ከዓመታት በፊት የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ (ዶይቸ ቬለ) የአማርኛ አገልግሎት ጋዜጠኛ የነበረው አቶ ጌታቸው ደስታ፣ በአንድ
ቃለ-መጠይቅ ላይ ስለዜና አሠራራቸው ተጠይቆ ሲመልስ፣ “የዓለም ዜናዎችን ስንሠራ የተለያዩ አገራት ሰዎችን ስም መጥቀስ ስላለብን፣
በስም አጠራር ላይ ስህተት ላለመሥራት በጣም እንጠነቀቃለን፤ ለምሳሌ የቻይና ስም በዜናችን ላይ ካለ፣ የእኛ ቢሮ ካለበት ፎቅ በላይ
ወዳለው የማንዳሪን ቋንቋ አገልግሎት ቢሮ ሄደን ስሙን እስከነአጠራሩ ጠይቀን መጥተን ተለማምደን ነው የምናነበው፡፡ እነሱም የኢትዮጵያ
ሰው ስም በዜናቸው ውስጥ ካለ ወርደው መጥተው፣ ጠይቀውና አጥንተው ያነባሉ፡፡” ብሎ ነበር፡፡
አብዛኛዎቹ የአገራችን ጋዜጠኞች (ሁሉም ማለት ያስደፍራል)፣ በሚሠሯቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች የሚጠቀሟቸውን ቃላት፣ ስያሜዎች
እና ስሞችን በትክክለኛው መንገድ ለመጥራት ሲቸገሩ አያለሁ፣ እሰማለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችና ተቋማትን
ስምም በአግባቡ ሳይጠሩ ሲቀሩ ያጋጥመኛል፡፡ ችግሩ ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ በደንብ አለመዘጋጀት ነው፡፡ እናም ለዚህ ትኩረት ቢሰጡ፣
በተለይ በዚህ የኢንተርኔት ዘመን፣ ብዙ የመማሪያ አማራጮች ስላሉ፣ እነርሱን ቢጠቀሙ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
ለአሁኑ ግን፣ አንድ ሁለት ነጥቦችን እንዲያስተካክሉ ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
ለአሁኑ ግን፣ አንድ ሁለት ነጥቦችን እንዲያስተካክሉ ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
·
በአንድ ወቅት፣ ስለአንድ የዘረፋ ወንጀል የሚዘግብ ዜና በሬዲዮ
ሲነበብ ሰምቼ ነበር፡፡ በዜናው ውስጥ፣ የዝርፊያውን ፈጻሚዎች ለመለየት በደህንነት ካሜራ (CCTV) የተቀረጸውን ምስል ፖሊሶች
እየመረመሩ እንደሆነ የሚገልጽ ዓረፍተ-ነገር ነበረበት፡፡ ታዲያ፣ ጋዜጠኛው “CCTV” የሚለውን ምህፃረ-ቃል የተረጎመመበት መንገድ
አስቂኝ ነበር፣ እሱ የተረጎመው “የቻይና ማዕከላዊ ቴሌቪዥን (China Central TeleVision) በሚለው የቻይና ብሔራዊ
ቴሌቪዥን ስም ነው፡፡ በዜናው ዐውድ ውስጥ ግን “CCTV” ማለት “Closed Circuit TeleVision” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ
ጋዜጠኞች፣ ምህፃረ-ቃል ሲገጥማችሁ በደንብ አጣርታችሁ ፍቱ፣ አለበለዚያ ባትተነትኑት ይመረጣል፡፡
·
ብዙ ጊዜ ከኢንተርኔት ገጾች የሚገኙ መረጃዎችን ስትጠቅሱ
“እገሌ የተባለው ድረ-ገጽ” ትላላችሁ፡፡ “ድረ-ገጽ” የእንግሊዝኛውን “website” ለመተካት ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፣ ትርጉሙ
ግን ትክክል አይደለም፡፡ “ድረ ገጽ” በእንግሊዝኛ “webpage” ማለት ሲሆን፣ ይህም የአንድ ዌብሳይት አንድ ገጽ ብቻ ነው፡፡
“Website” ማለት በርካታ ገጾች (webpages) እርስ በርስ ተያይዘው (linked ሆነው) የሚገኙበት የገጾች ስብስብ ነው፡፡
ምናልባት አንድ ሰሞን መጥቶ የነበረው “ ድር-አምባ” የሚለው ስያሜ የተሻለ ቅርበት ያለው ቢሆንም፣ ለአብዛኛው ሰው የሚከብድ ስለሚሆን
“ዌብሳይት” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል እንዳለ ብትጠቀሙበት የተሻለ ነው እላለሁ፡፡
ሌሎች ማስተካከያዎችን በቀጣይ አቀርባለሁ፡፡
ሌሎች ማስተካከያዎችን በቀጣይ አቀርባለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment