Sunday, August 30, 2015

ማሳሰቢያ፤ ለማስታወቂያ ሠሪዎች

በዚህ ሰሞን በሬዲዮና በቴሌቪዥን እየቀረበ ያለ አንድ ማስታወቂያ አለ፡፡የማስታወቂያው ባለቤት ብሔራዊ ሎተሪ ሲሆን፣ ጳጉሜን 6 ቀን የሚወጣውን ”እንቁጣጣሽ ሎተሪ”ን ለማስተዋወቅ የተሠራ ነው፡፡ በማስታወቂያው ላይ ባልና ሚስት በእንቁጣጣሽ ዕለት የአገር ባሕል ልብሳቸውን ለብሰው ድፎ ዳቦ ቆርሰው ለመብላት እየተዘጋጁ ሳለ ”አበባየሆሽ” የሚጨፍሩ ልጃገረዶች ወደቤታቸው መጥተው፡
”ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን፤
ስድስት ሚሊየን ይዘን…፡፡”
እያሉ ሲያዜሙና ጥንዶቹም ድፎ ዳቦና ለሎተሪ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጥተው ሲሸኟቸው ያሳያል፡፡
የማስታወቂያው ዓላማ ለአዲስ ዓመት መግቢያና መቀበያ የተዘጋጀውን ሎተሪ ማስተዋወቅ እንደመሆኑ በዓል በዓል የሚሸት ትዕይንት መያዙ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ነገር ግን የማስታወቂያው አዘጋጆች አንድ ትልቅ ነገር ረስተዋል፣ የጊዜ ቅደም-ተከተልን፡፡ ልብ በሉ! የሎተሪው ዕጣ የሚወጣው ጳጉሜን 6፣ የበዓል መስተንግዶውና አበባየሆሹ የሚደረገው ከዕጣው መውጫ (የእንቁጣጣሽ ዋዜማ) እና ከበዓሉ ቀናት በፊት፡፡
ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው አበባየሆሽ በነሐሴ የሆነው? በየትም አገር የበዓል አከባበር የበዓል ድግስ በዋዜማውም ሆነ አስቀድሞ ባለ ቀን አይበላም፣ አይጠጣም፡፡ የግድ ሎተሪውን ከበዓሉ ጋር ለማገጣጠም ሲባል ብቻ ነገሮችን ያለጊዜው ማምጣት አግባብ አይደለም፡፡ የዚህ ማስታወቂያ አዘጋጆች ጊዜ ወስደው ቢያስቡበት ኖሮ እንቁጣጣሽ ሎተሪን ከእንቁጣጣሽ ጋር የሚያያይዙ ብዙ ትዕይንቶችን መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ ከዓመት በዓል ሸመታ ጋር፣ ከበዓል ስጦታ ጋር፣ ከዋዜማ ምሽት የእንኳን አደረሳችሁና የመልካም ምኞት ልውውጥ ጋር፣ ወዘተ ማገናኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የይድረስ ይድረስ ሥራ ሆነና የማይመስል ማስታወቂያ ተሠራ፣ ብሔራዊ ሎተሪም ያለበቂ ግምገማ ”ይሁን” ብሎ አቀረበልን፡፡
ማስታወቂያ ግነትን እንጂ ውሸትን አይፈልግም፡፡ ከእውነታ ጋር የተጋጨ ማስታወቂያ ውሸት እንጂ ሌላ ምንም ስም የለውም፡፡ የማስታወቂያ አዘጋጆች ገንዘብን ብቻ እያያችሁ ያለዕውቀትና ያለጥንቃቄ የተሠራን እውነት ያልሆነ ድራማ ”ማስታወቂያ ” እያላችሁ እባካችሁ አትቀልዱብን፡፡ ባለማስታወቂያዎችም በግዴለሽነት የተሠራላችሁን ማስታወቂያ ሳትገመግሙ እያሳለፋችሁ ሥርዓት አታፍርሱ፡፡ ሚዲያዎችም ብትሆኑ ገና ለገና ”ሳንሱር ቀርቷል” ብላችሁ የመጣላችሁን ማስታወቂያ ሁሉ ሳትፈትሹ አትልቀቁ፡፡ የሚታዘብ ሕዝብ፣ የሚያድግና የሚማር ትውልድ አለና!

Wednesday, August 12, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፫

በክፍል ሁለት ጽሑፌ ቴሌቪዥንን አብዝቶና ያለምርጫ መመልከት በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ አስመልክቶ ሳይንሳዊ ጥናቶች የደረሱበትን ድምዳሜ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክሬ ነበር፡፡ ጥናቱ ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት የሆናቸው ሕጻናት ከቴሌቪዥን ጋር ባላቸው ቆይታ ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች እንደሚደርሱባቸው ያመለከተ ሲሆን አብዛኞቹ ተጽዕኖዎች አሉታዊ መሆናቸውን ከጥናቱ ውጤት ለማየት ተችሏል፡፡
ይህ ጥናትም ሆነ ሌሎች ጥናቶች በርከት ያሉ ጎጂ ተጽዕኖዎችን የዘረዘሩ ቢሆንም፣  ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚቀርቡት ጉዳቶች ባለፈው ጽሑፍ ላይ ተጠቃለው የቀረቡት በመሆናቸው በዚሁ እናቁመውና በዚህኛው ጽሑፍ ለልጆቻችን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ የሚጠቅሙ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንቃኛለን፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው?
ሲንዲ ስሚዝ የተለያዩ ባለሙያዎችና ተቋማት ወላጆች የልጆቻቸውን ጤናማ የቴሌቪዥን ዕይታ ለማረጋገጥ ያግዟቸዋል በማለት ካስቀመጧቸው የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አቅርበዋቸዋል፡፡
1.    የቴሌቪዥን መመልከቻ ሰዓትን መወሰን፡- ሕጻናት እንደ ዕድሜያቸው የተለያየ የቴሌቪዥን መመልከቻ የሰዓት ገደብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ድሜ ላይ ያሉ ልጆች ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት አይገባቸውም፡፡ ስለዚህም፡-
 
ሀ. ከ2 ዓመት በታች፡- የአሜሪካ የሕጻናት ሕክምና ማኅበር (American Association of Pediatrics) እና በርካታ ኤክስፐርቶች ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በጭራሽ ቴሌቪዥን መመልከት አይኖርባቸውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጨቅላ ሕጻናት አዕምሮ በፈጣን ሁኔታ የሚለዋወጡ ምስሎችና ንግግሮችን ለማስተናገድ በሚያስችል ደረጃ የተዋቀረ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ የዕድሜ ክልል ተብለው የሚዘጋጁ ዲቪዲዎች ቢኖሩም እንኳ አንድ ሕጻን የግንኙነትና የተግባቦት ክህሎቱን ሊያዳብር የሚችለው ከሌሎች ጋር አብሮ በመሆኑ ብቻ ነው እንጂ በዲቪዲው ዕይታ ምክንያት አይደለም ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡
ለ. ከ2 እስከ 3 ዓመት፡- በብሪታኒያ የታወቁት የንግግርና የቋንቋ ቴራፒስት ዶ/ር ሳሊ ዋርድ በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናት የቴሌቪዥን መመልከቻ ጊዜ በቀን ለግማሽ ሰዓት ብቻ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ሐ. ከ3 እስከ 5 ዓመት፡- እንደባለሙያዎቹ ለዚህ የዕድሜ ክልል በቀን ለአንድ ሰዓት ብቻ ቴሌቪዥን መመልከት በቂ ነው፡፡

2.   ቴሌቪዥንን በማይታይበት ጊዜ ማጥፋት፡- በቤታችሁ ውስጥ ቴሌቪዥን ተከፍቶ የሚመለከተው ሰው ከሌለ አጥፉት፡፡ ከቴሌቪዥኑ የሚወጣው ድምጽ ትኩረትን የሚሠርቅ ስለሆነ ልጆቻችሁ በሌሎች ጠቃሚ ነገሮች (ለምሳሌ የወላጆች ድምጽ) ላይ እንዳያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከሰዎች ጋር የግንኙነት መዘግየት ችግር ላለባቸው ልጆች ይህ ጠቃሚ መፍትሄ ነው ይላሉ ባለሙያዋ፡፡

3.   ተስማሚ ፕሮግራሞችን መምረጥ፡- ልጆቻችሁ የሚወዷቸውን፣ ነገር ግን ለዕድሜና የዕድገት ደረጃቸው የሚመጥኑና የአዋቂ ይዘት(adult theme) የሌላቸውን ፕሮግራሞች እንዲመለከቱ ፍቀዱላቸው፡፡  በተለይ ልጆቻቸሁ በወደፊት ሕይወታቸው ውስጥ ከሚገጥሟቸው ተሞክሮዎች ጋር የተገናኙ ፕሮግራሞች ተመራጭ ናቸው፡፡

4.   ፕሮግራሞችን አብሮ መመልከትና መወያየት፡- በተቻላችሁ መጠን ከልጆቻችሁ ጋር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመመልከት ሞክሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ በፕሮግራሙ እየተደረገ ስላለው ነገር አብዝታችሁ ከልጆቻችሁ ጋር ተወያዩ፡፡ ሁልጊዜ አብራችሁ ለመመልከት ካልቻላችሁ የፕሮግራሙን ተስማሚነት አስቀድማችሁ አረጋግጡ፡፡ ለሕጻናት በሚቀርቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ የተለመዱት ገጸ-ባሕርያት ተወዳጅ ቢሆኑም፣ አስፈሪ የሆኑትን ግን እንዳይመለከቱ ተጠንቀቁ፡፡
 
5.   አማራጮችን ማሰብ፡- ቴሌቪዥንን አብዝተው የሚመለከቱ ልጆች አልፎ አልፎ የንባብ ችሎታ ማነስ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ ንባብ በልጆች የወደፊት የትምህርት ስኬት ላይ ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ ልጆቻችሁን በትንሽነት ዕድሜያቸው ከመጻሕፍት ጋር እንዲላመዱ ጥረት አድርጉ፡፡ ልጆች በጨቅላነታቸው ጊዜ ማንኛውንም ዕቃ (አሻንጉሊቶቻቸውን ጨምሮ) የመወርወር፣ ከግድግዳ ጋር የማጋጨት፣ እና ለማኘክ የመሞከር ልምድ ስላላቸው በዚህ ዕድሜያቸው የምትገዙላቸው መጻሕፍት የጠንካራ ፕላስቲክ፣ የጨርቅ፣ ወይም የካርድቦርድ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ከመጻሕፍት ጋር የተዋወቁ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር መጻሕፍትን አብሮ ማንበብን ይወዳሉ ሲሉ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡
በአጠቃላይ ቴሌቪዥን መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት በኩል ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት የመገናኛ መሣሪያ ቢሆንም፣ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት በልጆች አስተሳሰብ ላይ ከፍ ያለ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መረዳት ይገባናል፡፡ ወላጆች ”ቴሌቪዥን ልጆቻችንን አበላሸ” ከሚል ጭፍን አመለካከት ወጥተው የወላጅነት ኃላፊነታቸውን በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መንገድ ለመወጣት ቢሞክሩ ለልጆቻቸው ጤናማ አስተዳደግ መሠረት ስለሚጥሉ ከኃላፊነት መሸሹን ትተው የወላጅነት ግብራቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል እላለሁ፡፡

 

Thursday, August 6, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፪



ልጆች እና ቴሌቪዥንን አስመልክቶ ብዙ ስለማይነገርለት የወላጆች ኃላፊነት ሐሳቦችን መሰንዘር ጀምሬ ነበር፡፡ የአገራችን ወላጆች (ሁሉም ባይሆኑ አብዛኛው) በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በልጆቻቸው ባሕሪና አስተሳሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ጊዜ ወስደው ለማሰብ የሚጨነቁ አይመስለኝም፡፡ በቅርበት ከማውቃቸው ወላጆች መካከል በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው የልጆቻቸውን የቴሌቪዥን ዕይታ የሚከታተሉና ጥንቃቄ የሚያደርጉት፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግድ ከማጣት በተጨማሪ አለማወቅም ነው ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፌ ቴሌቪዥን በልጆች ላይ ስለሚያስከትለው ተጽዕኖ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
የሃያኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የቴክኖሎጂ አብዮት ካፈራቸው ግኝቶች መካከል አንዱ የሆነው ቴሌቪዥን የዕድሜ ታላቁ የሆነው ሬዲዮ ለሰው ልጅ ከሰጠው መረጃን በድምጽ የማስተላለፍ ዕድል አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ምስልን በማከል በአካል ልንገኝባቸው በማንችላቸው ሥፍራዎች ሁሉ እንድንገኝ አስችሎናል፡፡ የመረጃ፣ የመማሪያና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ ከዘመን ዘመን እያደገና እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ከቴክኖሎጂው መዘመን ጋር ተያይዞ በእጃችን መዳፍ ላይ እስከመገኘት ድረስ ተራቋል፡፡
 በዚህ ዘመን የቴሌቪዥን ቻናሎች በጣም በዝተዋል፡፡ ብዛታቸው የፈጠረው ውድድር ቀደም ባለው ጊዜ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ የነበረው የአየር ላይ ቆይታቸው ወደ ሃያ አራት ሰዓታት እንዲያድግ አድርጓል፡፡ ድሮ በባለዘንግ አንቴና በየቤታችን ይደርስ የነበረው የቴሌቪዥን ስርጭት ዛሬ በዲጂታል ስርጭት መቀበያ ሳህን (dish) እና የስርጭት መቀበያ መሣሪያ (decoder) እየመጣ ፣ ከሁለትና ሦስት ቻናሎች በላይ የማይታዩበት ጊዜ ቀርቶ በሺ የሚቆጠሩ ቻናሎችን በቴሌቪዥናችን መስኮት እየተመለከትን ነው፡፡ 
ይህ የቻናሎችና የፕሮግራሞቻቸው መብዛት አማራጭ በመስጠት በኩል ጥሩ የሚባል ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ተመልካቾች እንደምርጫና ፍላጎታቸው የተለያዩ ቻናሎችን እያማረጡ መመልከት መቻላቸው መረጃ በማግኘት፣ በመማር፣ እና በመዝናናት ረገድ እርካታቸው ጨምሯል፡፡ በሌላ በኩል ግን በጊዜ ያልተገደበ እና ምርጫ-አልባ የሆነ ቴልቪዥን የመመልከት ልምድ ቀላል ያልሆነ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥን መመልከት የጤናና የሥነ-ልቡና ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ ጉዳት የቅርብ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ላይ ብቻ ሳይሆን በአዋቂዎችም ላይ የሚደርስ እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሌላው የቴሌቪዥን ጉዳት የሚቀርቡት ፕሮግራሞች በተመልካቾችን አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተጽዕኖ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በማስተማር፣ በማሳወቅ፣ መረጃ በመስጠት እና በማዝናናት ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በተለይ ደግና ክፉውን ለይቶ ለማወቅ ገና የሆኑት ሕጻናትና ታዳጊዎች ሊመለከቷቸው የሚገቡትን ፕሮግራሞች መርጦ እንዲመለከቱ ማድረግ ካልተቻለ በወደፊት ባሕሪያቸው ላይ አደገኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡
ጥናቶች ምን ይላሉ?
ለመሆኑ ቴሌቪዥን በሕጻናት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን እንኳን ይህንን ስለመሰለው ጉዳይ ቀርቶ በጣም አንገብጋቢ ስለሆኑ ጉዳዮቻችን ጥልቅ ጥናቶች አይደረጉም፣ ቢደረጉም እንኳን በተሟላ ሁኔታ ተደራጅተው ስለማይቀመጡ አግኝቶ መጠቀሙም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ጽሑፍ የምንመለከታቸው ጥናቶች ባደጉት አገሮች የተደረጉትን ይሆናል፡፡ የእነዚህ ጥናቶች ውጤት በተወሰነ መልኩ ከአገራችን ሁኔታ የሚለይባቸው መልኮች ቢኖሩትም፣ መነሻው ግን ተመሳሳይ ስለሆነ ከጥናቶቹ በመነሳት ለእኛ የሚሆነውን ድምዳሜ መውሰድ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ቴሌቪዥን በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ የሚደረጉ ጥናቶች የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ፡-
1.       ልጆች በቀን ለምን የህል ሰዓታት ቴሌቪዥን ይመለከታሉ? እና
2.     በጨቅላነት ዕድሜ ቴሌቪዥን መመልከታቸው ምን ዓይነት ውጤት ያስከትላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞከራል፡፡
ሲንዲ ስሚዝ የተባሉ የንግግር ነክ ሕመሞች ተመራማሪ (speech pathologist) “Television Watching: Practical Advice for Parents of Young Children” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ወላጆች ለምን ልጆቻቸው ቴሌቪዥን እንዲመለከቱ እንደሚያደርጉ ከልምዳቸው ተነስተው ሲያብራሩ ”አንዳንዶቹ ‘ልጄ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ስለሚወደው፣’ ወይም ‘ ፊደላትን ስለሚማርበት’፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘ልጄ ምግብ አማርጣ የምትመገብ ናት፤ ቴሌቪዥኑ ከተከፈተ ግን እየበላች እንደሆነ ስለማታስተውለው ያለምርጫ ትመገባለች፣’ ወይም ‘እኔ እራት ሳዘጋጅ ልጄ ቴሌቪዥን በማየት ስለምትጠመድ አትረብሸኝም’ የሚሉና መሰል ምክንያቶችን ይሰጣሉ” ይላሉ፡፡
ባለሙያዋ በጥናታቸው ቴሌቪዥን ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 11 ዓመት ድረስ በሆኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ተመልክተዋል፡፡ የጥናታቸው ትኩረት ሕጻናትና ታዳጊዎች በቀን ውስጥ ለስንት ሰዓታት ቴሌቪዥን እንደሚመለከቱ የሚፈትሽ ሲሆን፣ በተገኘው ውጤት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ልጅ በአማካይ በቀን ከ4 ሰዓታት በላይ ቴሌቪዥን የሚመለከት ሲሆን፣ በካናዳ እና አውስትራሊያ በቀን ከ2 ሰዓታት በላይ፣ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ከ2 ሰዓት ተኩል በላይ ልጆች ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ”አንድ ልጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በክፍል ውስጥ ካሳለፈው ጊዜ ይልቅ በቴሌቪዥን ፊት ተቀምጦ ያሳለፈው ጊዜ ይበልጣል” ይላል ጥናቱ፡፡
ይህ የልጆች የቴሌቪዥን ልምድ ታዲያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናቸው ሲንዲ ስሚዝ፡፡ ጉዳቶቹ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተመድበዋል፡፡
1.      አካላዊ ጤና፡- በምዕራባዊያን አገሮች ለሕጻናት ውፍረት በዋነኛነት ምክንያት ተደርገው ከሚወሰዱት ነገሮች መካከል አንዱ ልጆች ቴሌቪዥን፣ ቪዲዮና ዲቪዲ ለመመልከት፣ እንዲሁም የኮምፒዩተር ጌም ለመጫወት ሲሉ በርካታ ሰዓታትን ተቀምጠው ማሳለፋቸው ነው (ይህ ልምድ ወደ አገራችንም በአሁኑ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህም የተነሳ የልጆች የአካል እንቅስቃሴ ልምድ ቀላል በማይባል ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል፡፡
2.     ሥነ-ባሕሪያዊ ጤና፡- እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ አንዳንድ ለሕጻናት ተብለው የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች በአማካይ በሰዓት 20 የሚደርሱ የግጭት/ረብሻ ትዕይንቶችን የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ትዕይንቶች በካርቱን ፊልሞች ላይ ከሚታየው የገጸ-ባሕርያት የእርስ በርስ መጋጨት አንስቶ በእውነተኛ ገጸ-ባሕርያት ከሚተወኑ የረብሻ (violence) ድርጊቶች ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ የሕጻናትና ታዳጊዎች የቴሌቪዥን ዕይታ ድርጊቶችን መሞከር፣ ፍርሃትን፣ እና ችግሮችን በኃይልና በጉልበት የመፍታት ዝንባሌን ያዳብራሉ ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
3.     ቋንቋ እና አጠቃላይ ትምህርት፡- ይህንን ክፍል አስመልክቶ በርካታ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ውጤታቸው የተለያዩ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን ”ዜናው ጥሩ አይደለም” ይላል የስሚዝ ጽሑፍ፡፡ እንደነዚህ ጥናቶች ከሆነ ለማስተማሪያ ተብለው የሚዘጋጁት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ በጨቅላ ሕጻናት የቋንቋ ትምህርት ብቃት ላይ መቀነስን አስከትለዋል፡፡
(ይቀጥላል)