Wednesday, June 8, 2016

Half-way across Life: Reflection of a Birthday Boy

Hmm... Just marked the big '4'! The feeling? Well, if you're looking at the age, you might say, "Oh, I got old!" But if you look at the bigger picture, your reaction will be, "Man! I'm half-way across the journey of life." That's what I like to see as I celebrate my birthday.
I woke up on a sunny October morning, and the little voice in my head said: "Guess what, you're turning 40 this year!" That sparked this thought, "Ha! Time to reminisce on the past and reflect on the future."
I don't know how many years I have left, for it's in God's hands. But if it were up to my desire, I'd like to live till 100. Too much? OK, let's make it 80. Being this the case, I've lived half of my life. Looking back at the first half, it's a mixed one. I've had bed of roses and rough patches, both of which were of important lessons in life. Despite the good and not-good experiences that I had over the last four decades, I see those times now as "warm-up" sessions.
Looking ahead, I've got the "2nd half" coming up. With all the challenges & triumphs, success & failure, and laughter & cries, I got a strong feeling that the next 40 [to 60] years will be my interesting and pivotal ones. So as I turned 40, I feel more energetic, happy, and optimist, amid these times of uncertainty!

Thursday, May 12, 2016

አንዳንድ ሐሳቦች- ስለኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያ (ክፍል ፫)


ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎቼ የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያን አስመልክቶ ጥቅል የመንደርደሪያ ሐሳብ ለመስጠት እና የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት አጀማመርና ወቅታዊ ሁኔታን በመንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢቢሲ) ማሳያነት ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፌ ደግሞ አሁን ”በአገራችን በሥርጭት ላይ የሚገኙትና ለሥርጭት በመዘጋጀት ላይ ያሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከፕሮግራም ይዘት፣ ከዘውግ ስብጥር፣ እንዲሁም ከጥራት ጋር ተያይዞ ምን ማድረግ አለባቸው?” በሚለው ጉዳይ ላይ የበኩሌን ጥቂት ለማለት እሞክራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወቅታዊ የፕሮግራም ይዘት
በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ እንደጠቀስኩት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሥርጭት ላይ የሚገኙት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ተቋቁመው እየሠሩ ካሉት ሚዲያዎች መካከል፤ በመንግሥት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሶማሌ ክልሎች፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ቴሌቪዥኖች የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ በግል ዘርፍ ደግሞ መሠረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ሰርቪስስ (ኢቢኤስ)፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ፕሮግራሞች ደግሞ በእንግሊዝ አገር መቀመጫውን ያደረገው ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የእነዚህን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የፕሮግራም ይዘት ስንፈትሽ፤ መንግሥታዊ/የሕዝብ ሚዲያዎች በዋነኛነት የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ባደረጉ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች እንዲሁም በተወሰኑ የመዝናኛ ዘርፎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ የግሉ ኢቢኤስ ደግሞ መዝናኛን በዋንኛነት ያተኩርበታል፡፡ ሌሎቹ ፕሮግራሞቹ ማኅበራዊ ኑሮን፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ኢኮኖሚን ለመዳሰስ ይሞክራሉ፡፡ ኤልሻዳይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በክርስትና ሃይማኖት ላይ ትኩረት አድርጎ ፕሮግራሞችን ያስተላልፋል፡፡
ወደ ይዘቶቹ ደረጃ ስንሄድ፣ በግሌ የሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉት ፕሮግራሞች የተመልካቾችን ፍላጎት በሚያሟላ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኤልሻዳይ ቴሌቪዥንን በትኩረት አቅጣጫው ምክንያት ከንጽጽሩ ውጭ አድርገን ሌሎቹን ጣቢያዎች ስንገመግም፣ በአብዛኛው ተመሳሳይነትና ተደጋጋሚነት እናይባቸዋለን፡፡ የመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያዎች፣ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከረው፣ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ተከትለው ፕሮግራማቸውን የሚያቀርቡ በመሆናቸው በዜናና ወቅታዊ ዝግጅቶቻቸው ላይ ከቋንቋ እስከ አቀራረብ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ምናልባትም መለያ ምልክታቸውን (ሎጎ) ካላየን በስተቀር አንዱን ከሌላው ለመለየት ይከብዳል፡፡ የፕሮግራማቸው አቀራረብ”ልማታዊ ጋዜጠኝነት” በሚባለው የጋዜጠኝነት ዘርፍ እንዲመራ የተደረገ በመሆኑ፣ በአመዛኙ ”ልማት-ተኮር” በሆኑ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች የአየር ሰዓታቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ ናቸው፡፡ የግሎቹ ኢቢኤስ እና የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኦቢሲ) ደግሞ ከቋንቋ ልዩነት በስተቀር በአብዛኛው ተመሳሳይ የሆነ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ የይዘት ድግግሞሽ በብዛት ይታይባቸዋል፡፡ ድግግሞሽ ደግሞ በአብዛኛው አሰልቺነትን አስከትሎ የሚመጣ እንደመሆኑ በእኔ የቴሌቪዥን ተመልካችነት ልምድ እንዳየሁት [በሁሉም ቻናሎች] ከጥቂት ፕሮግራሞች በስተቀር አብዛኛዎቹ አሰልቺና ለመመልከት የማይጋብዙ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንዳንድ ፕሮግራሞች (በተለይም በቅርብ ጊዜ የተጀመሩት የ”መዝናኛ” ፕሮግራሞች) በፍጹም ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ለተመልካች ክብር የማይሰጡና የአገራችንን የባሕል፣ የአስተሳሰብና የዕውቀት ደረጃ ከግምት ያላስገቡ ሆነዋል፡፡ ከዕውቀት ማነስ ይሁን፣ ወይም ተመልካቹን ከመናቅ፣ በደረጃቸው የወረዱ ፕሮግራሞችን መመልከት እየተደጋገመ ነው፡፡አንዳንዶቹ ፕሮግራሞች እንዲያውም፣ የሌሎችን አገሮች የፕሮግራም ፎርማት እንዳለ በመገልበጥ የሚቀርቡ በመሆናቸው፣ ለኢትዮጵያዊ ተመልካች የማይመጥኑ ፕሮግራሞች ከአሰልቺ አቀራረብ ጋር  በቴሌቪዥናችን ብቅ እያሉ እያታከቱን ይገኛሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተጨማሪ አዳዲስ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘርፉን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ አካባቢያዊ የሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት ለመስጠት ለሚፈልጉ ድርጅቶች ባቀረበው ጥሪ መሠረት ”ናሁ” እና ”ቃና” የተሰኙ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች መደበኛ ሥርጭት በቅርቡ የጀመሩ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ የሬዲዮ ሥርጭቱና በመላዋ ኢትዮጵያ 12 የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋም የታወቀው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም የቴሌቪዥን ሥርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዝርዝር ባይገለጽም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን አገልግሎት ለመጀመር ማሰቧም ተነግሯል፡፡ የእነዚህን ቻናሎች ይዘት መደበኛ ሥርጭት ሲጀምሩ የምናየው ይሆናል፡፡
ቴሌቪዥኖቻችን በምን ላይ ያተኩሩ?
በአሁኑ ወቅት ከተቀላቀሉት አዳዲስ ቻናሎች መካከል ሁለቱ (ናሁ እና ቃና) በአብዛኛው መዝናኛ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል፡፡ በውስን ደረጃ ናሁ ከመዝናኛው በተጨማሪ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ዝግጅቶችን (ቶክ ሾዎችና ሪያሊቲ ሾዎች) እያቀረበ መገኘቱ እንዳለ ሆኖ፡፡
አዳዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ ቻናሎች መዝናኛ ላይ ማተኮራቸው በመሠረቱ ብዙም ችግር የለውም፣ መዝናኛ የሕይወታችን አንድ አካል እንደመሆኑ ሽፋን ሊሰጠው ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ ለምን መዝናኛ ብቻ? ሌሎች ጉዳዮችስ? አገራችን በርካታ ውይይትና የመረጃ ልውውጥ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሏት፡፡ ፖለቲካችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ ባሕላችን፣ ታሪካችን፣ ወዘተ የሚዲያዎቻችን የትኩረት ማዕከል ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ምናልባት አሁን በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት አንዳንዶቹ ጉዳዮች አይነኬና ምናልባትም ”አይደፈሬ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ግን፣ ሚዲያዎቻችን ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ባለመዘንጋት ባሉት አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መጣር ይኖርባቸዋል፡፡
ይዘት
ይዘትን በተመለከተ፣ የቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን ”ከፈረንጅ የመጣ ሁሉ ትክክል ነው” ከሚል አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው፡፡ ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት አንዳንዶቹ ሚዲያዎች የውጭ ሚዲያዎችን ፎርማት እንዳለ ገልብጠው ለማቅረብ በሚያደርጉት ሙከራ የኢትዮጵያን ባሕል፣ ሥነ-ምግባር፣ እና የሕዝቡን የአስተሳሰብና የሞራል ደረጃ ከግምት የማያስገቡ በመሆናቸው የማይገቡ፣ ዓላማቸውና መድረሻቸው በፍጹም ግልጽ ያልሆነና ሲከፋም ግልብ የሆኑ ፕሮግራሞችን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ፣ ሚዲያዎቻችን ለራሳቸው ሕልውናም ሲሉ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በሚገባ ሊያውቁ ይገባቸዋል፡፡ ከውጭ የምንቀበለው የሚጠቅመንን ብቻ መሆኑን እና እኛም ለዓለም የምንሰጠው ብዙ ነገር እንዳለን ተረድተው ሥራቸውን ከጀመሩ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ያከብራሉ፤ አገርና ሕዝብን ሳያውቁና ሳያከብሩ ”ቴሌቪዥን እጀምራለሁ” ማለት የጨለማ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡
የዝግጅት ደረጃ
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሚዲያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተቆጣጣሪው የመንግሥት አካልም በጋራ ሊሠሩት የሚገባ አንድ ሥራ አለ፤ የሚዲያ ዝግጅቶች ደረጃ! በሌሎች አገሮች እንደተለመደው፣ በሚዲያ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በሲኒማ የሚቀርቡ ፊልሞችም በተመልካቾች የዕድሜ ደረጃ ላይ የተመሠረተ ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ በእኛም አገር ይህ ዓይነቱ የደረጃ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባዋል፡፡ አሁን አሁን በቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን የሚቀርቡ ድራማዎች፣ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ እና ማስታወቂያዎች የተመልካቾችን ዕድሜና የግንዛቤ ደረጃን፣ እንዲሁም የሥርጭት ሰዓት ምርጫን በፍጹም ከግምት የማያስገቡ ናቸው፡፡ በተለይ በዚህ ፈጣን የመረጃ ዘመን አዲሱ ትውልድ ለሚመለከታቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይዘት መጨነቅና መጠንቀቅ ካልጀመርን ከባድ ጥፋት እየፈጸምን መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ የሚዲያዎቻችንን የፕሮግራም ይዘት እየገመገመ ደረጃ የሚሰጥ የሚዲያና የመዝናኛ ”ደረጃ መዳቢ” በአስቸኳይ ያስፈልገናል፡፡

ከላይ ለማንሳት የሞከርኳቸው ሐሳቦች አሁን በሥርጭት ላይ ላሉትም ሆነ ወደፊት ሥርጭት ለሚጀምሩት የቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ይሆናሉ ያልኳቸውን ጥቂቶቹን ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ ሐሳቦች ሊነሱ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ለቴሌቪዥን ብቻ ሳሆን ለሬዲዮ ሚዲያዎቻንም የሚጠቅሙ ናቸው፣ ምክንያቱም ሁለቱም ሚዲያዎች በርካታ ተከታታይ ያላቸው በመሆናቸው ለተከታዮቻቸው ኃላፊነት ሊሰማቸው ግድ ይላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን፣ ሚዲያ ሕዝብን በማሳወቅና በማዝናናት፣ እንዲሁም የውይይት መድረክ በመሆን በርካታ ሥራ ሊሠራ የሚችል ተቋም እንደመሆኑ፣ ያለው አቅም ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ኃላፊነት አንዳለበት በማወቅ ለአገራችንና ለሕዝቧ የሚበጀውን ለመሥራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል እላለሁ፡፡

Tuesday, May 10, 2016

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ ”ቃና” ወይስ ...?

(የመጨረሻው ክፍል)
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች፣ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ተያይዞ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት የተነሱ ሥጋቶችን መነሻ በማድረግ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችንንና ፊልሞቻችንን ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፡፡ በእነዚያ ጽሑፎች የእስካሁኑ የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ድራማ ሂደት በራሱ ሊፈታቸው ሲችል ያልፈታቸውን ችግሮቹን በመጠቆም የዘርፉ ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የ”ቃና” መምጣት አለመሆኑን ከማንሳቴም በተጨማሪ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች (በተለይም ደራሲዎች) ማድረግ ያለባቸውን ዝግጅቶች በጥያቄ መልክ በማቅረብ  የሥራዎቹን የጥራት ደረጃ መቃኘት ጀምሬ ነበር፤ ከዚያው ልቀጥል፡፡
በክፍል 2 ጽሑፌ ማጠቃለያ ላይ አንስቻቸው የነበሩትን ጥያቄዎች ከባለሙያዎቹ በሚገኝ ምላሽ፣ ወይም በድራማዎቻችን ላይ በሚደረግ ጥናት ለመመለስ ብንሞክር፣ አጥጋቢ መልስ እናገኛለን ብዬ አላምንም፡፡ ለምን? ቢባል፣ ሥራዎቹ ራሱ የሚናገሩት ይህንኑ ስለሆነ! እስቲ፣ እስከዛሬ ድረስ በአገራችን የቴሌቪዥን ቻናሎች የቀረቡትንና እየቀረቡ ያሉትን ድራማዎች በዓይነ-ልቦናችን እንመልከታቸው፡፡ ያለምንም ጉድለትና ግድፈት፣ ያለምንም አስተቺ አቀራረብ የተከታተልናቸው ድራማዎችን ማግኘት በጣም ይቸግራል፡፡ በእኔ ውሱን ግምገማ፣ ”እዚህ ላይ ልክ አይደለም” ሳይባል ያለፈ ሲሪያል ድራማም ሆነ ሲትኮም አላስታውስም፡፡ ይህንን ስል፣ በድራማዎቻችን ላይ ”ስለምን ጉድለት ተገኘ?” የሚል ጥያቄ እያነሳሁ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ጉድለትማ፣ እንኳን በእኛ አገር ጀማሪ የድራማ ሥራ፣ በታላላቆቹ የሆሊውድ ሥራዎችም ላይ አለ፡፡ ልዩነቱ፣ የእኛዎቹ በወረቀት ላይ ሊስተካከሉ ሲችሉ፣ ባለማወቅ ወይም በቸልተኝነት የሚፈጸሙት ግድፈቶች ብዙ መሆናቸው ላይ ነው፡፡ ባለፈው ጽሑፍ ላይ እንደጠቆምኩት፣ ”በወረቀት ላይ” ስል፣ በድራማው ድርሰት ላይ ሊደረጉ ስለሚችሉ ማስተካከያዎች ማለቴ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ እኔ በእስካሁኑ የቴሌቪዥን ድራማ ተመልካችነት ልምዴ፣ በድራማዎቻችን የተሳታፊዎች መግለጫ (credit) ላይ የፊልሙን ድርሰት የሚያርምና ማስተካከያ የሚሰጥ ባለሙያ (Script Editor) ሲጠቀስ አላየሁም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፣ በተለይ በቅርብ ጊዜዎቹ ሥራዎች ላይ፣ ቋንቋና አገላለጽ፣ የታሪክ ፍሰትና የሁነቶች ቅደም-ተከተል መሥመር ሲስቱ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያሳዩ ትዕይንቶች በሚጻፉበትም ሆነ በሚተወኑበት ጊዜ፣ የሙያዉን ሥነ-ምግባርና ትክክለኛ አሠራር ማሳየታቸውን ማረጋገጥ ላይ ድራማዎቻችን ግልጽ የሆነ ችግር አለባቸው፡፡ እንደምሳሌ፣ ፖሊስን የሚመለከት ትዕይንትን ብንወስድ፣ ሁሉም ማለት በሚያስደፍር ደረጃ፣ ድራማዎቻችን ፖሊስን በትክክል ለመግለጽ ይሳናቸዋል፡፡ የፖሊስ ሰላምታ አሰጣጥ፣ አለባበስ፣ የባለጉዳይ መስተንግዶ፣ የምርመራ ዘዴ፣ የተጠርጣሪ አያያዝ፣ ወዘተ …፣ በትክክል የተገለጸባቸውን የቅርብ ጊዜ ድራማዎቻችንን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ታዲያ፣ ጊዜ ወስዶ በማጥናት፣ የሙያውን ባለቤቶች በማነጋገር፣ ሙያው ያለው ሰው በተቆጣጣሪነት (supervision) እንዲመለከተው በማድረግ ሊስተካከል የሚችል እንጂ፣ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ሥራ አልነበረም፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎቻችን ግን፣ በአብዛኛው አይጨነቁበትም፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልን፣ የድራማዎቻችንን ግዙፍ፣ ግን በወረቀት ላይ ሊስተካከሉ የሚችሉ ስህተቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ እነዚህን ውስጣዊ ክፍተቶች ማስተካከል ቢቻል ኖሮ፣ ሌሎቹ ውጫዊ ችግሮች በድርሰቱ ውጤታማነት ሊሸፈኑ ይችሉ ነበር፡፡ ሌሎችም ብዙ ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም፣ ቀላሉን የድርሰት ላይ ችግር ካየን ለአሁኑ የሚበቃን ይመስለኛል፡፡ በመቀጠል ደግሞ፣  ”ቃና ቲቪ” በጀመረው አካሄድ ላይ ጥቂት ልበል፡፡
የ”ቃና” አካሄድ
ስለ”ቃና” ቲቪ አመሠራረትና የሥራ እንቅስቃሴ መቼም ብዙ ስለተባለ አሁን አልመለስበትም፡፡ ከርዕሳችን ጋር በተያያዘ ግን፣ ቻናሉ 70 በመቶ የሥርጭት ጊዜውን ለውጭ አገር ተከታታይ ድራማዎችና ፊልሞች በመመደብ በቀን የ24 ሰዓታት ሥርጭት የሚያቀርብ መሆኑን እንደመነሻ ብንይዘው መልካም ነው፡፡ ”ቃና” በዚህ የፊልምና ድራማ አቅርቦቱ፣ ከህንድ፣ ከቱርክ፣ ከጣሊያን፣ እና ከደቡብ ኮሪያ፣ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተመረጡ ድራማዎችን፣ ተከታታይ ፊልሞችን (series) እና ሲትኮሞችን በአማርኛ ቋንቋ የድምጽ ትርጉም (dubbing) ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ከሆነ፣ ይህንን አቀራረብ የመረጠው የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን ተመልካቾች ፍላጎት በሚመለከት ጥናት ካካሄደ በኋላ ነው፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያዊያንን የሳተላይት ቴሌቪዥን ተመልካችነት ልምድና ምርጫ አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ 50 በመቶ የሚሆኑት ተመልካቾች የውጭ ፕሮግራሞችን ያለምንም ባሕላዊ እሳቤዎችና በውጭ ቋንቋ እንደሚመለከቱ እንደተረዳ ይናገራል፡፡ በ12 ከተሞች መካሄዱ በተገለጸው ጥናት 3,500 ሰዎች ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን፣ በጥናቱ ግምት መሠረት በገጠርና በከተማ የሚኖሩና የሳተላይት ቴሌቪዥንን የሚከታተሉ 18.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጥና የውጭ አገር ፐሮግራሞችን እንደሚመለከቱ ተመልክቷል፡፡ ከ”ቃና” መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ኤሊያስ ሹልዝ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንደገለጹት፣ ጣቢያቸው የውጪዎቹን ፕሮግራሞች ለኢትዮጵያዊው ተመልካች እንዲስማሙ በጥንቃቄ የመረጠ ሲሆን፣ በራሱ ከሚያዘጋጃቸው የፕሮግራም ይዘቶች በተጨማሪ፣ የተመረጡ የአገር ውስጥ ፕሮግራሞችን ከውጭ ተባባሪዎች ጋር ለማቅረብ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡
ይህንን የ”ቃና”ን ሐሳብ እንደመነሻ ሐሳብ ጥሩ ነው ብለን ልንቀበለው የምንችለው ቢሆንም፣ ”ቃና” በኢትዮጵያ ሥራውን ለመጀመር ሲነሳ፣ በአገር ውስጥ ጥሩ ሥራዎች መኖር አለመኖራቸውን ለማወቅ የሞከረ አልመሰለኝም፡፡ ተሞክሮ ከሆነ እሰየው! ካልተደረገ ግን፣ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም፣ ጥሩ ሥራ በአገር ውስጥ ከተገኘ፣ ከቱርክም ሆነ ከህንድ፣ ከጣሊያንም ሆነ ከኮርያ፣ የተሻለ ቅርበት ያለውን ሥራ ተመልካቹ ይፈልጋል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን፣ ”ቃና” ይህንን ቢያስብበት መልካም ይሆናል እላለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ ”ቃና” ያለውን አቅም ለአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለማካፈል ፈቃደኛ ቢሆንና የልምድ ልውውጥ ቢደረግ፣ አሁን ያለውን የ70/30 ምጣኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገር ውስጥ ሥራዎች በሚያመች መልኩ ለማስተካከል ያስችላል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡
ለኢትዮጵያ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ዕድገት ምን ይደረግ?
ስለቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ድክመቶች በመጠኑ ጥቆማ ለመስጠት መነሻ የሆነኝ ”ቃና” የጀመረው አቀራረብ ያስነሳው አቧራ ይሁን እንጂ፣ ፊልሞቻችንና ድራማዎቻችን ሊያሻሽሏቸው ስለሚገቡ ነገሮች ማሰብ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ በኪነ-ጥበብ ማኅበራቱ የመጋቢት 21 መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችን በዕድሜው ትንሽ ነው፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ማደግና መብሰል ይጠበቅበታል፡፡ ለማደግ፣ ለመብሰልና ለመሻሻል ደግሞ ሊያደርጋቸው የሚገቡ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል፣ አሁኑኑ ሊያከናውናቸው የሚችሉትን ጥቂቶቹን እነሆ፡-
1.      ሙያዊ ዕውቀትን ማዳበር፡- በተደጋጋሚ ሲገለጹ ከሚሰሙት የዘርፉ ችግሮች መካከል አንደኛው የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ዕውቀታቸውን ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ዕድሉ ያላቸው ትምህርት ቤት ገብተው ሙያዉን ሊማሩ ሲችሉ፣ ያልቻሉት ደግሞ አማራጭ መውሰድ አለባቸው፡፡ ከሰሞኑ የ”ቃና” ጉዳይ ጋር ተያያዘው ሲነሱ ከሰማኋቸው የዘርፉ ችግሮች መካከል አንደኛው ዘርፉን በሚመለከት ለመማሪያነት በሚያገለግሉ መጻሕፍት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ ነው፡፡ ችግርነቱ ላይ ብስማማም፣ ባለሙያዎቹም ሆነ በዘርፉ ላይ ለመሠማራት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች፣ ባሉን ጥቂት አብያተ- መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን መጻሕፍትን ለማንበብ መሞከር ቀርቶ ከነመኖራቸውም የሚያውቋቸው አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የንባብ ባሕላችን ደካማነት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር፣ በዚህ የመረጃ ዘመን፣ ውቅያኖስ ከሆነው የኢንተርኔት መድረክ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ዋቢ መጻሕፍት በነፃ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በመጠቀም ዕውቀትን ማዳበር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሌሎች አገሮችን ፊልሞች በደፈናው ”ባሕል አደፍራሽ” ብሎ ከማውገዝ፣ ቀረብ ብሎ እንዴት እንደተሠሩ ማየት ሌላው የመማሪያ መንገድ ነው፡፡ በተለይ፣ በታሪክና በባሕላዊ ይዘታቸው ለእኛ ቀረብ የሚሉትን አገራት ፊልሞች ፈልገን ብንመለከት፣ ከታሪክ አወቃቀር አንስቶ እስከ ድኅረ-ዝግጅት ድረስ ብዙ ልንማርባቸው እንችላለን፡፡ ”የት እናገኛቸዋለን?” ከተባለ የተለያዩ መንገዶች አሁንም አሉ፡፡ በየዓመቱ በአዲስ አበባ (አልፎ አልፎ በሌሎች ከተሞች) የሚካሄዱ የውጭ አገራት የፊልም ፌስቲቫሎች አሉ፡፡ የአውሮፓ የፊልም ፌስቲቫል፣ አይቤሮ-አሜሪካን የፊልም ፌስቲቫል፣ የኢራን የፊልም ሳምንት፣ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እንዳለመታደል ግን፣ ብዙዎቹ የዘርፉ ተዋንያን እነዚህን መድረኮች ሲታደሙ አላይም፣ ከነመኖራቸውም አያውቋቸውም፡፡ እናም፣ ባለሙያዎቻችን ዓይንና ጆሯቸውን ከፍተው ቢመለከቱ ብዙ የዕውቀት ምንጮች አሉ፤ መጠቀም የእነርሱ ፋንታ ነው፡፡
2.     በትብብር መሥራት፡- እስከዛሬ እንደተመለከትነው፣ አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን በአንድ ፕሮዲዩሰር (የፕሮዳክሽን ድርጅት) ብቻ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህ የተበታተነ አሠራር ደግሞ ምሉዕነት የጎደለው ሥራ ለተመልካች እንዲቀርብ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ሐሳቦችና ዕውቀቶች በአንድ ላይ ተዋሕደው ሲቀርቡ ሊገኝ የሚችለውን መልካም ፍሬ እያሳጣን  ይገኛል፡፡ ስለዚህ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በአገር ደረጃ የተጠናወተንን የግለኝነትና የ”ጥሎ-ማለፍ” አባዜ ሰብረው በመውጣት፣ ሁለትና ሦስት የፕሮዳክሽን ድርጅቶች በአንድ ፕሮጀክት ላይ አብረው ቢሠሩ፣ በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በመሣሪያ፣ በልምድና በሌላውም ያላቸውን አቅም አዋሕደው በመሥራት ውጤታማ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ለተደራሲው ከማቅረባቸውም ባሻገር፣ ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑትን ውስጣዊ
ና ውጫዊ ችግሮች ለማስወገድ የሚችል ጠንካራ ግንባር መፍጠር ያስችላቸዋል፡፡
3.     የሕግ ማዕቀፍ እንዲፈጠር መጣር፡- የኪነ-ጥበብ ማኅበራት ”ሥጋታችን ነው” ባሉት የ”ቃና” ቴሌቪዥን አካሄድ ላይ ያሳዩትን ኅብረት፣ በመንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግም ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ መንግሥት ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠርና ያለውንም ከባቢ ለማጠናከር እንዲሠራ እነዚህ ማኅበራት ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ እስካሁን ግን ይህንን እያደረጉ ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ረቂቅ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ከቀረበ ወደ ሁለት ዓመት እየተጠጋ ነው፡፡ የዘርፉ የሙያ ማኅበራት ከዚያ ውይይት በኋላ ፖሊሲውን ሥራ ላይ የማዋሉ ሂደት ምን ላይ እንደደረሰ ጠይቀዋል? ተከታትለዋል? እኔ አላውቅም፡፡ ፖሊሲው በቶሎ ጸድቆ ሥራ ላይ ቢውል እኮ፣ አሁን የምንወያይባቸውን ችግሮች ለመፍታት በጠቀመ ነበር፡፡ የባሕል መበረዝን ለመከላከል፣ የፊልሞችን ደረጃ ለማውጣት፣ የዕድሜ ገደብን ከአገራችን ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለመወሰን፣ ለዘርፉ ሊሰጡ የሚገባቸውን ማበረታቻዎች ለመስጠት የሚያስችሉ ህጎችን ለማውጣት፣ወዘተ፣ የፖሊሲው መጽደቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ማኅበራቱ ለዚህ ቢተጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡
ማጠቃለያ
በተከታታይ ጽሑፎቼ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት ”ቃና”ን አስመልክቶ የተነሳውን ቅሬታ ለመሞገት ስሞክር፣ እስካሁን በዘርፉ የተሠሩትን ሥራዎች ዕውቅና በመስጠትም ጭምር እንደሆነ ከግንዛቤ እንዲገባልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የቴሌቪዥን ድራማዎችን እያቀረቡልን ላሉት የዘርፉ ባለድርሻዎች ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከተነሳው ቅሬታ ጋር ያለኝ ብቸኛ ልዩነት ”በእጃችን ባለው አቅም ልናስተካክለው በምንችለው ጉድለት የሚፈጠረውን የተመልካች አማራጭ ፍለጋ በውጭ አካል ላይ ማላከክ አግባብ አይደለም” የሚል ነው፡፡ የራስን ችግር ሳይፈቱ ሌላውን ለመውቀስ መሯሯጥ ሥራዎቹን ከነድክመታቸውም ጭምር በትዕግሥት የሚመለከተውን ተመልካች አለማወቅና አለማክበር ይሆናል፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራትን ከለመድንና በውስጥ ችግራችን ላይ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተን ሥራዎቻችንን በአግባቡ ከሠራን (ምንም እንኳን ሥራው ከባድና ረዥም ጉዞ ያለው ቢሆንም) ”ቃና”ም ሆነ ሌላ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አይደለም ሰባ በመቶ፣ መቶ በመቶ የሥርጭት ሰዓቱን ለውጭ ፊልምና ድራማ ቢሰጥ ሥጋት ሊሆን አይችልም፤ የራሱን ታሪክ በራሱ ቋንቋ መመልከት የሚፈልግ ተመልካች እስካለ ድረስ፡፡ ስለዚህ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችን፣ ”ሥራውን ከራሳችሁ ጀምሩ!”


(ይህ ጽሑፍ በሚያዚያ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡)

Tuesday, May 3, 2016

አንዳንድ ሐሳቦች- ስለኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያ (ክፍል ፪)

በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ለግል ቴሌቪዥኖች ፈቃድ ለመስጠት የተያዘውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ አንዳንድ ሐሳቦችን መሰንዘር ጀምሬ ነበር፡፡ በዚያ ጽሑፌ የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን ሚዲያ ትናንትና ዛሬ በግርድፉ እንደመንደርደሪያ በማንሳትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የቴሌቪዥን አገልግሎትን አስመልክቶ ለመሥራት ያቀደውን በመጥቀስ፣ ይህን ተከትሎም ብቃትና ጥራትን የሚመለከቱና ተያያዥ ሐሳቦቼን በተከታታይ እንደማቀርብ ገልጫለሁ፡፡
ወደ ዋናው ሐሳብ ከመግባቴ በፊት ባለፈው ጽሑፍ በመንደርደሪያነት ካነሳኋቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የነበረውን ጉዳይ የዛሬው ጽሑፍ ዋነኛ ነጥብ በማድረግ ጥቂት ለማለት እወዳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከ1995 ዓ.ም. በፊት የነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁለት ብቻ እንደነበሩ፣ እነርሱም ብሔራዊው ቴሌቪዥን (የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን) እና የትምህርት ቴሌቪዥን እንደሆኑ በክፍል አንድ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህ የጊዜው ብቸኛ ቴሌቪዥኖች መካከል ዘንድሮ 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ያከበረውን ኢቴቪ (የአሁኑ ኢቢሲ) አመሠራረትና ታሪክ በመጠኑ እንመለከታለን፡፡ በነገራችን ላይ፣ ይህ የኢቢሲ ”50ኛ ዓመት በዓል” ነገር ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም እየጠየቁት ያለው ይህ ጥያቄ ”ማነው አክባሪው?” የሚል ነው፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ አሁን እየተከበረ ያለው 50 ዓመት የቴሌቪዥን አገልግሎት የተጀመረበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደግሞ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ዘርፎችን አጣምሮ የያዘ እንደመሆኑ፣ በአገራችን ከተጀመረ ወደ 80 ዓመት ገደማ የሆነውን የሬዲዮ ዘርፍ ”ለምን ተወው?” የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ስለዚህ፣ እንደእኔ አስተያየት፣ መከበር የነበረበት 50ኛ ዓመት ሳይሆን 80ኛ ዓመት መሆን ነበረበት፤ አልያም የበዓሉ መጠሪያ ”የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን አገልግሎት 50ኛ ዓመት” ቢባል የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
 ከበዓሉ አከባበር ጋር አብረው ሊደረጉ የሚገባቸውና ያልተደረጉ ነገሮችንም ታዝቤያለሁ፡፡ በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን ጎብኝቸዋለሁ፡፡ የተቋሙን ታሪክ ለማሳየት የተደረገው ዝግጅት በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ፎቶግራፎችን፣ የቴሌቪዥን መሣሪያዎች እና የተለያዩ የተቋሙ ሰነዶችን ለሕዝብ ዕይታ ክፍት በማድረግ ተቋሙን ለማስተዋወቅ ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ታላቅና ጠቃሚ መድረክ (milestone) እንደመሆኑ መጠን፣ የተቋሙን ታሪክ በመጽሐፍ፣ በመጽሔት፣ በድረ-ገጽ፣ … አደራጅቶ በቋሚነት ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ በተጨማሪ ከጣቢያው የቀድሞና የአሁን ጋዜጠኞች መካከል በርከት ያሉት ፎቶግራፋቸውና ስማቸው ለዕይታ የቀረበ ቢሆንም ሳይቀርቡ የቀሩ ጋዜጠኞችም አሉ፡፡ ፎቷቸው ባይገኝ እንኳ ስማቸውን ማቅረብ ምን ይከብዳል? ይህ አለመደረጉ በበኩሌ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ ለወደፊቱ ይታሰብበት!
የኢቴቪ ታሪክ
አመሠራረት
ቴሌቪዥን የኢትዮጵያን ምድር የረገጠውና አገሪቱም የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆነችው ቴክኖሎጂው በመገናኛ መሣሪነት ለዓለም ከተዋወቀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ ቴሌቪዥንን በአገሪቱ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ የመጀመሪያው ሙከራ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን የዘውድ በዓል አስመልክቶ በአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ (ብሥራተ-ገብርኤል) አካባቢ ተዘጋጅቶ በነበረው ኤግዚቢሽን ላይ የእንግሊዙ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ያቀረበው ፕሮግራም ነበር፡፡ ቀጥሎም በ1952/53 ዓ.ም. ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አጣ፡፡ የብሥራተ-ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያና የቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣንም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደረገባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭቱን የጀመረው ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ስብሰባን በቀጥታ በማስተላለፍ ነበር፡፡ እንደቴክኖሎጂው አዲስነት በጊዜው ቴሌቪዥን በየቤቱ የገባበት ጊዜ ስላልነበረ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ የጉባዔውን ሂደት የተከታተለው በፊሊፕስ ኢትዮጵያ አማካይነት ከአዳራሹ ውጭ በተተከሉ ቴሌቪዥኖች አማካኝነት ነበር፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በይፋ መርቀው የከፈቱት አጼ ኃይለሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ”የቴሌቪዥን ጣቢያ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም፣ ወደፊት ድርጅቱ ተስፋፍቶ የሚሰጠው ጥቅም መላውን ሕዝባችንን እንደሚያዳርስ ተስፋ አለን፡፡” ብለው ነበር፡፡


አደረጃጀትና የሥራ እንቅስቃሴ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእንግሊዙ ቶምሶን ኩባንያና በፊሊፕስ ኢትዮጵያ በቀረበ ምክረ-ሐሳብ እና በኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበለት ብር 247‚000 በጀት፣ እንዲሁም  ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆኖ ሲቋቋም፣ ሥራውን ለማለማመድ በኃላፊነት በተሾሙት እንግሊዛዊ ሚስተር ጂ. ዋትሶንና ከዘመኑ ምርጥ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ በነበሩት አቶ ሳሙኤል ፈረንጅ ምክትል ኃላፊነት ይመራ ነበር፡፡ በጥቅምት ወር 1957 ሥርጭቱን ለመጀመር አዲስ አበባና አካባቢዋን መሸፈን የሚችል ባለ 500 ዋት ትራንስሚተር ከነሙሉ ድርጅቱ በማቋቋም ዝግጅቱን አጠናቀቀ፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው ሥርጭት በጀመረበት ወቅት በየቀኑ የሁለት ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃ ፕሮግራሞችን ያስተላልፍ የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪ በየሳምንቱ ቅዳሜ የአንድ ሰዓት የልጆች ፕሮግራምም ያቀርብ ነበር፡፡ በፕሮግራም ይዘት በኩል በጊዜው 30 በመቶ ፕሮግራሞቹ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ሲሆኑ፣ ቀሪው 70 በመቶ ከውጭ አገር በፊልም መልክ የሚመጣ ነበር፡፡
ዕድገት
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭት ከጀመረበት ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቁርና ነጭ ሥርጭት ለ20 ዓመታት ያህል ዝግጅቶቹን ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ በደርግ የሥልጣን ዘመን በ1976 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 10ኛውን የአብዮት በዓልና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምሥረታን ምክንያት በማድረግ ባለቀለም ሥርጭት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜም የሥርጭት ሰዓቱ ከሁለት ሰዓት ከአሥራ አምስት ደቂቃ ወደ አራት ሰዓታት በቀን ከፍ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ ቅዳሜና እሁድም በሥርጭት ቀናትነት ተጨምረዋል፡፡ ይህ የሥርጭት ሰዓት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ እየጨመረ የሄደ ሲሆን፣ በተለይም ”120” የተሰኘው የሰንበት ፕሮግራም ከተጀመረ በኋላ የእሁድ ፕሮግራሙ የአየር ጊዜ ወደ 9 ሰዓታት አደገ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የፕሮግራሞች ብዛት መጨመርና የሳተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የ24 ሰዓታት ሥርጭት በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡
በፕሮግራሞች ይዘትና ስብጥር ረገድ፣ በ1957 ዓ.ም. በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጀመረው ሥርጭት በ1983/84 ዓ.ም. የትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ ፕሮግራሞችን አካቶ መቅረብ የጀመረ ሲሆን፣ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ደግሞ የአፋርኛና የሶማሊኛ ቋንቋ ሥርጭቶችን በማከል የቋንቋ ስብጥሩን አስፍቷል፡፡ ለ37 ዓመታት በአንድ ቻናል ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ኢቴቪ፣ ”ቲቪ አፍሪካ” ከተባለው የቴሌቪዥን ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የቲቪ አፍሪካን ፕሮግራሞች ለማስተላለፍ በ1994 ዓ.ም. ሁለተኛ ቻናል ከፍቷል፡፡ ይህ ቻናል ቲቪ አፍሪካ በኪሳራ ምክንያት ሲዘጋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማስተላለፍ የጀመረ ሲሆን፣ ኢቲቪም የሥርጭትና የፕሮግራም አቅሙን ለማዳበር በተባባሪ ድርጅቶች በሚሠሩ ፕሮግራሞች የሚሸፈነውን ኢቴቪ 3 በ2003 ዓ.ም.  ሥራ አስጀምሯል፡፡
በሰው ኃይል በኩል፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ ሲጀምር 27 ኢትዮጵያዊያንና 5 እንግሊዛዊያን ሠራተኞች ነበሩት ይላል ለ50ኛው ዓመት በዓል የታተመው ብሮሹር፡፡ ሌሎች የመረጃ ምንጮች ደግሞ ቁጥሩን ወደ 16 ዝቅ ያደርጉታል (ለማንኛውም ”ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው”ና የመጀመሪያውን ቁጥር እንውሰደው)፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮ ዘርፉን ጨምሮ 2,222 የሚደርሱ ሠራተኞች እንዳሉት ከላይ የጠቀስኩት ብሮሹር ይናገራል፡፡
እንግዲህ የኢቴቪ (የአሁኑ ኢቢሲ) ታሪክ በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ ይህንን ታሪክ በመጠኑ መዳሰስ የፈለግሁት ኢቴቪ የአገራችን የመጀመሪያ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆኑ ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ያለውን ታሪክ ለመመልከት መነሻ ሊሆን ይችላል በሚል እንጂ የተሟላ አለመሆኑን መግለጽ ይገባኛል፡፡ ምናልባት በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁትን የመረጃ አቅርቦት ሐሳብ ኢቢሲ ተግባራዊ የሚያደርገው ከሆነ ሙሉ መረጃዎችን ከባለቤቱ በቀጥታ ማግኘት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ጽሑፌ አሁን በሥርጭት ላይ የሚገኙትም ሆኑ ሥርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኙት ቴሌቪዥኖቻችን ”ምን ዓይነት ፕሮግራሞችን ማቅረብና ምን ምን ተጓዳኝ ጉዳዮችን ማሰብ ይኖርባቸዋል?” በሚሉት ጥያቄዎች ላይ የምለው ይኖረኛል፡፡
የመረጃ ምንጮች: መነን መጽሔት፣ 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 2፣ ኅዳር 1957 ዓ.ም. ፣ BBC World Service Trust. African Media Development Initiative (via Wikipedia) ፣ የኢቢሲ 50ኛ ዓመት ብሮሹር፡፡

Sunday, May 1, 2016

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ ”ቃና” ወይስ ...?

የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ብቃትና ጥራት ሲፈተሽ …
(ካለፈው የቀጠለ)
በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ፣ ቃና ቴሌቪዥን የውጭ አገራት ተከታታይ ፊልሞችን በአማርኛ ትርጉም ማቅረቡን ተከትሎ የኪነ-ጥበብ ማኅበራት ያወጡትን መግለጫ መግለጫ መነሻ በማድረግ፣ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማዎቻችንን ሥጋት የሚፈትሽ ጥቅል ሐሳብ ሰጥቼ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ይህንን ሐሳቤን በዝርዝር ለማቅረብና በአሁኑ ወቅት የቀረቡትንና በመቅረብ ላይ የሚገኙትን የቴሌቪዥን ድራማዎች የብቃትና ጥራት ደረጃ በተመልካች ዕይታ በጥቅሉ ለመገምገም እሞክራለሁ፡፡
በመጀመሪያ ግን፣ ባለፈው ጽሑፍ ላይ አንስቼው ያለፍኩትን አንድ ነጥብ ለማብራራት እፈልጋለሁ፡፡ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራቱ በመጋቢት 21 መግለጫቸው ”ሥጋቶች” ብለው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የባሕል ወረራን የሚጠቅሰው ከቴሌቪዥን ድራማ ሕልውና ጋር ተያይዞ የቀረበውን ሥጋት ለመደገፍ የመጣ እንጂ ከመቆርቆር የመነጨ ነው ብዬ እንደማላምን ገልጬ ነበር፡፡ ምክንያቴን ላስቀምጥ፡፡
እነዚህ ማኅበራት እውነት ለባሕል ተቆርቋሪ ከሆኑ እስከዛሬ ድረስ ስንትና ስንት ባሕል ሸርሻሪ ሥራዎች በአገር ውስጥ ሲሠሩና ከውጭ እየመጡ ሲቀርቡ ለምን ዝም አሉ? ዛሬ በቃና ቲቪ እየቀረቡ ከሚገኙት ድራማዎች መካከል የተወሰኑት በሌሎች ቻናሎች የቀረቡና ለዕይታ በቀረቡባቸው አገሮች (ለዚያውም ጥብቅ የባሕል ጥበቃ ሥርዓት ባለባቸው) ቅሬታ ያልቀረበባቸውና ያልታገዱ መሆናቸውን ሳያውቁ ቀርተው ነው? ደግሞስ፣ ማኅበራቱ ለዕይታ በቀረቡት ፊልሞች ላይ አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ምን ያህል ፊልሞችን ተመልክተዋል? አንዳንድ የማኅበራቱ አባላት የተወሰኑትን መመልከታቸውንና ጥሩ ያልሆኑ የፊልሞቹን ክፍሎች አስመልክቶ ለቃና ኃላፊዎች አስተያየት መስጠታቸውን ሲናገሩ የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ የትኞቹ ፊልሞች እንደሆኑና የተሰጣቸውን ምላሽ ግን ወይ እነርሱ አልተናገሩም፣ ወይ እኔ አልሰማሁም፡፡ እኔ የተወሰኑትን ፊልሞች በኤምቢሲ ቻናሎች ላይ የተመለከትኩ ሲሆን፣ ስለተቀሩትም  ፊልሞች ዝርዝር መረጃዎችን ከተለያዩ ድረ-ገጾች ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ ባገኘሁት ውጤት ታዲያ እነዚህ ፊልሞች ጉልህ የሆነ ሞራልና ሥነ-ምግባርን የሚያጎድፍ ይዘት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር አላገኘሁም፣ አለ ቢባል እንኳ ”ቃና” በኃላፊነት መንፈስ ከዕይታ ሊያወጣቸው የሚችል እንጂ በእኛው አገር እየተሠሩ ከሚቀርቡት መሰል ሥራዎች ብዙም ያልተለዩ እንደሆኑ ነው የሚታየው (እዚህ ላይ ”ተሳስተሃል” ብሎ በማስረጃ የሚሞግተኝ ካለ ለማድመጥና ካስፈለገም ለመታረም ዝግጁ ነኝ)፡፡ እናም፣ የባሕል ወረራው ”ሥጋት” ደጋፊ ብቻ እንጂ በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም ባይ ነኝ፡፡                                                                                               
ዋናው ችግር ምንድን ነው?       
የመጀመሪያውን ክፍል ጽሑፍ ሳጠቃልል ” …ዋነኛው ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የቃና መምጣት አይደለም…” ብዬ ነበር፡፡ ”ሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ አልቀረቡም” ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ አንድ የኪነ-ጥበብ ሥራ ”ደረጃውን ጠብቋል” የሚያሰኙት ነጥቦች ምን ምን እንደሆኑ በቅድሚያ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
”ኪነ-ጥበብ” ስንል በይበልጥ የሚታዩና የሚደመጡ ጥበባዊ ሥራዎችን (ክዋኔዎችን) ማለታችን ነው፡፡ እነዚህ ክዋኔ-ጥበቦች በእንግሊዝኛ ”Performing Arts” የሚባሉት ሲሆኑ ሙዚቃን፣ ቴአትርን፣ የመድረክና የቴሌቪዥን ድራማን፣ ሲኒማንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላሉ፡፡ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች ለተመልካችና ለአድማጭ ከመቅረባቸው በፊትም ሆነ ከቀረቡ በኋላ በተደራሲያን፣ በባለሙያዎች፣ እና በሐያሲያን የሚገመገሙባቸው የተለያዩ መስፈርቶችና የደረጃ መስጫ ነጥቦች አሉ፡፡ የባለሙያዎችና የሐያሲያኑን ነጥቦች ባለቤቶቹ በስፋት ሊያብራሩት የሚችሉት ቢሆንም፣ በእኔ በኩል ጥቂቶቹን ብገልጽ ደስ ይለኛል፡፡
በዴንማርክ  የአርሁስ ዩኒቨርሲቲ (University of Aarhus) ባልደረቦች የሆኑት ካረን ሃና፣ ዮርን ላንግስቴድ፣ እና ቻርሎቴ ሮድሃም ላርሰን ”Evaluation of Artistic Quality in the Performing Arts” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2003 ዓ.ም. ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ የአንድ ኪነ-ጥበባዊ ሥራ የጥራት ደረጃ (Artistic Quality) በሦስት ነጥቦች እንደሚፈተሽ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ነጥቦች፤ ዓላማ (Intention)፣ አቅም (Ability)፣ እና አስፈላጊነት (Necessity) ናቸው፡፡ በእነዚህ ነጥቦች ጥምረት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ለመገምገም የሚረዳ The IAN Model የሚል ስያሜ የሰጡትን ሞዴል አጥኚዎቹ አስተዋውቀዋል (IAN= Intention, Ability, Necessity)፡፡ በዚህ ሞዴል አማካይነት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መገምገም እንደሚቻል ጥናቱ ይገልጻል፡፡
ሙያዊ የሆነውን ይህንን የመገምገሚያ መንገድ ዝርዝር ጉዳይ ለባለሙያዎቹ ልተወውና፣ ”እንደተደራሲ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን እንዴት እንገመግማለን?” የሚለውን ጥያቄ ከግል ተሞክሮዬና ምናልባትም ብዙሃኑ ተደራሲ ይጋራኛል ብዬ ከማስበው በመነሳት መልስ ልስጥ፡፡ ማንኛውም ኪነ-ጥበባዊ ሥራ በብቸኝነት የሚቀርበው ለተደራሲው (audience) ነው፡፡ ተደራሲው (አድማጭ/ተመልካች) የኪነ-ጥበብ ሥራውን ለመመልከት ወይም ለማድመጥ ሲዘጋጅ ከሥራው የሚጠብቃቸው ጥቅሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል የተወሰኑት መዝናናት፣ መመሰጥ፣ መማር፣ የማሰቢያና የመወያያ ርዕስ ማግኘት፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ለአንድ ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን በሙሉ ትኩረት ለሚከታተል ተደራሲ እነዚህን ጥቅሞች ማግኘት ትልቁ ትርፉ ሲሆን፣ ማጣቱ ደግሞ ኪሳራው ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎችን ”ጥሩ” ወይም ”መጥፎ ” ብሎ ደረጃ ለመስጠት እነዚህና ሌሎችንም ነጥቦች በመጠቀም ግምገማ ያደርጋል፡፡ በግምገማው ውጤት መሠረትም የሚፈልገውን ሥራ ይመርጣል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን የተደራሲ ፍላጎቶች መሠረት አድርገን የአገራችንን የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የብቃት ደረጃ ብንገመግም፣ ከጥቂት ሥራዎች በስተቀር ሙሉ በሙሉ የተደራሲን ፍላጎት አርክተዋል የሚባሉ ሥራዎችን በስፋት አናገኝም፡፡ በተለይ አሁን ርዕሰ-ጉዳያችን በሆኑት ፊልሞቻችንና የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ላይ የበዛ እንከን እንደሚገኝ አልጠራጠርም፡፡ እስካሁን በዚህ ላይ የተደረገ ጥናት ስለመኖሩ መረጃው የለኝም፤ ቢኖረንና ብንመለከተው የበለጠ ለመተማመን ይረዳን ነበር፡፡ ባደጉት አገሮች የሚሠራበት የግምገማ ሥርዓት (Rating System) የሚያስፈልገን ለዚህ ጊዜ ነበር፡፡  ይህ ሥርዓት ቢተገበር ውጤቱ ከፍ ሲል ከጠቀስኩት እንደማይለይ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችንም ይህንን ሐቅ አይክዱትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ”ለምን ይህ ሆነ?” የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያነጋግር ይመስለኛል፡፡ ተደጋግሞ የሚገለጸው የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ የመሣሪያዎች ውድነትና በቀላሉ አለመገኘት፣ የታክስ ጫና፣ የመሥሪያ ቦታ አለማግኘት፣ …፣ አሁንም በችግርነት የሚነሳና እኔም የምስማማበት ቢሆንም፣ ዋነኛው ችግር ይህ አይመስለኝም፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ጥራት ያላቸውን የቴሌቪዥን ድራማዎች የመሥራት ጉዳይ በአብዛኛው በወረቀት ላይ ሊያልቅ የሚችል ነው፡፡  ” በወረቀት ላይ” ስል ”በድርሰቱ ላይ” ማለቴ ነው፡፡ የድራማው ደራሲ(ዎች) ሊጽፉበት ስላሰቡት ሐሳብ በቂ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ? መጻሕፍትንና መዛግብትን ያገላብጣሉ? ባለሙያዎችንና ሌሎች መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎችን ያነጋግራሉ? የጻፉትን ድርሰት በሌሎች ያስገመግማሉ? በውይይትና በአስተያየት ያዳብራሉ? ጥርት ያለ ሥራ እስኪሆን ድረስ ደጋግመው ያሹታል? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ይመስለኛል የችግሩን ምንጭ የሚጠቁመን፡፡
(ይቀጥላል)
(ይህ ጽሑፍ በሚያዚያ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡)

Wednesday, April 20, 2016

አንዳንድ ሐሳቦች- ስለኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያ (ክፍል ፩)

እንደ መንደርደሪያ
ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለግል ቴሌቪዥን ፈቃድ መስጠት በመጪው ዓመት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ መናገራቸውን የሚገልጽ ዜና አነበብኩ፡፡ የታሰበው ዕውን መሆኑ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ቢሆንም፣ ሐሳቡ መነሳቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነውና አቶ ልዑልንና አዲስ አድማስን ”ቸር ወሬ ያሰማችሁ!” ልላቸው እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የግል ቴሌቪዥን መኖር ጉዳይ ላለፉት 24 ዓመታት ተደጋግሞ ሲነሳ የቆየ ነው፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በፊት በአገሪቱ የነበሩት አንድ ብሔራዊ ቴሌቪዥንና አንድ የትምህርት ቴሌቪዥን ብቻ መሆናቸው የቴሌቪዥን አገልግሎትን ውስን ይዘት ያለው እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ሐሳብን በነፃነት እና በተለያዩ መንገዶች መግለጽ በመርህና በሕግ የተረጋገጡ መብቶች መሆናቸውን ተከትሎ ከመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ በሆነው የብሮድካስት ሚዲያ ዘርፍ የኅትመት ሚዲያውን ያህል እርምጃ ያለመታየቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ ዋነኛው ጥያቄ የአማራጭ ሚዲያ መኖር ሲሆን፣ በተያያዥነትም በአሁኑ ወቅት በሥርጭት ላይ ያሉት የቴሌቪዥን ሚዲያዎች የአገልግሎት ጥራት፣ የጊዜ ርዝማኔ፣ እና የሥርጭት ተደራሽነት አብረው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የብሮድካስት ሚዲያን ለማስፋፋት የተለያዩ እርምጃዎች ባለፉት ዓመታት ተወስደዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ከመፍጠር አንስቶ የብሮድካስት ሚዲያዎች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ በሕግ ደረጃ በ1991 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. የወጡት የብሮድካስት አዋጆች ለዘርፉ መስፋፋት በመንግሥት በኩል ያለው ፈቃደኝነት ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ሲሆኑ፣ አዋጁን ተከትለው በቁጥር በርከት ያሉ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ ተቋቁመው መንቀሳቀሳቸው ለዘርፉ ማደግ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ሊታይ የሚችል እርምጃ ነው፡፡
አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው የብሮድካስት አዋጅ ቁጥር 533/1999 አንቀጽ 2(2) መሠረት የብሮድካስት አገልግሎት ማለት ”ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ፣ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት” ነው፡፡ ከዚህ ትርጉም አንፃር በአገራችን በአሁኑ ወቅት በብዛት በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ በቴሌቪዥን ዘርፍ ግን ከመንግሥታዊው ኢቢሲ፣ ከተወሰኑ የክልል ቴሌቪዥኖች እና መሠረታቸውን በውጪ አገራት አድርገው በሳተላይት ከሚሠራጩ የግል ቴሌቪዥኖች በስተቀር በቁጥርም ሆነ በጥራት በቂ የሆኑ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች የሉም፡፡
ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች እጥረትና የጥራት ውሱንነት የአገራችንን የቴሌቪዥን ተመልካች አማራጭ በማሳጣቱ የተነሳ በርካታ ሕዝብ ወደውጪ ሚዲያዎች ፊቱን እንዲያዞር ተገዷል፡፡ በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በነፃ የሚሠራጩ የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻናሎች (free-to-air TV channels) በአብዛኛው የቴሌቪዥን ተመልካቾች ዘንድ በአማራጭነት ተወስደዋል፡፡ እነዚህ ቻናሎች ደግሞ በአመዛኙ በአረብኛ ቋንቋ የሚቀርቡ በመሆናቸው ተመልካቹ በማይገባው ቋንቋ ፕሮግራሞችን ለመከታተል መገደዱ ቻናሎቹን ከመማሪያና መዝናኛነት ይልቅ የጊዜ ማሳለፊያ ብቻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች በመነሳት በአገራችን አማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ በስፋት መኖር አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ጸሐፊ ያምናል፡፡
በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጥቅምት 6 ዕትም፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለ22 የመንግሥትና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን ይገልጻል፡፡  የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለጋዜጣው እንደተናገሩት፣ በዚህ ዓመት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር ሲጠናቀቅ ከሚኖሩት 22 ቻናሎች መካከል ለእያንዳንዱ ክልልና ለኢቢሲ ቻናሎች የሚሰጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ቻናሎች ደግሞ ለግል ድርጅቶች በጨረታ ይሰጣሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው የቻናሎች ክፍፍል መሠረት፣ ሦስት ቻናሎች ለግል ብሮድካስተሮች ተመድበዋል፡፡ ቀሪዎቹ 19 ቻናሎች ደግሞ ለመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያዎች የሚሰጡ ይሆናል፡፡
ሦስት የግል ቻናሎች ካለው ፍላጎት አንፃር አነስተኛ ቢሆኑም፣ የግል ብሮድካስተሮችን ወቅታዊ አቅም ከግምት ስናስገባ ለጊዜው በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁም ነገሩ ግን ብዛታቸው ሳይሆን ጥራትና ብቃት ነው ባይ ነኝ፡፡ ልናተኩርበትም የሚገባው ይኸው የጥራትና ብቃት ጉዳይ ነው፡፡ ደጋግሜ ያነሳሁት የአማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ አስፈላጊነት መነሻው እስካሁን ያሉን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚፈለገው የጥራትና የብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው መሆኑን ስንመለከት፣ ስለእነዚህ ጉዳዮች የማሰብና የመወያየትን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ  ይመስለኛል፡፡ ይህ የጥራት ጉዳይ አሁን በሥርጭት ላይ ያሉትንም ሆነ ወደፊት ሥራ ይጀምራሉ የሚባሉትን ጣቢያዎች በእኩል የሚመለከት በመሆኑ፣ በእኔ በኩል ያሉኝን ዕይታዎችና ተያያዥ ሐሳቦች በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡


ማስታወሻ-   ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ ስድስት ወራት ያለፉት ቢሆንም፣ በጊዜው በጋዜጣ እንዲወጣ ተልኮ ሳይወጣ የቀረ  ጽሑፍ ነው፡፡  አሁን ግን ከርዕሰ-ጉዳዩ ወቅታዊነት አንፃር በዚህ ብሎግ ላይ ቀርቧል፡፡

Saturday, April 16, 2016

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ "ቃና" ወይስ ...?

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት ”ቃና” የተባለው የሳተላይት ቴሌቪዥን እያቀረበ ባለው የፕሮግራም ይዘት ላይ ”አለን” ያሉትን ሥጋትና ተቃውሞ የሚገልጽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በመግለጫው ላይ የተነሱት ሐሳቦች በሁለት ነጥቦች ተጠቃለው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነርሱም፡-
1.      የቃና ቲቪ አካሄድ የአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋል፣
2.     በቃና ቲቪ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ለባሕል ወረራ ያጋልጣሉ
የሚሉ  ናቸው፡፡
በመሠረቱ፣ እነዚህ ማኅበራት የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብና ባሕልን አስመልክቶ የተቆርቋሪነት ሥጋታቸውን መግለጻቸው ከምንም በፊትና በላይ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ነገር ግን፣  የእስከዛሬ ልምዳችንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችንን እንቅስቃሴ ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ ”የማኅበራቱ እውነተኛ ሥጋት ምንድን ነው?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም አብረው ይመጣሉ፡፡ እኔም በመግለጫውና ከመግለጫው በኋላ በተሰሙትና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተገለጹት ሐሳቦች በመነሳት አስተያየቴን ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
የሥጋቱ ምንጭ ምንድን ነው?
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራቱ በመግለጫቸው የቃና ቲቪ አካሄድ ”ያስከትላቸዋል” ያሏቸውን ”ጉዳቶች” ከላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች አንፃር በሚከተለው መልኩ አስቀምጠዋቸዋል፡፡
·         ”ጣቢያው አጭር ዕድሜ ያለውን የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችንን በማቀጨጭ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚያሰናክል በመሆኑ ፕሮግራሙን በድጋሚ ሊከልስ ይገባዋል፡፡”
·         ”በጣቢያው የሚቀርቡት የውጭ አገር ፊልሞች ንግድ-ተኮር በመሆናቸው ምንም ዓይነት ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት የላቸውም፡፡”
እነዚህ የማኅበራቱ ”ሥጋቶች” ”መነሻቸው ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ፣ በይፋ የምናገኘው መልስ ”ከዘርፉ ሕልውና ከመጨነቅና የኢትዮጵያን ባሕል ከወረራና ከመበረዝ ለመከላከል ከማሰብ” የሚል ነው፡፡ የተሸፈነውና ትክክለኛው ምላሽ ግን አሁን ያሉት የዘርፉ ተዋንያን ”የእንጀራ ገመድ መበጠስ” ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በኪነ-ጥበቡ (በፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽኖች) ዘርፍ የሚሠሩ 10‚000 ያህል ”ባለሙያዎች” አሉ (”ባለሙያዎች” የሚለውን ቃል በትዕምርተ-ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት በዕውቀት የተደገፈ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ቁጥር ይህን ያህል ደርሷል ብዬ ለማመን ስለሚከብደኝ ነው)፡፡ የእነርሱ ሥጋት ”እነዚህ ሁሉ ”ባለሙያዎች” በቃና ቲቪ አካሄድ ምክንያት ሥራ-አጥ ይሆናሉ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛውና ከባሕል ወረራ ጋር የሚገናኘው ሐሳብ የመጀመሪያውን ሐሳብ ለመደገፍና ለማኅበራቱ አቋም ጉልበት ለመስጠት የመጣ እንጂ በእውነት ማኅበራቱ ዛሬ ላይ ተቆርቁረውበት የሚያነሱት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቴን ወደፊት እመለስበታለሁ፡፡
የሥጋቶቹ የተጨባጭነት ልክ
በኪነ-ጥበብ ማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች ትክክለኛ ሥጋት መሆናቸውን ለመፈተሽ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የቴሌቪዥንና የፊልም ዘርፍ ሁኔታ መቃኘት የሚያስፈልግ  ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ቻናሎች ቁጥር (በሳተላይት ከውጭ የሚተላለፉትን ጨምሮ) ወደ 20 ገደማ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ቻናሎች መካከል ቀዳሚ የሚባሉት ብሔራዊና የክልል ቴሌቪዥኖች እንዲሁም የግል ቻናሎች ለቴሌቪዥን ድራማዎችና የአገር ውስጥ ፊልሞች ሰፊ የአየር ሰዓት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንደ ማሳያ ኢቢሲ እና ኢቢኤስን ብንወስድ፣ ኢቢሲ አምስት ድራማዎችን (አራት ሲሪያል እና አንድ ሲትኮም) ሳምንቱን በሙሉ በሁለት ቻናሎች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢቢኤስ በበኩሉ አራት ድራማዎችን (ሁለት ሲሪያል እና ሁለት ሲትኮም) ያቀርባል፡፡ በፊልም በኩልም ሁለቱም ቻናሎች ሳምንታዊ የታላቅ ፊልም (feature films) ፕሮግራሞች አሏቸው፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም ድራማዎችና ፊልሞች ከመደበኛ ቀናቸው በተጨማሪ በድጋሚ የሚቀርቡ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ከዚህ አንፃር ዛሬ ላይ በተለይ ለቴሌቪዥን ድራማዎች ቀን ወጥቶላቸዋል ማለት እንችላለን፡፡ ሚዲያዎቹም ተጨማሪ ድራማዎችን እንደሚፈልጉ እየሰማን ነውና በብዛት ደረጃ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ዕድሉ ሰፍቷል ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ”ጥራት ላይ እንዴት ናቸው?” የሚለው ይሆናል፡፡ ምናልባትም የአሁኑ የማኅበራቱ ሥጋት እውነተኛ መነሻ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፡፡
የጥራትን ጉዳይ ከይዘት ጋር አጣምሮ መመልከት የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይዘት ሐሳብን፣ መልዕክትንና አቀራረብን የሚወስን በመሆኑ፡፡ ይዘት (content) ለተደራሲው ልናቀርብ የፈለግናቸውን ጉዳዮችና የምናነሳቸውን ጥያቄዎች በአንድነት ሰብስቦ የሚይዝ ቋት እንደመሆኑ፣ የይዘት ምርጫና ውሳኔ በሚተላለፈው ሐሳብና መልዕክት ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ይዘት በሚዲያዎቹ ምርጫ የሚወሰኑ ከሆነ፣ የደራሲዎችና የሐሳብ አመንጪዎች ምናብ በሚዲያው ምርጫ፣ አለፍ ሲልም ጫና ምክንያት ሊገደብ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ቢያዳግተኝም፣ የጊዜያችን የቴሌቪዥን ድራማዎች የዚህ አካሄድ ሰለባ መሆናቸውን በተባራሪ ከምንሰማቸው ሁነቶችና እንደተመልካችም ከምናስተውላቸው የሐሳብ መሳሳቶች በመነሳት መናገር እችላለሁ፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመለከትናቸውንና እየተመለከትናቸው ያሉትን የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማዎች ከይዘትና ጥራት አንፃር ስገመግማቸው፣ የሚያነሷቸውን ርዕሰ-ጉዳዮች በአጠቃላይ ”በጣም ጥሩ” የሚል ደረጃ እሰጣቸዋለሁ፡፡ የአብዛኞቹ መነሻ ታሪክ ትኩረትን የሚስብ፣ አንዳንዴም የሚያመራምርና የሚያወያይ ነው፡፡ የሚያነሱት ጭብጥ በአብዛኛው ለኢትዮጵያዊያን ቅርብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ድራማዎቻችን ከፍተኛ የተከታታይ ቁጥር አስመዝግበዋል ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ግን፣ ድራማዎቻችን ቀላል የማይባሉ ቴክኒካዊ ግድፈቶችን የተሸከሙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ድራማዎች መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን የማያውቁ፣ ሌሎቹ በአንድ ድራማ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን አጭቀው ሁሉንም ለማሳየት የሚውተረተሩና ያልተሳካላቸው፣ ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም ደግሞ ድርሰቶቻቸውን በበቂ ጥናትና መረጃዎች ያላስደገፉ፣ በተለይም ደግሞ ሙያ-ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ የተአማኒነት ጉድለት ያለባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ በእኔ አመለካከት፣ በወረቀት ላይ ተስተካክለው ሊቀርቡ የሚችሉ እንጂ፣ አሁን በቃና ቲቪ ጉዳይ ላይ እንደሚነሳው ከገንዘብ አቅም ማነስ፣ ከግብዓቶች ውድነት፣ ወዘተ፣ ጋር የሚያያዙ አይደሉም፡፡ ይህንን እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው ባለሙያዎቻችን ናቸው እንግዲህ አዲስ አቅጣጫ ይዞ የመጣውን ሚዲያ በገና-ለገና ”ከገበያ ያስወጣናል” በሚል ሥጋት እርምጃ እንዲወሰድበት እየወተወቱ ያሉት፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጉድለቶች በጥቅሉ ያስቀመጥኩት፣ አሁን በማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች በተወሰነ ደረጃ መሠረት ያላቸው ቢሆኑም፣ ዋነኛው ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የቃና መምጣት አይደለም ለማለት ነው፡፡ በቀጣይ ይህን ሐሳቤን በዝርዝር ለማቅረብና የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማ ወቅታዊ ሁኔታ ከቃና ቲቪ አካሄድ አንፃር ለመገምገም እሞክራለሁ፤ እግረ-መንገድም ”ቃና” ያስተዋወቀውን አቀራረብ በሂሳዊ ዓይን ለመመልከት፡፡ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ምን ቢያደርግ የተሻለ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የምሰጠው አስተያየት ይኖረኛል፡፡

(ይህ ጽሑፍ በሚያዚያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡)

Tuesday, April 12, 2016

የማለዳ ትዝብቴ

ዛሬ ማለዳ በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የስፖርት ዜና ላይ ያዳመጥኩት ዜና በጣም አስገርሞኛል፡፡ ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ሲጫወቱ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች አሉላ ግርማ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ተጫዋቹ ሕክምና እንዲደረግለት ከሜዳ መውጣት ነበረበት፣ ነገር ግን ለዚህ የሚያገለግለው ቃሬዛም ሆነ አምቡላንስ በስታዲየሙ አልነበረም፡፡ አምቡላንሱ በሥፍራው የተገኘው በሁለተኛው ግማሽ ላይ ነበር፡፡ አሉላም በዚህ ምክንያት ከሜዳ በቡድን ጓደኞቹ ተሸካሚነት ለመውጣት ተገደደ፡፡
እንዴት እግር ኳስን የመሰለ፣ ለጉዳት ሊዳርግ የሚችል አካላዊ ንክኪ ያለበት ጨዋታ ቢያንስ ያለቃሬዛ ይካሄዳል? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ”ጉዳዩን ተመልክቼ እርምጃ እወስዳለሁ” ብሏል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሸገር ስፖርት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ኃላፊው በዚህ ጉዳይ ከአምቡላንስ አቅራቢው ተቋም በተጨማሪ የጨዋታው ኮሚሽነርም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲገልጹ፣ የኮሚሽነሩን ማንነት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ”በሰዓቱ ስብሰባ ላይ ስለነበርን ኮሚሽነሩ ማን እንደነበሩ አላወቅንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጣም ያሳፍራል! እንዴት አንድ አወዳዳሪ አካል፣ ራሱ የመደበውን የጨዋታ ታዛቢ ማንነት ”አላውቅም” ይላል? መቼም የጨዋታ መረጃ በጽሑፍ ሳይመዘገብ አይቀርም፡፡ ”እነ እከሌ ዳኞች፣ እከሌ ኮሚሽነር” ብሎ ለሁሉም ወገን የሚያሳውቅ ይመስለኛል፡፡ እና፣ ፋይል አገላብጦ እንኳን ኮሚሽነሩ እገሌ ነው ማለት ይቸግራል? እንዲህ ዓይነቱ ቀልድ የሚያበቃው መቼ ይሆን?!

Friday, February 12, 2016

Art vs Business: Probable Cause for the Oscars Controversy?

The recently-reopened issue of race and color in the United States (though hasn’t been closed in the first place) has taken a new course, and continues on a new battlefield. The new destination: Hollywood!
It all began on January 16, when actress Jada Pinkett-Smith expressed outrage over the nominations of this year’s Academy Awards, which were announced on January 14. She tweeted, “At the Oscars … people of color are always welcomed to give out awards … even entertain, but we are rarely recognized for our artistic accomplishments. Should people of color refrain from participating all together?”
Since then, big names, from Spike Lee to Whoopi Goldberg, from Janet Hubert to Tyrese, from Helen Mirren to George Clooney…, all weighed in on the issue, adding their voices both for and against the apparent “Boycott Oscars” movement. Even Donald Trump, the GOP presidential hopeful, spoke about it. This unprecedented wave of anger from the “colored population” has finally forced Academy president, Cheryl Boone Isaacs, to officially announce on January 19, of the changes that the AMPAS is planning to do in the future with the aim of ensuring diversity.
My take on the issue, well, my first response to the news was “What’s new about it?” It’s no wonder the “colored” people have received less attention in the US, regardless of their achievements in their respective fields, and the film industry is of no exception. What triggered this discourse now is the fact that no colored nominees are included for the second consecutive year. And with the recent cases of abuses on the black people of America, I believe some folks have become sensitive over this issue.
Then I thought, “Why did Mrs. Smith get so upset about it?” Well, it’s obvious she might get upset over the fact that her husband, Will Smith, who starred in the medical biopic “Concussion,” wasn’t in the nomination for “Actor in a Leading Role” category. I, for one, agree that Will should get nominated for his performance in the film, since his acting skills are truly convincing. But, the Academy had its say on it.
After watching “Concussion” earlier this week, however, I feel that the Academy’s snub of the film has got nothing to do with artistic appraisals. Rather, I've got a hunch it’s more of a “corporate influence.” Will’s character, Dr. Bennett Omalu, a Nigerian-American physician [and more], was brave enough to expose the effects of head injuries inflicted in American Football games. His findings on Chronic Traumatic Encephalopathy (CTE) have sparked anger at the corridors of the National Football League (NFL) and loyal fans were furious at him. He was literally stoned for saying “Football killed the players!” It was seen as a defying act to “crucify” America’s greatest game. Almost no one was willing to listen to him until 2009, when the NFL finally forced to acknowledge his findings.
The NFL clubs are owned by billionaires who’ve got long arms in business. And it wouldn’t be somewhat silly for one to suspect they’ve got something to do in “convincing the Academy members not to give their nods” to the film, in order to keep their interest. Even if they don’t, I suspect many die-hard fans of American football (I don’t understand why they call it “football,” when the players use their feet on the ball only on penalties) had a hand on it. So I believe, “Business takes the upper hand on Art!”


Citations: Oscars 2016 Boycott: A Timeline of the Controversy, US Weekly, January 20, 2016

Tuesday, January 26, 2016

ከማፍረስ እንጀምር!

መቼም ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ብዙ ተብሏል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የስፖርት ተከታታይ አገራችን ስሟን በክብር ከሚያስጠራት አትሌቲክስ በበለጠ ለእግር ኳስ ከፍ ያለ ፍቅር ቢኖረውም፣ በውጤታማነት ግን አርኪ የሆነ ነገር ጠብ ሳይልለት ዓመታትን ገፍቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የስፖርቱ ደረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በኢንተርናሽናል ደረጃ ከዓመት ዓመት እየወረደ ብቻ ሳይሆን እየወደቀ መሄዱ ለስፖርቱ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን አፍቃሪና ተከታታይ ላልሆነው ሕዝብ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሐቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እኛም በአገራችን እግር ኳስ ውጤት-አልባነት መናደዳችን እየቀረ መሳለቅ ከጀመርን ቆየን፡፡
ዘንድሮም ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ትናንት ማምሻውን በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ከሚገኘው የቻን ውድድር በጊዜ ተሰናብተናል፡፡ ያው የተለመደ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ከሚዲያዎች በስተቀር ማንም ምንም ሲል አልሰማሁም፡፡ ሚዲያዎቹም ቢሆኑ ስለችግሩ ብዙ ስላሉበትና አዲስ ነገር ስላልመጣ እንደቀደመው ጊዜ ብዙ ነገር አልተናገሩም፡፡ ይልቁንስ፣ ”ካለፈው የቻን ተሳትፏችን የተሻለው ነገር አንድ ጎልና አንድ ነጥብ ማግኘታችን ነው” የሚል ማጽናኛ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ አይፈረድባቸውም! ማለት የሚችሉት ይህንኑ ብቻ ስለሆነ፡፡
በሚዲያዎቹ ከተነገረው ጥቂት ነገር ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዐቢይ ነጥብ ”ከዚህ በኋላስ ምን ይደረግ?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ያዳመጥኳቸው ሁለት የኤፍ.ኤም ሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞች ስለዚህ ጥያቄ ከሰጧቸው ምላሾች ውስጥ አንደኛውና እኔም በግሌ የተስማማሁበት ”ምን መደረግ እንዳለበት ብዙ ተነግሯል፣ ከዚህ በኋላ ይህንን ደጋግሞ ማንሳት አሰልቺ ነው” የሚለውን ነበር፡፡ እውነት ነው! ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ስለዚህ ጉዳይ ስንቴ አወራን? ስንቴ ተናደድን? ስንቴ ተከራከርን? በጣም ብዙ ጊዜ! ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡
የፕሮግራሞቹ አቅራቢዎች ይህንን ቢሉም፣ ”አሰልቺ ነው” በማለት ብቻ ነገሩን አልተውትም፡፡ ግዴታቸው ነውና ከዚህ በኋላም ”ቢሆን ጥሩ ነው” ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተዋል፡፡ እኔ የወደድኩት ሐሳብ በብሥራት ኤፍ.ኤም 101.1 የ”ብሥራት ስፖርት” አዘጋጁ መንሱር አብዱልቀኒ ያቀረበውን ሐሳብ ነው፡፡ የመንሱር ሐሳብ በጥቅሉ ”ብዙውን ጊዜ በታዳጊዎች ላይ ስለመሥራትና ለውጡን ከታች ስለመጀመር ተወርቷል፣ ይህም ለሰሚው አሰልቺ ሆኗል፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ለውጡን ከላይ ስለመጀመር እናስብ” የሚል ነበር፡፡
ይህ በእውነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኖቻችንና ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል መድረኮችም ሆነ በውስጥ ውድድሮች አንገት አስደፊ ውጤት ባስመዘገቡ ቁጥር የሚሰጠው ምክንያት ”የተጫዋቾቹ የአካል ብቃት ዝቅተኛ መሆን፣ የአየሩ መክበድ፣ የዳኛ ውሳኔ፣ የመስተንግዶ ጥሩ አለመሆን፣ የአሰልጣኙ የአሰለጣጠን መንገድ፣” ወዘተ ሲባል ነው የምናየውና የምንሰማው፡፡ የስፖርቱ አመራርስ? ስፖርቱ ዓለም በደረሰበት የሥልጠናና የውድድር ደረጃ እንዲካሄድ የሚጠበቅበትን ሥራ ያልሠራው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ለምን ዝም ይባላል?
በእርግጥ በቅርቡ ሚዲያዎቻችንም ሆነ ሌሎች የስፖርቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ለውጤት መጥፋት ፌዴሬሽኑን ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ወቀሳው ጠንከር ብሎና ቁርጠኛ የመፍትሄ ሐሳቦችን አዝሎ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ወቀሳው ጠንከር ይበል ስል ግለሰብ የፌዴሬሽን አመራሮችን መውቀስ ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሥርዓቱንና አሠራሩን ”ትክክል አይደለም፣ ኋላ-ቀር ነው ” ብለን ማውገዝና እንዲቀየር መጠየቅ አለብን እያልኩ ነው፡፡
በእኔ እምነት የእግር ኳሱም ሆነ የአጠቃላዩ ስፖርት ውጤት-አልባነት መነሻ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አደረጃጀትና አሠራር አለመኖር ነው፡፡ የስፖርት ፌዴሬሽኖቻችን በሙሉ በአማተር አገልጋዮች የሚመራ ነው፡፡ እነዚህ አማተር አገልጋዮች ደግሞ አብዛኛው ጊዜያቸውን በመደበኛ ሥራቸው ላይ የሚያውሉና የስፖርቱን ውሎና አዳር በሙሉ ትኩረት የሚከታተሉ አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ለስፖርቱ ባላቸው ፍቅር ብቻ የሚሠሩ እንጂ የስፖርቱ ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው፣ በስፖርቱ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ ከተመልካችነት በዘለለ ያልተሳተፉ ስለሆኑ ስፖርቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ የሚሳናቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ዛሬ፣ ስፖርት ሳይንስ በሆነበት ዘመን አገራችንን ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር አያስችሉም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህም ተቋማዊ አደረጃጀትና ለውጥ በፍጥነት ያስፈልገናል፡፡
ምን ዓይነት ለውጥ? የአመራር ለውጥ? የአሰልጣኝ ለውጥ? የተጫዋች ለውጥ? የእነዚህ ሁሉ ለውጥ ውጤት አያመጣም፡፡ የሚፈለገው የሥርዓት (system) ለውጥ ነው፡፡ ሰዎችን በመቀያየር ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ሰዎቹ ሥራቸውን በዕውቀትና በነፃነት መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሥርዓት፣ አቅም ያላቸው ባለድርሻዎች ተለምነው ሳይሆን ለምነው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የሚያበረታታ ሥርዓት፣ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ እምነት ሊጣልበት የሚችል ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት ስፖርት በዕውቀት እንጂ በፍቅርና በወኔ ብቻ የማይመራበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የስፖርቱ አመራር የዕለት ተዕለት ሥራቸው የሆነ ባለሙያዎች በደመወዝተኝነት የሚሠሩት ሥራ መሆን አለበት፡፡ በቀላል ቋንቋ ስፖርታችን ፕሮፌሽናል አመራር ያስፈልገዋል፡፡
”ፕሮፌሽናል አመራር ያስፈልገናል” ሲባል አሁን ያለው አማተር አመራርና አሠራር መወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ አማተሪዝም ይብቃን! አማተሪዝም በአንድ ወቅድ ጠቅሞን ሊሆን ይችላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ግን አይሠራም፡፡ አማተሮች ስፖርቱን እስከመሩ ድረስ በስፖርቱ መንደር ሰላም አይሰፍንም፡፡ ምክንያቱም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በስፖርታዊ ቋንቋ መነጋገር እስካልቻሉ ድረስ ውዝግብ፣ ጭቅጭቅ፣ ጥቅም ፍለጋ፣ ሙስና፣ ወዘተ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ (ነፍሱን ይማረውና) ብዙ ጊዜ ይል እንደነበረው ”በስፖርት ቋንቋ መነጋገር የሚችሉ አመራሮች ወደስፖርቱ አምባ መምጣት አለባቸው፡፡”
ይህንን ለማድረግ ”ከምን ይጀመር?” ከተባለ የኔ መልስ ”ከማፍረስ ” የሚል ነው፡፡ ”ማፍረስ” ሲባል አሉታዊ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ አሮጌ ቤታችንን ባለበት ቦታ ላይ በአዲስ ቤት ለመተካት ካሰብን ያለን አማራጭ አሮጌውን ቤት ማፍረስ ብቻ ነው፡፡ እናም፣ ዘመናትን ያስቆጠረው፣ አሮጌው የአማተር የስፖርት ሥርዓት፣ መፍረስ አለበት፡፡ አሮጌውን አማተሪዝምን አፍርሰን፣ አዲሱን ፕሮፌሽናሊዝምን እንገንባ፡፡ ፌዴሬሽኖቻችንን እናፍርስ፣ አፍርሰንም በፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ ላይ እንገንባቸው፡፡ ያኔ፣ ጊዜው ቢረዝምም፣ ውጤታማ እንደምንሆንበት በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡ እናም ከማፍረስ እንጀምር!