በዚህ ሰሞን በሬዲዮና በቴሌቪዥን እየቀረበ ያለ አንድ ማስታወቂያ አለ፡፡የማስታወቂያው
ባለቤት ብሔራዊ ሎተሪ ሲሆን፣ ጳጉሜን 6 ቀን የሚወጣውን ”እንቁጣጣሽ ሎተሪ”ን ለማስተዋወቅ የተሠራ ነው፡፡ በማስታወቂያው ላይ
ባልና ሚስት በእንቁጣጣሽ ዕለት የአገር ባሕል ልብሳቸውን ለብሰው ድፎ ዳቦ ቆርሰው ለመብላት እየተዘጋጁ ሳለ ”አበባየሆሽ” የሚጨፍሩ ልጃገረዶች ወደቤታቸው መጥተው፡
”ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን፤
ስድስት ሚሊየን ይዘን…፡፡”
እያሉ ሲያዜሙና ጥንዶቹም ድፎ ዳቦና ለሎተሪ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጥተው ሲሸኟቸው ያሳያል፡፡
የማስታወቂያው ዓላማ ለአዲስ ዓመት መግቢያና መቀበያ የተዘጋጀውን ሎተሪ ማስተዋወቅ እንደመሆኑ በዓል በዓል የሚሸት
ትዕይንት መያዙ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ነገር ግን የማስታወቂያው አዘጋጆች አንድ ትልቅ ነገር ረስተዋል፣ የጊዜ ቅደም-ተከተልን፡፡
ልብ በሉ! የሎተሪው ዕጣ የሚወጣው ጳጉሜን 6፣ የበዓል መስተንግዶውና አበባየሆሹ የሚደረገው ከዕጣው መውጫ (የእንቁጣጣሽ ዋዜማ)
እና ከበዓሉ ቀናት በፊት፡፡
ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው አበባየሆሽ በነሐሴ የሆነው? በየትም አገር የበዓል አከባበር የበዓል ድግስ በዋዜማውም ሆነ
አስቀድሞ ባለ ቀን አይበላም፣ አይጠጣም፡፡ የግድ ሎተሪውን ከበዓሉ ጋር ለማገጣጠም ሲባል ብቻ ነገሮችን ያለጊዜው ማምጣት አግባብ
አይደለም፡፡ የዚህ ማስታወቂያ አዘጋጆች ጊዜ ወስደው ቢያስቡበት ኖሮ እንቁጣጣሽ ሎተሪን ከእንቁጣጣሽ ጋር የሚያያይዙ ብዙ ትዕይንቶችን
መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ ከዓመት በዓል ሸመታ ጋር፣ ከበዓል ስጦታ ጋር፣ ከዋዜማ ምሽት የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት ልውውጥ
ጋር፣ ወዘተ ማገናኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የይድረስ ይድረስ ሥራ ሆነና የማይመስል ማስታወቂያ ተሠራ፣ ብሔራዊ ሎተሪም ያለበቂ
ግምገማ ”ይሁን” ብሎ አቀረበልን፡፡
ማስታወቂያ ግነትን እንጂ ውሸትን አይፈልግም፡፡ ከእውነታ ጋር የተጋጨ ማስታወቂያ
ውሸት እንጂ ሌላ ምንም ስም የለውም፡፡ የማስታወቂያ አዘጋጆች ገንዘብን ብቻ እያያችሁ ያለዕውቀትና ያለጥንቃቄ የተሠራን እውነት
ያልሆነ ድራማ ”ማስታወቂያ ” እያላችሁ እባካችሁ አትቀልዱብን፡፡ ባለማስታወቂያዎችም በግዴለሽነት የተሠራላችሁን ማስታወቂያ ሳትገመግሙ
እያሳለፋችሁ ሥርዓት አታፍርሱ፡፡ ሚዲያዎችም ብትሆኑ ገና ለገና ”ሳንሱር ቀርቷል” ብላችሁ የመጣላችሁን ማስታወቂያ ሁሉ ሳትፈትሹ
አትልቀቁ፡፡ የሚታዘብ ሕዝብ፣ የሚያድግና የሚማር ትውልድ አለና!
No comments:
Post a Comment