Thursday, May 12, 2016

አንዳንድ ሐሳቦች- ስለኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያ (ክፍል ፫)


ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎቼ የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያን አስመልክቶ ጥቅል የመንደርደሪያ ሐሳብ ለመስጠት እና የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት አጀማመርና ወቅታዊ ሁኔታን በመንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢቢሲ) ማሳያነት ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፌ ደግሞ አሁን ”በአገራችን በሥርጭት ላይ የሚገኙትና ለሥርጭት በመዘጋጀት ላይ ያሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከፕሮግራም ይዘት፣ ከዘውግ ስብጥር፣ እንዲሁም ከጥራት ጋር ተያይዞ ምን ማድረግ አለባቸው?” በሚለው ጉዳይ ላይ የበኩሌን ጥቂት ለማለት እሞክራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወቅታዊ የፕሮግራም ይዘት
በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ እንደጠቀስኩት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሥርጭት ላይ የሚገኙት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ተቋቁመው እየሠሩ ካሉት ሚዲያዎች መካከል፤ በመንግሥት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሶማሌ ክልሎች፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ቴሌቪዥኖች የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ በግል ዘርፍ ደግሞ መሠረቱን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ሰርቪስስ (ኢቢኤስ)፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ፕሮግራሞች ደግሞ በእንግሊዝ አገር መቀመጫውን ያደረገው ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የእነዚህን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የፕሮግራም ይዘት ስንፈትሽ፤ መንግሥታዊ/የሕዝብ ሚዲያዎች በዋነኛነት የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ባደረጉ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች እንዲሁም በተወሰኑ የመዝናኛ ዘርፎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ የግሉ ኢቢኤስ ደግሞ መዝናኛን በዋንኛነት ያተኩርበታል፡፡ ሌሎቹ ፕሮግራሞቹ ማኅበራዊ ኑሮን፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ኢኮኖሚን ለመዳሰስ ይሞክራሉ፡፡ ኤልሻዳይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በክርስትና ሃይማኖት ላይ ትኩረት አድርጎ ፕሮግራሞችን ያስተላልፋል፡፡
ወደ ይዘቶቹ ደረጃ ስንሄድ፣ በግሌ የሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉት ፕሮግራሞች የተመልካቾችን ፍላጎት በሚያሟላ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኤልሻዳይ ቴሌቪዥንን በትኩረት አቅጣጫው ምክንያት ከንጽጽሩ ውጭ አድርገን ሌሎቹን ጣቢያዎች ስንገመግም፣ በአብዛኛው ተመሳሳይነትና ተደጋጋሚነት እናይባቸዋለን፡፡ የመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያዎች፣ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከረው፣ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ ተከትለው ፕሮግራማቸውን የሚያቀርቡ በመሆናቸው በዜናና ወቅታዊ ዝግጅቶቻቸው ላይ ከቋንቋ እስከ አቀራረብ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ምናልባትም መለያ ምልክታቸውን (ሎጎ) ካላየን በስተቀር አንዱን ከሌላው ለመለየት ይከብዳል፡፡ የፕሮግራማቸው አቀራረብ”ልማታዊ ጋዜጠኝነት” በሚባለው የጋዜጠኝነት ዘርፍ እንዲመራ የተደረገ በመሆኑ፣ በአመዛኙ ”ልማት-ተኮር” በሆኑ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች የአየር ሰዓታቸውን ለመሸፈን የሚጥሩ ናቸው፡፡ የግሎቹ ኢቢኤስ እና የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኦቢሲ) ደግሞ ከቋንቋ ልዩነት በስተቀር በአብዛኛው ተመሳሳይ የሆነ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ የይዘት ድግግሞሽ በብዛት ይታይባቸዋል፡፡ ድግግሞሽ ደግሞ በአብዛኛው አሰልቺነትን አስከትሎ የሚመጣ እንደመሆኑ በእኔ የቴሌቪዥን ተመልካችነት ልምድ እንዳየሁት [በሁሉም ቻናሎች] ከጥቂት ፕሮግራሞች በስተቀር አብዛኛዎቹ አሰልቺና ለመመልከት የማይጋብዙ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንዳንድ ፕሮግራሞች (በተለይም በቅርብ ጊዜ የተጀመሩት የ”መዝናኛ” ፕሮግራሞች) በፍጹም ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ለተመልካች ክብር የማይሰጡና የአገራችንን የባሕል፣ የአስተሳሰብና የዕውቀት ደረጃ ከግምት ያላስገቡ ሆነዋል፡፡ ከዕውቀት ማነስ ይሁን፣ ወይም ተመልካቹን ከመናቅ፣ በደረጃቸው የወረዱ ፕሮግራሞችን መመልከት እየተደጋገመ ነው፡፡አንዳንዶቹ ፕሮግራሞች እንዲያውም፣ የሌሎችን አገሮች የፕሮግራም ፎርማት እንዳለ በመገልበጥ የሚቀርቡ በመሆናቸው፣ ለኢትዮጵያዊ ተመልካች የማይመጥኑ ፕሮግራሞች ከአሰልቺ አቀራረብ ጋር  በቴሌቪዥናችን ብቅ እያሉ እያታከቱን ይገኛሉ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተጨማሪ አዳዲስ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘርፉን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ አካባቢያዊ የሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት ለመስጠት ለሚፈልጉ ድርጅቶች ባቀረበው ጥሪ መሠረት ”ናሁ” እና ”ቃና” የተሰኙ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች መደበኛ ሥርጭት በቅርቡ የጀመሩ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ የሬዲዮ ሥርጭቱና በመላዋ ኢትዮጵያ 12 የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋም የታወቀው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም የቴሌቪዥን ሥርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዝርዝር ባይገለጽም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን አገልግሎት ለመጀመር ማሰቧም ተነግሯል፡፡ የእነዚህን ቻናሎች ይዘት መደበኛ ሥርጭት ሲጀምሩ የምናየው ይሆናል፡፡
ቴሌቪዥኖቻችን በምን ላይ ያተኩሩ?
በአሁኑ ወቅት ከተቀላቀሉት አዳዲስ ቻናሎች መካከል ሁለቱ (ናሁ እና ቃና) በአብዛኛው መዝናኛ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል፡፡ በውስን ደረጃ ናሁ ከመዝናኛው በተጨማሪ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ዝግጅቶችን (ቶክ ሾዎችና ሪያሊቲ ሾዎች) እያቀረበ መገኘቱ እንዳለ ሆኖ፡፡
አዳዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ ቻናሎች መዝናኛ ላይ ማተኮራቸው በመሠረቱ ብዙም ችግር የለውም፣ መዝናኛ የሕይወታችን አንድ አካል እንደመሆኑ ሽፋን ሊሰጠው ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ ለምን መዝናኛ ብቻ? ሌሎች ጉዳዮችስ? አገራችን በርካታ ውይይትና የመረጃ ልውውጥ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሏት፡፡ ፖለቲካችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ ባሕላችን፣ ታሪካችን፣ ወዘተ የሚዲያዎቻችን የትኩረት ማዕከል ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ምናልባት አሁን በአገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት አንዳንዶቹ ጉዳዮች አይነኬና ምናልባትም ”አይደፈሬ” ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ግን፣ ሚዲያዎቻችን ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ባለመዘንጋት ባሉት አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መጣር ይኖርባቸዋል፡፡
ይዘት
ይዘትን በተመለከተ፣ የቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን ”ከፈረንጅ የመጣ ሁሉ ትክክል ነው” ከሚል አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው፡፡ ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት አንዳንዶቹ ሚዲያዎች የውጭ ሚዲያዎችን ፎርማት እንዳለ ገልብጠው ለማቅረብ በሚያደርጉት ሙከራ የኢትዮጵያን ባሕል፣ ሥነ-ምግባር፣ እና የሕዝቡን የአስተሳሰብና የሞራል ደረጃ ከግምት የማያስገቡ በመሆናቸው የማይገቡ፣ ዓላማቸውና መድረሻቸው በፍጹም ግልጽ ያልሆነና ሲከፋም ግልብ የሆኑ ፕሮግራሞችን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ፣ ሚዲያዎቻችን ለራሳቸው ሕልውናም ሲሉ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በሚገባ ሊያውቁ ይገባቸዋል፡፡ ከውጭ የምንቀበለው የሚጠቅመንን ብቻ መሆኑን እና እኛም ለዓለም የምንሰጠው ብዙ ነገር እንዳለን ተረድተው ሥራቸውን ከጀመሩ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ያከብራሉ፤ አገርና ሕዝብን ሳያውቁና ሳያከብሩ ”ቴሌቪዥን እጀምራለሁ” ማለት የጨለማ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡
የዝግጅት ደረጃ
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሚዲያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተቆጣጣሪው የመንግሥት አካልም በጋራ ሊሠሩት የሚገባ አንድ ሥራ አለ፤ የሚዲያ ዝግጅቶች ደረጃ! በሌሎች አገሮች እንደተለመደው፣ በሚዲያ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በሲኒማ የሚቀርቡ ፊልሞችም በተመልካቾች የዕድሜ ደረጃ ላይ የተመሠረተ ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ በእኛም አገር ይህ ዓይነቱ የደረጃ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባዋል፡፡ አሁን አሁን በቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን የሚቀርቡ ድራማዎች፣ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ እና ማስታወቂያዎች የተመልካቾችን ዕድሜና የግንዛቤ ደረጃን፣ እንዲሁም የሥርጭት ሰዓት ምርጫን በፍጹም ከግምት የማያስገቡ ናቸው፡፡ በተለይ በዚህ ፈጣን የመረጃ ዘመን አዲሱ ትውልድ ለሚመለከታቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይዘት መጨነቅና መጠንቀቅ ካልጀመርን ከባድ ጥፋት እየፈጸምን መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ፣ የሚዲያዎቻችንን የፕሮግራም ይዘት እየገመገመ ደረጃ የሚሰጥ የሚዲያና የመዝናኛ ”ደረጃ መዳቢ” በአስቸኳይ ያስፈልገናል፡፡

ከላይ ለማንሳት የሞከርኳቸው ሐሳቦች አሁን በሥርጭት ላይ ላሉትም ሆነ ወደፊት ሥርጭት ለሚጀምሩት የቴሌቪዥን ሚዲያዎቻችን ጠቃሚ ግብዓት ይሆናሉ ያልኳቸውን ጥቂቶቹን ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ ሐሳቦች ሊነሱ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ለቴሌቪዥን ብቻ ሳሆን ለሬዲዮ ሚዲያዎቻንም የሚጠቅሙ ናቸው፣ ምክንያቱም ሁለቱም ሚዲያዎች በርካታ ተከታታይ ያላቸው በመሆናቸው ለተከታዮቻቸው ኃላፊነት ሊሰማቸው ግድ ይላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን፣ ሚዲያ ሕዝብን በማሳወቅና በማዝናናት፣ እንዲሁም የውይይት መድረክ በመሆን በርካታ ሥራ ሊሠራ የሚችል ተቋም እንደመሆኑ፣ ያለው አቅም ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ኃላፊነት አንዳለበት በማወቅ ለአገራችንና ለሕዝቧ የሚበጀውን ለመሥራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል እላለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment