ማክስ
ሉካዶ የታወቀ አሜሪካዊ ጸሐፊ፣ ሰባኪ እና ተናጋሪ ነው፡፡ ከጻፋቸው በርካታ መጻሕፍት መካከል “The Woodcutter’s Wisdom & Other
Favorite Stories” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም. የታተመው መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡
በዚህ
መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው እና የመጽሐፉ መጠሪያ የሆነው “The Woodcutter’s Wisdom” የሚለው አጭር ታሪክ ለአሁኑ የአገራችን
ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ እና ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ምላሽ ጥሩ ምክር የሚሰጥ ይመስለኛል (ይህ አጭር ታሪክ “ዛፍ ቆራጩ” በሚል
ርዕስ በአማርኛ ተተርጉሞ ታትሟል፣ በሸገር ኤፍ ኤም የ”ሸገር ሸልፍ” ፕሮግራም ላይም አንዱዓለም ተስፋዬ አቅርቦት ነበር)፡፡
ታሪኩ
በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡
በአንዲት
አነስተኛ መንደር የሚኖር አንድ ሽማግሌ ዛፍ ቆራጭ ነበር፡፡ ይህ ሽማግሌ ደሃ ቢሆንም በጣም የሚያምር ፈረስ ስለነበረው በርካታ
ሰዎች (የአገሩን ንጉሥ ጨምሮ) ፈረሱን እንዲሸጥላቸው ከፍ ያለ ገንዘብ ይዘው ደጅ ይጠኑት ነበር፡፡ የሽማግሌው ምላሽ ግን “ይህ
ፈረስ ለእኔ ፈረስ አይደለም፣ ሰው ነው፣ ጓደኛዬ ነው፡፡ ጓደኛ እንዴት ይሸጣል?” የሚል ነበር፡፡
እንድ
ቀን ጠዋት ላይ ሽማግሌው ጋጣውን ሲያይ ባዶ ነው፣ ፈረሱ የለም! ይህንን የሰሙ የመንደሯ ሰዎች ተሰብስበው ወደሽማግሌው ቤት መጡና
“አንተ ሞኝ ሽማግሌ! ፈረስህ ሊሠረቅ እንደሚችል ነግረንህ ነበር፡፡ ያኔ ሸጠኸው ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ተንደላቀህ ትኖር ነበር፡፡ ዕድለ-ቢስ
ነህ፣ ተረግመሃል” ሲሉ ዘበቱበት፡፡
ሽማግሌው
ረጋ ብሎ “እስቲ ቸኩላችሁ አትናገሩ፣ ‘ፈረሱ በጋጣው ውስጥ የለም’ ብቻ በሉ፣ ተረግሜ ይሁን አይሁን በምን አውቃለሁ? እናንተስ
እንዴት ታውቃላችሁ?” አላቸው፡፡ ሰዎቹ አልተቀበሉትም፣ “ልታሞኘን
አትችልም” ብለውት ሄዱ፡፡
ከአሥራ
አምስት ቀናት በኋላ ፈረሱ ተመለሰ፡፡ አልተሠረቀም፣ ወደ ጫካው ነበር የሄደው፡፡ ሲመለስ ግን ብቻውን አልተመለሰም፣ ደርዘን ያህል
የዱር ፈረሶች አብረውት ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የመንደሩ ሰዎች እንደገና ተሰብስበው ወደ ሽማግሌው ዛፍ ቆራጭ መጡና “አንተ ልክ ነበርክ፣
እኛ ነን የተሳሳትነው፡፡ እርግማን ነው ያልነው ለካ ምርቃት ነበር፡፡ እባክህን ይቅር በለን” አሉት፡፡
ሽማግሌው
ግን እንዲህ አላቸው፣ “አሁንም ርቃችሁ እየሄዳችሁ ነው፡፡ ‘ፈረሱ ተመለሰ፣ ደርዘን የሚሆኑ ፈረሶችም አብረውት መጥተዋል’ ብቻ
በሉ፡፡ ይህ ምርቃት ይሁን እርግማን እንዴት ልታውቁ ይቻላችኋል? የመጽሐፉን አንድ ገጽ ብቻ አንብባችሁ ስለሙሉው መጽሐፍ እንዴት መፍረድ ትችላላችሁ?”
“ሽማግሌው ልክ ሊሆን ይችላል”
አሉ ሰዎቹ እርስ በርሳቸው፡፡ ውስጣቸው ግን እነርሱ ትክክል እንደሆኑ ይነግራቸዋል፡፡ ከዚያም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
ሽማግሌው ብቸኛ ወንድ ልጅ ነበረው፡፡
ይኸው ልጁ የዱር ፈረሶቹን መግራት ጀመረ፡፡ አንድ ቀን አንደኛውን ፈረስ እየገራው እያለ ፈረሱ ይጥለውና ሁለቱም እግሮቹ ይሰበራሉ፡፡
የመንደሩ ሰዎች የደረሰውን አደጋ ሰምተው ሊጠይቁትና አባትየውን ሊያጽናኑት ወደቤቱ መጡ፡፡
“አንተ ልክ ነበርክ፡፡ በእነዚህ
የተረገሙ ፈረሶች ምክንያት ይኸው ልጅህ እግሮቹ ተሰበሩ፡፡ ከእንግዲህ ማን ይረዳሃል? በጣም ተጎዳህ” አሉት ጎረቤቶቹ ልጁን ከጠየቁ
በኋላ፡፡
ሽማግሌው ተበሳጨ፡፡ “እናንተ ሰዎች!
በፍርድ ተለክፋችኋል እንዴ? ርቃችሁ አትሂዱ፡፡ ‘ልጁ እግሮቹ ተሰበሩ’ ብቻ በሉ፡፡ ይህ እርግማን ይሁን ምርቃት ማን ያውቃል?
የምናውቀው ጫፉን ብቻ ነው፣ ሙሉውን ታሪክ አናውቅም” አላቸው፡፡
ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ
አገሪቱ ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት ውስጥ ገባች፡፡ የመንደሯ ወጣቶች በሙሉ ለዘመቻ ሲጠሩ፣ እግሮቹ የተሰበሩት የሽማግሌው ልጅ
ብቻ ቀረ፡፡ ልጆቻቸው የዘመቱባቸው የመንደሯ ሰዎች እያለቀሱ ወደሽማግሌው ዛፍ ቆራጭ ዘንድ መጡና “አንተ አሁንም ልክ ነህ፡፡ በልጅህ
ላይ የደረሰው አደጋ በረከት ነው፡፡ ከዘመቻው ቀርቶ ካንተ ጋር ነው ያለው፡፡ እኛ ግን ልጆቻችንን መልሰን እናያቸው እንደሆነ አናውቅም”
አሉት፡፡
“ከእናንተ ጋር መነጋገር አስቸጋሪ
ነው” አላቸው ሽማግሌው፡፡ “አዎ፣ የእናንተ ልጆች ወደጦርነቱ ሄደዋል፣ የእኔው ግን አልሄደም፡፡ ይህ በረከት ይሁን እርግማን ማን
ማወቅ ይችላል? ጫፍ ብቻ ይዛችሁ ስለምን ትፈርዳላችሁ?” አላቸው አስከትሎ፡፡
የእኛ የኢትዮጵያዊያን ነገር እንደዚህ ነው፡፡
የእኛ የኢትዮጵያዊያን ነገር እንደዚህ ነው፡፡
ለማመስገን ቸኩለን፣ ለመተቸት ቸኩለን፣
ለውዳሴ ቸኩለን፣ ለስድብ ቸኩለን፣ ለምርቃት ቸኩለን፣ ለእርግማን ቸኩለን፣… ለሁሉ ነገር ቸኩለን እንዴት እንለወጣለን? በግማሽ
ሰምተን/አንብበን በሙሉ እየፈረድን እንዴት እንታደሳለን? እንደሽማግሌው
ያለ አስተዋይ ሰው የተናገረው ነገር እውነት ሲሆን “አንተ ልክ ነበርክ፣ እኛ ነበርን የተሳሳትነው” እያልን ነገር በመደጋገም፣
ነገ ደግሞ ተመልሰን ያንኑ እያደረግን ወደምንመኘው ብሩህ ነገ እንዴት መድረስ እንችላለን?
ለፍርድ አንቸኩል!