Monday, May 4, 2015

ሐውልትና አዲስ አበባ



ባለፉት ሳምንታት በአገራችን፣ በተለይም በአዲስ አበባ መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የቦብ ማርሌይ ሐውልት መቆም ነገር ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መከራከሪያም ለመሆን የበቃው ”ቦብ ማርሌይ ለእኛ ምናችን ነው?” ከሚል መነሻ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በመነሳትም በአንድ ወገን ”ሕይወቱን በአደንዛዥ ዕጽ አበላሽቶ፣ መንምኖና አልቆ ለሞተ ዘፋኝ ሐውልት ለምን ይቆማል?” በሚሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ”የነጻነት ሰባኪና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ ቦታ እንዲኖራት አስተዋጽኦ ያበረከተውን ሰው በሐውልት ብንዘክረው ምን ይለናል?” በሚሉ አስተሳሰቦች መካከል ክርክር ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡
ክርክሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሐውልቱ ከቆመ በኋላ የከሰመ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ሐውልት መቆም ጉዳይ ስለሌሎች ሐውልቶች በስፋት እንድናስብ፣ በአጠቃላይም በከተማችንና በአገራችን የሐውልቶችን አስፈላጊነትና ፋይዳ እንድንጠይቅ ሳያደርገን የቀረ አይመስለኝም፡፡ እኔም እንደ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪና ኢትዮጵያዊ ሐውልቶቻችንን (ያሉትንም የሌሉትንም) አስመልክቶ ቀደም ሲል ሳስበው የነበረውን ሐሳብ እንድመለስበት አድርጎኛልና ከበርካቶቹ ሐሳቦቼ መካከል አንዱን ላነሳ ወደድኩ፡፡
በበኩሌ የቦብ ማርሌ ሐውልት በአዲስ አበባ  መቆሙን አስመልክቶ ቅሬታ የለኝም፡፡ ሐውልቱን ለማቆም ሐሳቡና አቅሙ ያለው አካል በመኖሩ፣ ሐውልቱ ሊቆምበት የሚችል አደባባይ ስላለና፣ የሚመለከተው አካል ሐውልቱ እንዲቆም ፈቃድ በመስጠቱ ሐውልቱ ቆሟል፡፡ እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች ተሟልተው ከተማችን አንድ ተጨማሪ ሐውልት ማግኘቷ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ጠቃሚነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ፣ ምናልባት ከዚህም በላይ፣ አንገብጋቢው ጥያቄ ”ለራሳችን ጀግኖችስ ሐውልት የማቆሙ ነገር እንዴት ነው?” የሚለው ነው ባይ ነኝ፡፡
ኢትዮጵያ በየሙያ ዘርፋቸው ጎልተው የወጡ ጀግኖች ደሃ አይደለችም፡፡ ”እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ መቁጠሩ ያደክመን ይሆናል እንጂ ጀግኖች ሞልተውናል፡፡ እነዚህን ጀግኖቻችንን በአግባቡ ማሰብ፣ መዘከርና ማስተዋወቅ ላይ ግን መሥራት የሚገባንን ያህል አልሠራንም፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት ካሉት መንገዶች መካከል አንደኛው ደግሞ ሐውልት ማቆም ነው፡፡ ያሉን ሐውልቶች ግን የጀግኖቻችንን ያህል የበዙ አለመሆናቸው የቤት ሥራችንን ያለመሥራታችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ?
ከላይ ስለቦብ ማርሌ ሐውልት ሳነሳ ለሐውልቱ መቆም አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ቅድመ-ሁኔታዎች አስቀምጬ ነበር፡፡ ከእነዚያ ሦስት ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል ለጀግኖቻችን ሐውልት ለማቆም የተሟላ ቢኖር የአደባባይ መኖር ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ መንገዶች ተሠርተውላታል፣ እየተሠሩላትም ነው፡፡ እነዚህ መንገዶች እርስበርስ በሚገናኙባቸው ቦታዎች ላይ አደባባዮች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህም አደባባዮች በብዛት እያገኘን መሆኑ ሐውልት የማቆሚያ ቦታ ችግር እንደማይኖርብን ያረጋግጥልናል፡፡ ቀሪዎቹስ ቅድመ-ሁኔታዎች?
የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ ሐውልት የማቆም ሐሳብና አቅም ያለው አካል መኖር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ”እገሌ፣እገሊት ወይም እነእገሌ በሥራቸው ጀግኖች ናቸውና ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል” የሚል ሐሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት በብዛት የሉንም፣ ኧረ ከነጭራሹም በዚህ ጊዜ አሉ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ በእርግጥ ቀደም ባለው ጊዜ አንዳንድ ሙከራዎች ተደርገው ነበር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰናክለው ቀሩ እንጂ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንደኛው የትብብርና የፍቃድ አለማግኘት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሁለተኛውም ቅድመ-ሁኔታ (የሚመለከተው አካል ፍቃድ) አልተሟላም ማለት ነው፡፡
የአገራችን ሐውልት ነክ ጉዳዮች በርካታ ሐሳቦችን ያስነሳሉ፡፡ በመግቢያዬም በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ሐሳቦች እንዳሉኝ ጠቆም አድርጌ ነበር፡፡ ለአሁኑ ግን ማተኮር የፈለግኩት በአንደኛው ላይ ብቻ ነው፤ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት የማቆም ጉዳይ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማጠንጠኛ ደግሞ አንድ የከተማችንን አደባባይና በአደባባዩ ላይ የቆመውን ሐውልት እንመልከት፡፡
(ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment