Monday, September 17, 2018

ለውጥ፣ ለጸጥታ ኃይላችን!


አዲስ ዜና ሆኖ አይደለም፣ ግን መነገር ያለበት መራር እውነታ ስለሆነ ነው የማነሳው።
የትናንትናው የአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ እና ውጤቱ የጸጥታ ኃይላችን ላለፉት 27 ዓመታት እንዴት ሲደራጅና ሲገነባ እንደቆየ እንደገና ያየንበት አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አልፏል።ዛሬም የአድማ መበተኛ ዘዴያችን ጥይት ብቻ መሆኑ ያሳፍራል።
ይበልጥ የሚያሳዝነው፣ ሌላ የአድማ መበተኛ ሳናጣ ገዳይ ጥይት ለመተኮስ መቸኮላችን ነው። ለኢንጂነር ስመኘው ቀብር በወጣው ሕዝብና በፖሊስ መካከል "አልፋለሁ፣ አታልፍም" አለመግባባት የተነሳውን ግጭት ለማብረድ የተተኮሰው አስለቃሽ ጢስ አልቆ ነው ትናንትና በጥይት አምስት ሰው የተገደለው? ሰልፉ ወደቤተመንግሥት ስላመራ ብቻ የቤተመንግሥቱ ጠባቂ ወታደሮች ክላሻቸውን ወድረው ከሰልፈኛው ጋር መፋጠጥ ነበረባቸው? ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ ተቀባይነት ባለው የአድማ ብተና መንገድ ሁኔታውን ማብረድ ከባድ ነበር?
አልነበረም! ችግሩ፣ የጸጥታ ኃይሉ የሠለጠነው ለመደብደብና ለመግደል መሆኑ ነው።ባይሆንማ ኖሮ፣"ጥቃት ይቁም" ብለው አደባባይ የወጡ ዜጎች ላይ ጥይት ያለቦታው አይተኮስም ነበር። እንደሰማነው ከሆነ፣ ፌዴራል ፖሊስ የቅዳሜና እሁዱ ጥቃት እንደሚፈጸም መረጃ ደርሶት ነበር። በደረሰው መረጃ መሠረት ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዱ መጠየቅም፣ መቀጣትም የሚገባው እርሱ ነበር።
ምናልባት ይህንን ማለት ሰብዓዊ ላይሆን ይችላል፤ ግን መባሉ ግድ ነው። ትናንት አዲስ አበባ ላይ አምስት ወገኖቻችንን የገደሉት ጥይቶች የሚገቡት ለቡራዩዎቹ አረመኔዎች ነበር።ንጹሃንን ያልታደገ፣ ግን ንጹሃንን የሚገድል የጸጥታ ኃይል ይዘን ይህንን ለውጥ ዕውን ማድረግ መቻላችን አጠራጣሪ ነው።
እናም፣ ለውጥ ለጸጥታ ኃይላችንም በጣም ያስፈልገዋል!


No comments:

Post a Comment