Wednesday, August 12, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፫

በክፍል ሁለት ጽሑፌ ቴሌቪዥንን አብዝቶና ያለምርጫ መመልከት በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ አስመልክቶ ሳይንሳዊ ጥናቶች የደረሱበትን ድምዳሜ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ ጥናቱ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት የሆናቸው ሕጻናት ከቴሌቪዥን ጋር ባላቸው ቆይታ ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች እንደሚደርሱባቸው ያመለከተ ሲሆን አብዛኞቹ ተጽዕኖዎች አሉታዊ መሆናቸውን ከጥናቱ ውጤት ለማየት ተችሏል፡፡
ይህ ጥናትም ሆነ ሌሎች ጥናቶች በርከት ያሉ ጎጂ ተጽዕኖዎችን የዘረዘሩ ቢሆንም፣  ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚቀርቡት ጉዳቶች ባለፈው ጽሑፍ ላይ ተጠቃለው የቀረቡት በመሆናቸው በዚሁ እናቁመውና በዚህኛው ጽሑፍ ለልጆቻችን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ የሚጠቅሙ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንቃኛለን፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
ሲንዲ ስሚዝ የተለያዩ ባለሙያዎችና ተቋማት ወላጆች የልጆቻቸውን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ ለማረጋገጥ ያግዟቸዋል በማለት ካስቀመጧቸው የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበዋቸዋል፡፡
1.    የቴሌቪዥን መመልከቻ ሰዓትን መወሰን፡- ሕጻናት እንደ ዕድሜያቸው የተለያየ የቴሌቪዥን መመልከቻ የሰዓት ገደብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ድሜ ላይ ያሉ ልጆች ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት አይገባቸውም፡፡ ስለዚህም፡-
 
ሀ. ከ2 ዓመት በታች፡- የአሜሪካ የሕጻናት ሕክምና ማኅበር (American Association of Pediatrics) እና በርካታ ኤክስፐርቶች ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በጭራሽ ቴሌቪዥን መመልከት አይኖርባቸውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጨቅላ ሕጻናት አዕምሮ በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጡ ምስሎችና ንግግሮችን ለማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ የተዋቀረ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ የዕድሜ ክልል ተብለው የሚዘጋጁ ዲቪዲዎች ቢኖሩም እንኳ አንድ ሕጻን የግንኙነትና የተግባቦት ክህሎቱን ሊያዳብር የሚችለው ከሌሎች ጋር አብሮ በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ በዲቪዲው ዕይታ ምክንያት አይደለም ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡
ለ. ከ2 እስከ 3 ዓመት፡- በብሪታኒያ የታወቁት የንግግርና የቋንቋ ቴራፒስት ዶ/ር ሳሊ ዋርድ በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናት የቴሌቪዥን መመልከቻ ጊዜ በቀን ለግማሽ ሰዓት ብቻ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ሐ. ከ3 እስከ 5 ዓመት፡- እንደባለሙያዎቹ ለዚህ የዕድሜ ክልል በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ቴሌቪዥን መመልከት በቂ ነው፡፡

2.   ቴሌቪዥንን በማይታይበት ጊዜ ማጥፋት፡- በቤታችሁ ውስጥ ቴሌቪዥን ተከፍቶ የሚመለከተው ሰው ከሌለ አጥፉት፡፡ ከቴሌቪዥኑ የሚወጣው ድምጽ ትኩረትን የሚሠርቅ ስለሆነ ልጆቻችሁ በሌሎች ጠቃሚ ነገሮች (ለምሳሌ የወላጆች ድምጽ) ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከሰዎች ጋር የግንኙነት መዘግየት ችግር ላለባቸው ልጆች ይህ ጠቃሚ መፍትሄ ነው ይላሉ ባለሙያዋ፡፡

3.   ተስማሚ ፕሮግራሞችን መምረጥ፡- ልጆቻችሁ የሚወዷቸውን፣ ነገር ግን ለዕድሜና የዕድገት ደረጃቸው የሚመጥኑና የአዋቂ ይዘት(adult theme) የሌላቸውን ፕሮግራሞች እንዲመለከቱ ፍቀዱላቸው፡፡  በተለይ ልጆቻቸሁ በወደፊት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚገጥሟቸው ተሞክሮዎች ጋር የተገናኙ ፕሮግራሞች ተመራጭ ናቸው፡፡

4.   ፕሮግራሞችን አብሮ መመልከትና መወያየት፡- በተቻላችሁ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመመልከት ሞክሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በፕሮግራሙ እየተደረገ ስላለው ነገር አብዝታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ፡፡ ሁልጊዜ አብራችሁ ለመመልከት ካልቻላችሁ የፕሮግራሙን ተስማሚነት አስቀድማችሁ አረጋግጡ፡፡ ለሕጻናት በሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ የተለመዱት ገጸ-ባሕርያት ተወዳጅ ቢሆኑም፣ አስፈሪ የሆኑትን ግን እንዳይመለከቱ ተጠንቀቁ፡፡
 
5.   አማራጮችን ማሰብ፡- ቴሌቪዥንን አብዝተው የሚመለከቱ ልጆች አልፎ አልፎ የንባብ ችሎታ ማነስ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ንባብ በልጆች የወደፊት የትምህርት ስኬት ላይ ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ልጆቻችሁን በትንሽነት ዕድሜያቸው ከመጻሕፍት ጋር እንዲላመዱ ጥረት አድርጉ፡፡ ልጆች በጨቅላነታቸው ጊዜ ማንኛውንም ዕቃ (አሻንጉሊቶቻቸውን ጨምሮ) የመወርወር፣ ከግድግዳ ጋር የማጋጨት፣ እና ለማኘክ የመሞከር ልምድ ስላላቸው በዚህ ዕድሜያቸው የምትገዙላቸው መጻሕፍት የጠንካራ ፕላስቲክ፣ የጨርቅ፣ ወይም የካርድቦርድ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ከመጻሕፍት ጋር የተዋወቁ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር መጻሕፍትን አብሮ ማንበብን ይወዳሉ ሲሉ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡
በአጠቃላይ ቴሌቪዥን መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት በኩል ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት የመገናኛ መሣሪያ ቢሆንም፣ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት በልጆች አስተሳሰብ ላይ ከፍ ያለ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መረዳት ይገባናል፡፡ ወላጆች ”ቴሌቪዥን ልጆቻችንን አበላሸ” ከሚል ጭፍን አመለካከት ወጥተው የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መንገድ ለመወጣት ቢሞክሩ ለልጆቻቸው ጤናማ አስተዳደግ መሠረት ስለሚጥሉ ከኃላፊነት መሸሹን ትተው የወላጅነት ግብራቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል እላለሁ፡፡

 

No comments:

Post a Comment