶ እንደገና ማብራት ነው፡፡ ሆቴሉ መብራት ጠፍቶበት እንደገና ሲመጣ
ይህንን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም ለማለት ይከብደኛል፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ እንደተረዳሁት ችግሩ ከአንድ ቀን በላይ የቆየ
እንደሆነ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ችግር እንዴት አድርጎ ነው ከኤሌክትሪክ መቋረጥ ጋር ብቻ ሊያያዝ የሚችለው?
ጉዳዩ ቴክኒካዊ ስለሆነ ምናልባት እኔን ያልገባኝ ሙያዊ ነገር ካለ እታረማለሁ፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት አገልግሎት
መቋረጥ በትልልቅ ሆቴሎች ብቻ ሳይሆን የዋይ-ፋይ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አነስተኛ ካፌዎች እና ቢሮዎችም ጭምር በዚህ ሰሞን እያጋጠመ
ያለ ችግር ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ይህንን ሁሉን አቀፍ ችግር ከግምት አስገብቶ የተሰጠ አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት
ኩባንያው ችግሩን ወደሌላ አካል የመግፋት ዓይነት አካሄድ ተከትሏል ባይ ነኝ፡፡ በሌላ አነጋገር ከተጠያቂነት ሽሽት ነው፡፡
መቼ ይሆን ስህተትንና ጥፋትን አምኖ ኃላፊነትን መውሰድ የምንለምደው? እርግጥ ነው! በግለሰብ ደረጃ ይህ ዓይነት
ችግር የብዙዎቻችን ባሕርይ ነው (እኔም አንዱ የዚህ ባሕርይ ተሸካሚ መሆኔን እዚህ ላይ ማመን ይኖርብኛል)፡፡ ተቋማት ይህንን ግለሰባዊ
ባሕርይ ወርሰው ግትር ሲሆኑ ግን ደስ አይልም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት የሚወስድ በጠፋ ቁጥር ለመፍትሄ መትጋት አይኖርም፡፡
ለመፍትሄ ካልተጋን ደግሞ መሻሻል እንደናፈቀን ይቀራል፡፡ ኃላፊነትን አለመውሰድ የአገር በሽታ እየሆነብን ይመስለኛል፤ አደገኛ ገዳይ፡፡ በጊዜ እናክመው!
No comments:
Post a Comment