Tuesday, April 12, 2016

የማለዳ ትዝብቴ

ዛሬ ማለዳ በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የስፖርት ዜና ላይ ያዳመጥኩት ዜና በጣም አስገርሞኛል፡፡ ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ሲጫወቱ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች አሉላ ግርማ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ተጫዋቹ ሕክምና እንዲደረግለት ከሜዳ መውጣት ነበረበት፣ ነገር ግን ለዚህ የሚያገለግለው ቃሬዛም ሆነ አምቡላንስ በስታዲየሙ አልነበረም፡፡ አምቡላንሱ በሥፍራው የተገኘው በሁለተኛው ግማሽ ላይ ነበር፡፡ አሉላም በዚህ ምክንያት ከሜዳ በቡድን ጓደኞቹ ተሸካሚነት ለመውጣት ተገደደ፡፡
እንዴት እግር ኳስን የመሰለ፣ ለጉዳት ሊዳርግ የሚችል አካላዊ ንክኪ ያለበት ጨዋታ ቢያንስ ያለቃሬዛ ይካሄዳል? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ”ጉዳዩን ተመልክቼ እርምጃ እወስዳለሁ” ብሏል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሸገር ስፖርት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ኃላፊው በዚህ ጉዳይ ከአምቡላንስ አቅራቢው ተቋም በተጨማሪ የጨዋታው ኮሚሽነርም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲገልጹ፣ የኮሚሽነሩን ማንነት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ”በሰዓቱ ስብሰባ ላይ ስለነበርን ኮሚሽነሩ ማን እንደነበሩ አላወቅንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጣም ያሳፍራል! እንዴት አንድ አወዳዳሪ አካል፣ ራሱ የመደበውን የጨዋታ ታዛቢ ማንነት ”አላውቅም” ይላል? መቼም የጨዋታ መረጃ በጽሑፍ ሳይመዘገብ አይቀርም፡፡ ”እነ እከሌ ዳኞች፣ እከሌ ኮሚሽነር” ብሎ ለሁሉም ወገን የሚያሳውቅ ይመስለኛል፡፡ እና፣ ፋይል አገላብጦ እንኳን ኮሚሽነሩ እገሌ ነው ማለት ይቸግራል? እንዲህ ዓይነቱ ቀልድ የሚያበቃው መቼ ይሆን?!

No comments:

Post a Comment