ከዛሬ አራት ዓመት ከአሥር ወር
በፊት “ኧረ ጎበዝ ምን ነካን?!” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ ጽፌ ነበር (http://asnakesinesibhat.blogspot.com/2013/11/)፡፡
የጽሑፉ ሐሳብ በወቅቱ ቴዲ አፍሮን አስመልክቶ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ይሰነዘሩ የነበሩ ዘለፋዎችና መሠረተ-ቢስ ትችቶችን መቃወምና
መልስ መስጠት፣ እንዲሁም መምከር ነበር፡፡ ዛሬስ? የተለወጠ ነገር አለ?
እንደእኔ ዕይታ ከሆነ፣ የተለወጠ
ነገር የለም፡፡ ካለም የባሰበት እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ለሁሉም አንደበት ስለሰጠና ማንም የመሰለውን መጻፍ
ስለሚችል፣ መልካም ሐሳብ ከሚጽፈው ባልተናነሰ ክፉና ጠማማ ሐሳብ የሚቸከችከውም ቁጥሩ የጨመረ ይመስለኛል፡፡
እውነት ለመናገር፣ የአንዳንዶች
ድድብና ከማናደድም አልፎ ያስቃል፡፡ ሰው መልካም ነገር ሲያደርግ ማመስገኑ ቢቀር ያለምንም ምክንያት መሳደብና መዝለፍ “አዋቂ”
ከሚባለው ሰው የማይጠበቅ፣ ሕፃንነትም ያልሆነ፣ ደመ-ነፍሳዊ የሆኑት እንስሳት እንኳን የማያደርጉት ስም-አልባ ባሕርይ ስለሆነ፣
በግርምት የሚያስቅም ነው፡፡
ይህንን ሁሉ እንድል ያደረገኝ
ከቴዲ አፍሮ የበጎ አድራጎት ሥራ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ አንዳንድ ሰዎች ያሠፈሯቸው አስተያየቶች የፈጠሩብኝ ሀዘንና
ቅሬታ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ በትናንትናው ዕለት ቴዲ አፍሮ ከቡራዩና አካባቢዋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የአንድ ሚሊየን ብር እርዳታ
ሰጠ፣ ይህንን ተከትሎም በማኅበራዊ ሚዲያው የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጡ፡፡ አብዛኛዎቹ አስተያየቶች የአድናቆትና የምስጋና ሲሆኑ፣
የተወሰኑት ደግሞ ትችት፣ ሽሙጥ እና አለፍ ሲልም ዘለፋን ያዘሉ ነበሩ፡፡
እስቲ አሁን፣ ሰው ካለው ላይ
ቀንሶ ለተጎዳ ወገኑ መቋቋሚያ ቢሰጥ ነውሩ ምንድን ነው? የአንዳንዶቹ ትችት “ለምን ሰጠ?” ዓይነት ተራ ምቀኝነት ይመስላል፡፡
የሌሎቹ ከሁነቱ ጋር ጨርሶ የማይገናኝ ሀሳብ ይዘው አራምባና ቆቦ ይረግጣሉ፡፡ ያሳፍራል!
ላለፉት አሥርት ዓመታት ቴዲ አፍሮ
በሙያዊ ሥራውና በግለሰባዊ ማንነቱ፣ እንዲሁም በሚያደርጋቸው ተግባራት ምስጋናንም ሆነ ትችትን ሲያስተናግድ ኖሯል፡፡ መመስገኑ መልካም
ነው፣ መተቸቱም በመልካም ከሆነ ክፋት የለውም፡፡ የሚያሳዝነው ግን አብዛኛው ትችትና ወቀሳ ከክፉ አዕምሮ የሚመነጭ ማሰናከያ መሆኑ
ነው፡፡
ሦስት መስመር የቀበሌ ማመልከቻ
አስተካክሎ መጻፍ የማይችለው ሁሉ የበሰለ
ሀሳብን አጣፍጦ በበሰለ ግጥምና በውብ ዜማ የሚያቀርበውን ባለሙያ “መሃይም” ብሎ ይሳደባል፣ “አዝማሪ” ማለት “አመስጋኝ” ማለት
መሆኑን የማያውቅ ተቺ ሙያውን መስደቢያ ሊያደርግ ይሞክራል፣ ከሚኖርበት ሠፈር አልፎ የማይታወቀው ሁሉ በሙያው ራሱንና አገሩን ያስጠራውን
ሰው ስም-አልባ ሊያደርግ ይጥራል፣ ቴዲ በሙዚቃው ውስጥ የተወሰኑ ብሔሮችን ስም ከጠራ “እከሌ የተባለውን ብሔር ያልጠራው ስለሚጠላው
ነው” የሚል የሴራ ንድፈ-ሐሳብ ይዞ ዘረኛ ሊያደርገው ይከጅላል፣ በሙያው
ካገኘው ሀብት ለአገርና ለወገን ድጋፍ ቢያደርግ “ዘርፎ ያመጣው ነው” ከማለት የማይመለስ ምቀኛ ምላሱን ይዘረጋል፣ ሌላው ቢቀር
“እነእገሌ ሲቸገሩ ለምን አልረዳቸውም” እያለ በገንዘቡ ሊያዝ የሚቃጣው ከንቱም አለ፣…፡፡
ሌላም ወገን አለ፤ በ”አድናቂነት” ሽፋን ቀና ትችትን የሚደፈጥጥ፡፡ የቴዲን
ሙዚቃዊ ሥራዎች በሙያዊ ዓይን በመቃኘት “እዚህ ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር አለበት፣ እዚያ ላይ በዚህ ቢቀይረው” የሚል ቀና ሂስና
አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎችን “ቴዲን የነካ..” በሚል አጉል አድናቂነት አፈር ድሜ ለማብላት ታጥቆ የሚነሳ፡፡
ሁለቱም ወገን አይጠቅምም፡፡ ጽንፍ ይዞ በመውደድ ወይም በመጥላት ላይ
ብቻ የሚንጠለጠል ስሜት ይገድላል እንጂ አያለማም፡፡ በተለይ ቴዲ አፍሮ መክሊቱን አውቆ በሚሠራቸው መልካም የሙያና የበጎ አድራጎት
ሥራዎቹ የሚናደዱና ለስድብ የሚቸኩሉ ሰዎች ጤንነታቸው ያጠራጥራል፡፡ ቴዲን ለማሳያነት አነሳሁ እንጂ፣ በሙያቸው፣ በገንዘባቸው፣
በሀሳባቸውና በሌላም ነገራቸው ለኢትዮጵያ መልካም የሚሠሩ ዜጎችን ፌስቡክ ላይ ተጎልተው ለማዋረድ የሚተጉ ሰነፎችን ሁሉ ይመለከታል፡፡
በርካታ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ፣ የአሁኑን የአገራችንን ለውጥ “እንደግፋለን” የሚሉ መሆናቸው ሌላው አስቂኝ ነገር ነው፡፡
ፍቅር፣ ይቅርታ፣ አንድነት እና መደመር ካለቅንነት ዕውን አይሆኑም፣ ካለሚዛናዊነት አይሳኩም፡፡ እነዚህን ሳይዙ፣ የጠሉትን በጸያፍ
ስድብ ጭምር እያዋረዱ “መደመር” የለም፡፡ ስድብ አረም ይሆናል እንጂ አያርምም!
No comments:
Post a Comment