በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፌ ለግል ቴሌቪዥኖች ፈቃድ ለመስጠት
የተያዘውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ አንዳንድ ሐሳቦችን መሰንዘር ጀምሬ ነበር፡፡ በዚያ ጽሑፌ የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን ሚዲያ ትናንትና ዛሬ በግርድፉ እንደመንደርደሪያ
በማንሳትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የቴሌቪዥን አገልግሎትን አስመልክቶ ለመሥራት
ያቀደውን በመጥቀስ፣ ይህን ተከትሎም ብቃትና ጥራትን የሚመለከቱና ተያያዥ ሐሳቦቼን በተከታታይ እንደማቀርብ ገልጫለሁ፡፡
ወደ ዋናው ሐሳብ ከመግባቴ በፊት ባለፈው ጽሑፍ በመንደርደሪያነት ካነሳኋቸው ነጥቦች
መካከል አንዱ የነበረውን ጉዳይ የዛሬው ጽሑፍ ዋነኛ ነጥብ በማድረግ ጥቂት ለማለት እወዳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከ1995 ዓ.ም. በፊት
የነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሁለት ብቻ እንደነበሩ፣ እነርሱም ብሔራዊው ቴሌቪዥን (የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን) እና የትምህርት ቴሌቪዥን
እንደሆኑ በክፍል አንድ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህ የጊዜው ብቸኛ ቴሌቪዥኖች መካከል ዘንድሮ 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን
ያከበረውን ኢቴቪ (የአሁኑ ኢቢሲ) አመሠራረትና ታሪክ በመጠኑ እንመለከታለን፡፡ በነገራችን ላይ፣ ይህ የኢቢሲ ”50ኛ ዓመት በዓል”
ነገር ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም እየጠየቁት ያለው ይህ ጥያቄ ”ማነው አክባሪው?” የሚል ነው፡፡ እኔ እስከምረዳው
ድረስ አሁን እየተከበረ ያለው 50 ዓመት የቴሌቪዥን አገልግሎት የተጀመረበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደግሞ
የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ዘርፎችን አጣምሮ የያዘ እንደመሆኑ፣ በአገራችን ከተጀመረ ወደ 80 ዓመት ገደማ የሆነውን የሬዲዮ ዘርፍ ”ለምን
ተወው?” የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ስለዚህ፣ እንደእኔ አስተያየት፣ መከበር የነበረበት 50ኛ ዓመት ሳይሆን 80ኛ ዓመት መሆን
ነበረበት፤ አልያም የበዓሉ መጠሪያ ”የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን አገልግሎት 50ኛ ዓመት” ቢባል የተሻለ ይሆን
ነበር፡፡
ከበዓሉ አከባበር
ጋር አብረው ሊደረጉ የሚገባቸውና ያልተደረጉ ነገሮችንም ታዝቤያለሁ፡፡ በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን ጎብኝቸዋለሁ፡፡
የተቋሙን ታሪክ ለማሳየት የተደረገው ዝግጅት በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ፎቶግራፎችን፣ የቴሌቪዥን መሣሪያዎች እና የተለያዩ የተቋሙ
ሰነዶችን ለሕዝብ ዕይታ ክፍት በማድረግ ተቋሙን ለማስተዋወቅ ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን፣ ይህ
የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ታላቅና ጠቃሚ መድረክ (milestone) እንደመሆኑ መጠን፣ የተቋሙን ታሪክ በመጽሐፍ፣ በመጽሔት፣ በድረ-ገጽ፣
… አደራጅቶ በቋሚነት ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ በተጨማሪ ከጣቢያው የቀድሞና የአሁን ጋዜጠኞች መካከል በርከት ያሉት ፎቶግራፋቸውና
ስማቸው ለዕይታ የቀረበ ቢሆንም ሳይቀርቡ የቀሩ ጋዜጠኞችም አሉ፡፡ ፎቷቸው ባይገኝ እንኳ ስማቸውን ማቅረብ ምን ይከብዳል? ይህ
አለመደረጉ በበኩሌ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ ለወደፊቱ ይታሰብበት!
የኢቴቪ ታሪክ
አመሠራረት
ቴሌቪዥን የኢትዮጵያን ምድር የረገጠውና አገሪቱም የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆነችው
ቴክኖሎጂው በመገናኛ መሣሪነት ለዓለም ከተዋወቀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ ቴሌቪዥንን በአገሪቱ ለማስተዋወቅ
የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ የመጀመሪያው ሙከራ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን የዘውድ በዓል አስመልክቶ በአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ
(ብሥራተ-ገብርኤል) አካባቢ ተዘጋጅቶ በነበረው ኤግዚቢሽን ላይ የእንግሊዙ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ያቀረበው ፕሮግራም ነበር፡፡ ቀጥሎም
በ1952/53 ዓ.ም. ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት
አጣ፡፡ የብሥራተ-ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያና የቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣንም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደረገባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭቱን የጀመረው ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. የአፍሪካ
አንድነት ድርጅት መሥራች ስብሰባን በቀጥታ በማስተላለፍ ነበር፡፡ እንደቴክኖሎጂው አዲስነት በጊዜው ቴሌቪዥን በየቤቱ የገባበት ጊዜ
ስላልነበረ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ የጉባዔውን ሂደት የተከታተለው በፊሊፕስ ኢትዮጵያ አማካይነት ከአዳራሹ ውጭ በተተከሉ ቴሌቪዥኖች
አማካኝነት ነበር፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በይፋ መርቀው የከፈቱት አጼ ኃይለሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት
ንግግር ”የቴሌቪዥን ጣቢያ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም፣ ወደፊት ድርጅቱ ተስፋፍቶ የሚሰጠው ጥቅም መላውን ሕዝባችንን
እንደሚያዳርስ ተስፋ አለን፡፡” ብለው ነበር፡፡
አደረጃጀትና የሥራ
እንቅስቃሴ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በእንግሊዙ ቶምሶን ኩባንያና በፊሊፕስ ኢትዮጵያ በቀረበ ምክረ-ሐሳብ
እና በኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበለት ብር 247‚000 በጀት፣ እንዲሁም ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆኖ ሲቋቋም፣
ሥራውን ለማለማመድ በኃላፊነት በተሾሙት እንግሊዛዊ ሚስተር ጂ. ዋትሶንና ከዘመኑ ምርጥ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ በነበሩት አቶ ሳሙኤል
ፈረንጅ ምክትል ኃላፊነት ይመራ ነበር፡፡ በጥቅምት ወር 1957 ሥርጭቱን ለመጀመር አዲስ አበባና አካባቢዋን መሸፈን የሚችል ባለ
500 ዋት ትራንስሚተር ከነሙሉ ድርጅቱ በማቋቋም ዝግጅቱን አጠናቀቀ፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው ሥርጭት በጀመረበት ወቅት በየቀኑ የሁለት ሰዓት ከአስራ አምስት
ደቂቃ ፕሮግራሞችን ያስተላልፍ የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪ በየሳምንቱ ቅዳሜ የአንድ ሰዓት የልጆች ፕሮግራምም ያቀርብ ነበር፡፡ በፕሮግራም
ይዘት በኩል በጊዜው 30 በመቶ ፕሮግራሞቹ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ሲሆኑ፣ ቀሪው 70 በመቶ ከውጭ አገር በፊልም መልክ የሚመጣ
ነበር፡፡
ዕድገት
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥርጭት ከጀመረበት ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቁርና ነጭ ሥርጭት
ለ20 ዓመታት ያህል ዝግጅቶቹን ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ በደርግ የሥልጣን ዘመን በ1976 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 10ኛውን የአብዮት
በዓልና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምሥረታን ምክንያት በማድረግ ባለቀለም ሥርጭት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜም የሥርጭት ሰዓቱ
ከሁለት ሰዓት ከአሥራ አምስት ደቂቃ ወደ አራት ሰዓታት በቀን ከፍ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ ቅዳሜና እሁድም በሥርጭት ቀናትነት ተጨምረዋል፡፡
ይህ የሥርጭት ሰዓት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ እየጨመረ የሄደ ሲሆን፣ በተለይም ”120” የተሰኘው የሰንበት ፕሮግራም ከተጀመረ በኋላ
የእሁድ ፕሮግራሙ የአየር ጊዜ ወደ 9 ሰዓታት አደገ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የፕሮግራሞች ብዛት መጨመርና የሳተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት
መስፋፋትን ተከትሎ የ24 ሰዓታት ሥርጭት በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡
በፕሮግራሞች ይዘትና ስብጥር ረገድ፣ በ1957 ዓ.ም. በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች
የተጀመረው ሥርጭት በ1983/84 ዓ.ም. የትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ ፕሮግራሞችን አካቶ መቅረብ የጀመረ ሲሆን፣ በ1990ዎቹ መገባደጃ
ላይ ደግሞ የአፋርኛና የሶማሊኛ ቋንቋ ሥርጭቶችን በማከል የቋንቋ ስብጥሩን አስፍቷል፡፡ ለ37 ዓመታት በአንድ ቻናል ብቻ አገልግሎት
ሲሰጥ የቆየው ኢቴቪ፣ ”ቲቪ አፍሪካ” ከተባለው የቴሌቪዥን ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የቲቪ አፍሪካን ፕሮግራሞች ለማስተላለፍ
በ1994 ዓ.ም. ሁለተኛ ቻናል ከፍቷል፡፡ ይህ ቻናል ቲቪ አፍሪካ በኪሳራ ምክንያት ሲዘጋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የቴሌቪዥን
ፕሮግራም ማስተላለፍ የጀመረ ሲሆን፣ ኢቲቪም የሥርጭትና የፕሮግራም አቅሙን ለማዳበር በተባባሪ ድርጅቶች በሚሠሩ ፕሮግራሞች የሚሸፈነውን
ኢቴቪ 3 በ2003 ዓ.ም. ሥራ አስጀምሯል፡፡
በሰው ኃይል በኩል፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ ሲጀምር 27 ኢትዮጵያዊያንና 5 እንግሊዛዊያን
ሠራተኞች ነበሩት ይላል ለ50ኛው ዓመት በዓል የታተመው ብሮሹር፡፡ ሌሎች የመረጃ ምንጮች ደግሞ ቁጥሩን ወደ 16 ዝቅ ያደርጉታል
(ለማንኛውም ”ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው”ና የመጀመሪያውን ቁጥር እንውሰደው)፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮ
ዘርፉን ጨምሮ 2,222 የሚደርሱ ሠራተኞች እንዳሉት ከላይ የጠቀስኩት ብሮሹር ይናገራል፡፡
እንግዲህ የኢቴቪ (የአሁኑ ኢቢሲ) ታሪክ በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ ይህንን ታሪክ
በመጠኑ መዳሰስ የፈለግሁት ኢቴቪ የአገራችን የመጀመሪያ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆኑ ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ያለውን ታሪክ ለመመልከት
መነሻ ሊሆን ይችላል በሚል እንጂ የተሟላ አለመሆኑን መግለጽ ይገባኛል፡፡ ምናልባት በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁትን የመረጃ አቅርቦት
ሐሳብ ኢቢሲ ተግባራዊ የሚያደርገው ከሆነ ሙሉ መረጃዎችን ከባለቤቱ በቀጥታ ማግኘት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ጽሑፌ አሁን በሥርጭት ላይ
የሚገኙትም ሆኑ ሥርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኙት ቴሌቪዥኖቻችን ”ምን ዓይነት ፕሮግራሞችን ማቅረብና ምን ምን ተጓዳኝ ጉዳዮችን
ማሰብ ይኖርባቸዋል?” በሚሉት ጥያቄዎች ላይ የምለው ይኖረኛል፡፡
የመረጃ ምንጮች: መነን መጽሔት፣ 9ኛ ዓመት፣ ቁጥር 2፣ ኅዳር 1957 ዓ.ም. ፣ BBC
World Service Trust. African Media Development Initiative (via Wikipedia)
፣ የኢቢሲ 50ኛ ዓመት ብሮሹር፡፡
No comments:
Post a Comment