Friday, September 7, 2018

ልብ እንበል!

የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ሞት አስመልክቶ ሲደረግ የነበረው ምርመራ ውጤት ሲገለጽ፣ ብዙዎች "ራሳቸውን አጥፍተዋል" የሚለው መደምደሚያ አልተዋጠላቸውም። በዚህም የተነሳ በርካታ ዜጎች በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሀዘንና ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው።
መግለጫውን ስላልተከታተልኩት የተሟላ መረጃ ላይኖረኝ ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የኢንጂነሩ ራሳቸውን ማጥፋት አሁንም ሙሉ በሙሉ ካልተዋጠላቸው ሰዎች መሃል አንዱ ነኝ።ስለሆነም የብዙሃኑን ስሜት እረዳለሁ።
ነገር ግን፣በዚህ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ልብ ሊሏቸው ይገባሉ የምላቸውን ነጥቦች በአክብሮት ማስታወስ እወዳለሁ።
1. አገሪቱ ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ለዘመናት በፖለቲካዊ መጠላለፍ፣ በተንኮል፣ በሴራ፣ በሽኩቻ ውስጥ የኖረችና ዜጎቿም በዚህ የተካኑ ናቸው።ከዚህ አዙሪት በአራትና አምስት ወራት እንወጣለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ነውና ይህንን ብናስተውል፣
2. በዓለማችን በርካታ ምሥጢራዊ ግድያዎች ተፈጽመዋል። ምሥጢራቸውን ለመፍታት እጅግ አዳጋችና ከመጀመሪያው ግድያ በላይ ተጨማሪ መስዕዋትነት ያስከፈሉትንም አይተናል። የፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ አንዱ ምሳሌ ነው። ከፕሬዚዳንቱ ግድያ ማግስት ጀምሮ በግድያው ሰበብ ሠላሳ ሁለት ያህል ሰዎች ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገድለዋል።ግድያውን የመረመረው "The Warren Commission" ያቀረበው ሪፖርት ከ55 ዓመታት በኅላም አሳማኝ አልሆነም። ይህንን ምሳሌ ያነሳሁት ለንጽጽር አይደለም፣ ይልቁን የጉዳዩን ከባድነት ለማሳየት ያግዛል ከሚል ሀሳብ እንጂ። የሕዳሴው ግድብ ተራ ግድብ አይደለም፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ እና ሌሎችም ፍላጎቶች ያሉበት ፕሮጀክት ነው።ስለዚህ ሁኔታውን በዚህም ጎን ብናየው።
3. የኢንጂነሩ ሞት ጉዳይ ምላጩን በሳበው ሰው ላይ (እርሳቸውም ይሁኑ ሌላ ሰው) እንደማይቆም ሁላችንም እናውቃለን። ምርመራው ከዚህ በላይ ቢሄድም የጉዞው አቅጣጫ ወዴት ሊሆን እንደሚችልም መገመት አያቅተንም። ይህንን ውስብስብ ጉዳይ ለመፍታት የምንወስደው ጊዜ እንደኬኔዲ ግድያ ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍለን መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አገራችን በርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮች ያሉባት እንደመሆኗ በቀጣይ መሰል መከራና ሀዘን እንዳናስተናግድ የአሁኑን ለውጥ በጥንቃቄ መያዝ ይገባናል።
በርካታ ኢትዮጵያዊያን በምርመራው ውጤት ያልረካነው ሀጢያቱን የሆነ አካል እንዲሸከም ካለን ፍላጎት እንደሆነ እረዳለሁ፣ ግን ትዕግሥትና ማስተዋል በጣም ያስፈልገናል። ኢንጂነር ስመኘው የዚህ ለውጥ ተግዳሮቶች ካሳጡን ሰለባዎቻችን አንዱ ናቸው። ፈጣሪ ይጠብቀን እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ ሌሎቻችንም ሰለባ ልንሆን እንችላለን። ማሽነፍ የምንችለው የለውጡን ጠላቶች ባለን አቅምና ችሎታ ሁሉ መታገል ስንችል ብቻ ነው። አሁን የኢንጂነሩን ቤተሰቦች በምንችለው ሁሉ እያገዝን፣ ለዚህ መጥፎ ዕጣ የዳረገን ብልሹ አሠራር ዳግም ዋጋ እንዳያስከፍለን የበኩላችንን ማድረግ ነው። እውነታውን በተመለከተ ግን፣ ኢንጂነር ስመኘው በሞቱበት ዕለት በፌስቡክ የፃፍኩትን እደግመዋለሁ።
ጊዜ እውነቱን ያወጣዋል!

No comments:

Post a Comment