Monday, May 4, 2015

ሐውልትና አዲስ አበባ



ባለፉት ሳምንታት በአገራችን፣ በተለይም በአዲስ አበባ መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የቦብ ማርሌይ ሐውልት መቆም ነገር ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መከራከሪያም ለመሆን የበቃው ”ቦብ ማርሌይ ለእኛ ምናችን ነው?” ከሚል መነሻ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በመነሳትም በአንድ ወገን ”ሕይወቱን በአደንዛዥ ዕጽ አበላሽቶ፣ መንምኖና አልቆ ለሞተ ዘፋኝ ሐውልት ለምን ይቆማል?” በሚሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ”የነጻነት ሰባኪና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ ቦታ እንዲኖራት አስተዋጽኦ ያበረከተውን ሰው በሐውልት ብንዘክረው ምን ይለናል?” በሚሉ አስተሳሰቦች መካከል ክርክር ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡
ክርክሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሐውልቱ ከቆመ በኋላ የከሰመ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ሐውልት መቆም ጉዳይ ስለሌሎች ሐውልቶች በስፋት እንድናስብ፣ በአጠቃላይም በከተማችንና በአገራችን የሐውልቶችን አስፈላጊነትና ፋይዳ እንድንጠይቅ ሳያደርገን የቀረ አይመስለኝም፡፡ እኔም እንደ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪና ኢትዮጵያዊ ሐውልቶቻችንን (ያሉትንም የሌሉትንም) አስመልክቶ ቀደም ሲል ሳስበው የነበረውን ሐሳብ እንድመለስበት አድርጎኛልና ከበርካቶቹ ሐሳቦቼ መካከል አንዱን ላነሳ ወደድኩ፡፡
በበኩሌ የቦብ ማርሌ ሐውልት በአዲስ አበባ  መቆሙን አስመልክቶ ቅሬታ የለኝም፡፡ ሐውልቱን ለማቆም ሐሳቡና አቅሙ ያለው አካል በመኖሩ፣ ሐውልቱ ሊቆምበት የሚችል አደባባይ ስላለና፣ የሚመለከተው አካል ሐውልቱ እንዲቆም ፈቃድ በመስጠቱ ሐውልቱ ቆሟል፡፡ እነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች ተሟልተው ከተማችን አንድ ተጨማሪ ሐውልት ማግኘቷ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ጠቃሚነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ፣ ምናልባት ከዚህም በላይ፣ አንገብጋቢው ጥያቄ ”ለራሳችን ጀግኖችስ ሐውልት የማቆሙ ነገር እንዴት ነው?” የሚለው ነው ባይ ነኝ፡፡
ኢትዮጵያ በየሙያ ዘርፋቸው ጎልተው የወጡ ጀግኖች ደሃ አይደለችም፡፡ ”እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ መቁጠሩ ያደክመን ይሆናል እንጂ ጀግኖች ሞልተውናል፡፡ እነዚህን ጀግኖቻችንን በአግባቡ ማሰብ፣ መዘከርና ማስተዋወቅ ላይ ግን መሥራት የሚገባንን ያህል አልሠራንም፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት ካሉት መንገዶች መካከል አንደኛው ደግሞ ሐውልት ማቆም ነው፡፡ ያሉን ሐውልቶች ግን የጀግኖቻችንን ያህል የበዙ አለመሆናቸው የቤት ሥራችንን ያለመሥራታችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ?
ከላይ ስለቦብ ማርሌ ሐውልት ሳነሳ ለሐውልቱ መቆም አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ቅድመ-ሁኔታዎች አስቀምጬ ነበር፡፡ ከእነዚያ ሦስት ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል ለጀግኖቻችን ሐውልት ለማቆም የተሟላ ቢኖር የአደባባይ መኖር ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ መንገዶች ተሠርተውላታል፣ እየተሠሩላትም ነው፡፡ እነዚህ መንገዶች እርስበርስ በሚገናኙባቸው ቦታዎች ላይ አደባባዮች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህም አደባባዮች በብዛት እያገኘን መሆኑ ሐውልት የማቆሚያ ቦታ ችግር እንደማይኖርብን ያረጋግጥልናል፡፡ ቀሪዎቹስ ቅድመ-ሁኔታዎች?
የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ ሐውልት የማቆም ሐሳብና አቅም ያለው አካል መኖር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ”እገሌ፣እገሊት ወይም እነእገሌ በሥራቸው ጀግኖች ናቸውና ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል” የሚል ሐሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት በብዛት የሉንም፣ ኧረ ከነጭራሹም በዚህ ጊዜ አሉ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ በእርግጥ ቀደም ባለው ጊዜ አንዳንድ ሙከራዎች ተደርገው ነበር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተሰናክለው ቀሩ እንጂ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንደኛው የትብብርና የፍቃድ አለማግኘት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሁለተኛውም ቅድመ-ሁኔታ (የሚመለከተው አካል ፍቃድ) አልተሟላም ማለት ነው፡፡
የአገራችን ሐውልት ነክ ጉዳዮች በርካታ ሐሳቦችን ያስነሳሉ፡፡ በመግቢያዬም በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ሐሳቦች እንዳሉኝ ጠቆም አድርጌ ነበር፡፡ ለአሁኑ ግን ማተኮር የፈለግኩት በአንደኛው ላይ ብቻ ነው፤ ለተገቢው ጀግና ተገቢውን ሐውልት የማቆም ጉዳይ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማጠንጠኛ ደግሞ አንድ የከተማችንን አደባባይና በአደባባዩ ላይ የቆመውን ሐውልት እንመልከት፡፡
(ይቀጥላል)

Thursday, February 12, 2015

የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views: ጎንደሬው የጃማይካ ሰው

የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views: ጎንደሬው የጃማይካ ሰው: ዶ / ር በርናንድ ብራድሊ አንደርሰን ልደቱ ቅድስት ካትሪን ደብር ጀማይካ ዉስጥ ነዉ፡፡ ወሩ መስከረም፣ ቀኑ 21 ፣ ዓመተ ምሕረቱ 1944 ፣ አቆጣጠሩ በአዉሮጳውያን፡፡ ቅድስት ካ...

Tuesday, September 9, 2014

ደጋፊ! ደጋፊ! ደጋፊ!

ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ ያለሁት ብዙ ጊዜ ኳስ ከማይበት የመዝናኛ ሥፍራ ቁጭ ብዬ ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ ባለው ቴሌቪዥን ላይ ባለፈው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት በሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች (ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ) መካከል በኢትሃድ ስታዲየም (የማንቸስተር ሲቲ ሜዳ) ላይ የተካሄደው ጨዋታ እየተላለፈ ነበር፡፡ የዚህ ጨዋታ ውጤት ለዩናይትዶች አሸማቃቂና አሳፋሪ ነበር፡፡ አራት ለ አንድ!
ይህ ጨዋታ ከተካሄደ ዓመት ሊሆነው ስለተቃረበና ውጤቱንም የማውቀው ስለሆነ ትኩረቴ ጨዋታው ላይ አልነበረም፣ ከዚህ ይልቅ ትኩረቴበስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን እየተከታተሉ በነበሩት ተመልካቾች ላይ ነበር፡፡ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ቡድናቸው እንደዛ እየተቀጠቀጠ ባለበት ወቅት አኩርፈው ከመቀመጥ ይልቅ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ተጫዋቸቻቸውን ከማበረታታት አልቦዘኑም ነበር፡፡ ብስጭታቸው ፊታቸው ላይ እየተነበበ ቢሆንም፣ እዚያ ቦታ የተገኙበትን ምክንያትና ዓላማ አልዘነጉምና ማድረግ ያለባቸውን አድርገው ጨዋታውን እንደምንም ጨረሱት፡፡
ይህንን ለተመለከትሁ በኋላ፣ እኛስ እንዴት ነው የምንደግፈውን ቡድን የምናበረታታው? የሚለውን ጥያቄ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ለዚህ ሐሳቤ ደግሞ ተጨማሪ መነሻ ነበረኝ፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሲካሄዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከአልጄሪያ አቻው ጋር ተጋጥሞ ነበር፣ በውጤቱም 2-1 ተሸንፏል፡፡ ታዲያ በዚህ ጨዋታ ላይ እንደቀደሙት ጊዜያት ሁሉ በስታዲየሙ የታደሙ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ተመልካች ብቻ ሆነው መገኘታቸው ቅር አሰኝቶኝ ስለነበረም ጭምር ነው ይህ ጥያቄ የተፈጠረብኝ፡፡
"ደጋፊነት" ምን ማለት ነው? እኔ እንደሚገባኝ አንድ ሰው የአንድ ግለሰብ፣ ተቋም ወይም ስብስብ ደጋፊ ሲሆን፣ ለሚደግፈው አካል ዓላማና ተግባር መሳካት በበኩሉ ማድረግ የሚገባውን ነገር (ማበረታታት፣ በገንዘብ ወይም በጉልበት ወይም በሐሳብ እገዛ ማድረግ፣ በተደጋፊው አካል በሚደረግለት ጥሪ መሠረት መሳተፍ፣ ወዘተ) ማድረግ ነው፡፡ በዚህ የደጋፊነት ሚና ውስጥ ታዲያ፣ ተደጋፊው አካል በጉዞው ላይ አስፓልትም ሆነ ኮረኮንች መንገድ ቢያጋጥመው፣ ሜዳማ ወይም ተራራማ ቦታ ላይ ቢደርስ፣ የተራራው አናት ላይ ቢወጣ ወይም በሸለቆው ውስጥ ቢገባ፣ ዓላማውን እስካመነበት ድረስ ደጋፊው “አይዞህ! አለሁልህ! በርታ!” ሊለው ግድ ይላል፡፡ ይህንን ማድረግ ተስኖት፣ ሲወድቅ  “ይድፋህ!” የሚለው ከሆነ፣ አንድም ደጋፊ አይደለም፣ አንድም ደጋፊነትን አያውቀውም፡፡
ከዚህ ተነስተን የቅዳሜውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ድባብ ስንመለከት፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያኑ ታዳሚዎች “ደጋፊዎች” ሳይሆኑ “ተመልካቾች” ነበሩ ማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ አዲስ ሳይሆን፣ ለዓመታት ስናየው የኖረ ነው፡፡ ዛሬ ግን በደንብ ልናስብበት የሚያስፈልገውድጋፍ ከጭብጨባና ፉጨት ባለፈ ትልቅ ጉልበት ያለው መሣሪያ መሆኑን መረዳት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ በተለይ በእግር ኳሳችን ላይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየታየ ካለው አንጻራዊ መሻሻል አንጻር በሜዳላይ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች የምንሰጠው ድጋፍ ለዕድገቱ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ደጋፊ ሆነን የምናሰማው ዝማሬ፣ ጭብጨባ፣ ፉጨት፣ ወይም ጩኸት ለተጫዋቾቻችን የሞራል ስንቅና የሥነ-ልቦና ጉልበት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ የሚመቱት ኳስ ዒላማውን ባያገኝ ወይም የተጋጣሚ ቡድን ጎል ቢያገባ እንደተቆጡት ሕጻን እጅን ከንፈር ላይ አድርጎ መቀመጥ ለምንደግፈው ብድን እንደማይጠቅም ካላወቅንና የጨዋታውን እንቅስቃሴ ብቻ በመከታተል ጊዜውን የምናሳልፍ ከሆነ ገንዘብ ከፍለን ስታዲየም ከምንገባ በየቤታችን ቁጭ ብለን በነጻ በቴሌቪዥን ብንመለከት ይሻላል፡፡ ኧረ እንዲያውም ሰው ሰብሰብ ባለበት ቦታ ከሆነ ድጋፉም ከስታዲየሙም ይበልጣል! እኔ ጨዋታውን በተመለከትኩበት ቦታ (ይህ ጽሑፍ የተጻፈበት ቦታ ነው) ዝማሬውና ሆታው ሁለተኛው የአልጄሪያ ጎል ከተቆጠረ በኋላም አልተቋረጠም ነበር፡፡

ስለዚህ ጎበዝ! ደጋፊ እንጂ ተመልካች አንሁን፡፡ መመልከት ለመዝናናት መጥቀሙ ባይካድም፣ ስታዲየም ስንገባ የምንደግፈውን ቡድን ለማበረታታት መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ተጫዋቾቻችን የእኛን ድጋፍ በእጅጉ ይፈልጋሉና ዝም አንበላቸው፡፡ በአውሮፓው እግር ኳስ እኮ የጨዋታው ውበት የሜዳው ላይ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የደጋፊዎቹ የማያቋርጥ ዝማሬና ጩኸትም እንደሆነ በቴሌቪዥንም እናያለንና፣ ከኮረጅን አይቀር እንደቴክኒኩ ሁሉ አደጋገፉንም አብረን ብንኮርጅ ምን ይለናል?

Friday, May 30, 2014

ካርል፣ ከኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊ!


እነሆ! ትናንት ባለውለታችንን አጣን፡፡ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ አጋር፣ ከራሱ ዝናና ክብር በላይ ለሌሎች የመኖር ጉጉት አይሎበት፣ ምቾትና ድሎቱን ለሰብአዊነት ሲል ትቶ፣ችግራችንን ተቸግሮና በደስታችን ተደስቶ 33 ዓመታትን ከኢትዮጵያዊያን በላይ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኖረው ካርልሃይንዝ ቦም በ86ኛው ዕድሜው ላይ ለሞት እጁን ሰጠ፡፡ ሰው ሆኖ ኖሮ የማይሞት አለመኖሩ የማይቀር ቢሆንም፣ እንደካርል ዓይነቱ ልበ-ብርሃን ግን ሲሞት ብዙ ያጎድላል፡፡
ይህ ካርልሃይንዝ ቦም የሚባል ሰው የበርካታ ገድሎች ባለቤት ነው፣ ታሪኩ ትልቅ መጽሐፍ የሚወጣው፡፡ ከእኔ በላይ ብዙ ሊናገሩ የሚችሉ ሰዎች አሉና ብዙ ልል አልችልም፡፡ ሰውየውን ለማስታወስ ግን ከእርሱ ጋር የሚያያዙና በጣም የሚነኩኝን ሦስት  ነገሮች ብቻ ላንሳ፡፡
1.      ካርል ለበጎ አድራጎት ሥራው ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው በ1973 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን በቀጥታ አልነበረም ወደዚህ የመጣው፡፡ ወቅቱ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የድርቅ አደጋ ያንዣበበባቸው ወቅት ነበርና፣ ካርልም የድርቁ አደጋ የከፋባቸውን የሳህል አገሮችን ለመርዳት አስቦ ነበር ወደአፍሪካ የመጣው፡፡ በመጀመሪያ ቻድ ሄደ፣ የቻድ መንግሥት አልተቀበለውም፡፡ ቀጥሎ ወደሱዳን አቀና፣ የካርቱምም ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በሦስተኛ ሙከራው ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ግን የወቅቱ መንግሥት በደስታ ነበር የተቀበለው፤ ያለቢሮክራሲያዊ ውጣ-ውረድ፣ ”እስቲ የመደብ ጀርባው ይጠና ” ሳይባል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ያሳየው ተቆርቋሪነትና የተደረገለት አቀባበል ግን በሁሉም ወገን በኩል በቀና አልታየም፡፡ በተለይ በጊዜው በስደት በምዕራብ አገሮች የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ”ይህ የምዕራብ አገር ሰው ከደርግ ጋር መሥራቱ ክህደት ነው” በሚል ከፍተኛ የተቃውሞና አለፍ ሲልም የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ካርል፣ ”ሰብአዊ አገልግሎትና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ሰብአዊነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” በሚል ጽኑ አቋም፣ የተከፈተበትን ዘመቻ ከቁብም ሳይቆጥር ሥራውን ቀጠለ፡፡  ኢትዮጵያም ደርሶ ከ33 ዓመታት በፊት ”ሰዎች ለሰዎች” (Menschen für Menschen) የተባለውን ምግባረ-ሰናይ ድርጅቱን በመመሥረት በጤና እክል ምክንያት ሥራውን እስካቆመበት እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ በሊቀመንበርነት መርቶታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን እንደ ድርጅቱ ሠራተኛ አንድም ጊዜ ደመወዝ ሳይወስድ በነጻ ነበር ታላላቅ ሥራዎችን የሠራው፡፡
2.     ”ሰዎች ለሰዎች” ሥራውን በጀመረበት የኤረር ሸለቆ አካባቢ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዲ አሊ ቦሩ አንዱ ነው፡፡ አብዲ፣ እንደሌሎቹ ተጠቃሚዎች ሁሉ ለካርል ከፍ ያለ ፍቅር ቢኖረውም፣ የፍቅሩ መግለጫ ግን የተለየ ነበር፡፡ ማንም ሳያዘው፣ ሳይቀጥረውና ደመወዝ ሳይከፍለው፣ ካርል ወደ ቦታው በመጣ ጊዜ ሁሉ፣ እዚያ በሚገኘው ቤቱ በር ላይ ማታ ማታ እየተኛ፣ ክፉ እንዳያገኘው ሲጠብቀው ያድራል፡፡ ካርል ጠዋት ተነስቶ በሩን ሲከፍት መጀመሪያ የሚያየው ደጃፉ ላይ ጥቅልል ብሎ የተኛውን አብዲን ነበር፡፡ ታዲያ አብዲ ይህንን ለምን እንደሚያደርግ ሲጠየቅ፣ ”ካርል ለእኔ አባቴ ነው፡፡ አባቴ ያላደረገልኝን ነገር አድርጎልኛል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው አንድ ነገር ቢሆን ምን ይውጠኛል? መጥፎ ነገር ቢመጣ እንኳ መጀመሪያ እኔን ያግኘኝ ብዬ  ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ካርልም ለአብዲ ያለው ፍቅር እጅግ የበዛ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ለድርጅቱ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጀርመን ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ሰፊ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ባገኘ ፕሮግራም ላይ  ታዲያ አዘጋጆቹ ካርልን ሰርፕራይዝ ያደረጉት በአብዲ ነበር፡፡ አብዲ ሽርጡን እንዳሸረጠ ወደመድረኩ ሲመጣ ካርል ዓይኑን አላመነም ነበር፡፡ ትልቁን ሰውዬ እንደ ሕጻን ልጅ አገላብጦ ነበር የሳመው፡፡ ”ታማኝ ወዳጄ” ሲልም አሞግሶታል፡፡ ካርል ለሠራቸው በጎ ሥራዎቹ ሁሉ ተጠቃሚዎቹ አመስግነውት አይጠግቡም፡፡ በ1995 ዓ.ም. ”ሰዎች ለሰዎች” በሰሜን ሸዋ መሐል ሜዳ ላይ ያሠራው ”ካርል ሆስፒታል” በተመረቀበት ወቅት አንድ የአካባቢው አርሶ አደር ሲናገሩ (ቃል በቃል ላይሆን ይችላል) ”በፊት ሕክምና በዚህ ባልነበረ ጊዜ በትንሽ ሕመም እንኳ ብዙ ሰው ይሞትብን ነበረ፡፡ ቃሬዛ ሠርተን ተሸክመን ወደ ከተማ እየወሰድን መከራችንን ስንበላ ኖርን፡፡ አሁን ግን ካርል ከመጣ በኋላ ሰዉ ሆዴን ቆረጠኝ፣ ራሴን ፈለጠኝ ቢል ከዚሁ ከጓሯችን ሂዶ ክኒናውን እየዋጠ ጤና ሆነ፣ እኛም ይኸው ካርልን ያኑርልን እያልን ደስ ብሎን አለን፡፡” ብለው ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ምስጋናና ምርቃትም አግኝቷል፡፡
3.     ከዛሬ 8 ዓመት በፊት የ”ሰዎች ለሰዎች” 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጀርመን የባሕል ተቋም (ጎተ ኢንስትቲዩት) በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በረጅም ጊዜ የተቋሙ ደንበኝነቴ አዳራሹ እንደዚያ ቀን ሞልቶ ያየሁበትን ቀን አላስታውስም ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ካርል ነበር፡፡ በዚያው ሰሞን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርብ በነበረው ”ዐውደ-ሰብ” የተባለ ፕሮግራም ካርልን የተመለከተ ሰፊ ዝግጅት ቀርቦ ስለነበር ብዙ ሰዎች ለካርልና ለ”ሰዎች ለሰዎች” ግምታቸው ከፍ ብሎ ስለነበር ይመስለኛል፡፡ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ነበረ፣ ከካርል ጋር አብረው የሠሩና ካርልን የሚያውቁ ታዋቂ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጡ፣ በመጨረሻ ላይ ካርል ንግግር አደረገ፡፡ ከንግግሩ መካከል እስከዛሬ የማይረሳኝ ”ዛሬ ኢትዮጵያ አገሬ ሆናለች፡፡ አገሬን ደግሞ ተለውጣ ላያት እመኛለሁ፡፡ አሁን የናፈቀኝ እናንተ ‘ዛሬ ራሳችንን ችለናልና ላደረጋችሁልን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ካሁን በኋላ ግን አንፈልጋችሁም ‘ የምትሉበትን ቀን ነው፡፡” ያለውን ነው፡፡ ይህንን ሕልሙን ዕውን ሆኖ ሳያየው ሞት ቀደመው፡፡

ዛሬ ካርል አርፏል፡፡ የእርሱ ዕረፍት ደግሞ ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ”እኛ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ምን አደረግን?” የሚል ጥያቄ፡፡ ይህ ሰው፣ ምኑም ያልሆነች አገር ችግር ቢያመው፣ ብዙ ሐብት ያፈራበት የነበረውን የቴአትርና የፊልም ተዋናይነቱን ትቶ፣ ያለውን ሁሉ ለዚህች አገር ሲሰጥ፣ እኛ ያገር ተወላጆቹ ”ምን ሠራን?” ብንል መልሱ ያሳፍረናል፡፡ በተለይ፣ ”ባለሐብት” የሚባሉት (ከጥቂቶች በስተቀር)፣ ያላቸውን በሙሉ ባይሰጡ እንኳን፣ ከዓመታዊ ትርፋቸው ላይ ጥቂቱን አንስተው በተደራጀ መልኩ ለበጎ አድራጎት ሥራ ሲያውሉ የማይታዩ መሆናቸው አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ይህ ነው ”ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚያስብለው፡፡ ካርል! ከኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ኖረህ፣ ኢትዮጵያዊ ሆነህ አርፈሃል፡፡ ውለታህን ግን አንዘነጋውም፡፡ ስናመሰግንህ እንኖራለን፡፡  ምስጋናችን በሁለት ምክንያት ነው፣ አንድም፣ በችግራችን ወቅት ስለደረስክልን፣ ሁለትም፣ራሳችንን እንድንወቅስ  ስላደረከን፡፡

Sunday, November 17, 2013

ኧረ ጎበዝ ምን ነካን?!

እኔ የምለው፣ ትችትን ወይም ተቃውሞን ያለስድብ መግለጽ አይቻልም እንዴ? በፌስቡክ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል ብዙዎቹ ስድብና ዘለፋን ያዘሉ መሆናቸው በግሌ በጣም ያሳስበኛል፡፡ ያልተስማማንበትን ነገር ሲሆን በምክንያት፣ ካልሆነም እንዲሁ ”አልተስማማሁበትም” ብሎ መቃወም ሲቻል፣ በተራ የመንደር ስድቦች እና ጸያፍ ቃላት መዝለፍ ”ምን እየሆንን ነው? ”የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት በፌስቡክ ላይ ከወጡ በርካታ ዜናዎች ሥር የሚጻፉ አስተያየቶችን ማየት ይቻላል፡፡ እኔ ግን በተለይ ትኩረቴን የሳበውን አንድ ጉዳይ ብቻ አንስቼ የታየኝን ልል ወደድኩ፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቴዲ አፍሮ ”መሬት ሲመታ” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማበረታቻ አንድ ነጠላ ዜማ ለቀቀ፡፡ ይህም በፌስቡክ ላይ ተገለጸ፡፡ እንደተለመደውም ብዙ አስተያየቶች ተሰጡ፡፡ ከአስተያየቶቹ ውስጥ በርከት ያሉ አሉታዊ ትችቶች ባልተለመደ ሁኔታ ነበሩበት፡፡ ትችቱ ባልከፋ ፣ ግን፣ሁሉም ትችቶች በተራ ስድብ እና ዘለፋ የተሞሉ፣ ምክንያታዊ ያልሆኑ መሆናቸው ነው ችግሩ፡፡ ቴዲ ዋሊያዎችን ለማበረታታት፣ እኛን ደጋፊዎቻቸውንም ለማጠንከር በሙያው አንድ አስተዋጽኦ ሲያደርግ፣ ማመስገኑ እና ማድነቁ ቢቀር  እንዴት ሰብዕናን በሚያዋርድ መልኩ፣ያውም ሥራውን ሳናደምጥ፣ ለዘለፋ እንቸኩላለን? አያይ! በጣም ችግር አለብን፡፡
አንዳንዶች ”ቴዲ ዘገየ ” ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ”ቴዲ ራስ ወዳድ፣ ገንዘብ አፍቃሪ፣ ሳንቲም ለቃሚ፣ እና ስግብግብ ነው” ሲሉ ይሰማል (ይነበባል)፡፡ ሁሉም አሉታዊ ትችቶች መሠረት የሌላቸው እና ”ውሃ የማያነሱ” ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ከሙያዊ ማንነቱም ሆነ ከግላዊ ሰብዕናው ጋር የማይገናኙ እና፣ ምናልባትም፣ የቅናት የሚመስሉ፡፡ ከላይ ያነሳሁዋቸውን ”አስተያየቶች” እስቲ ተራ በተራ እንመልከት፡፡
1.      ቴዲ ዘግይቷል፡ ይህንን አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች መነሻቸው (በእኔ ግምት) ”ብሔራዊ ቡድናችን በኢንተርናሽናል መድረኮች ረዥም ርቀት ከተጓዘ እና ቡድኑን የሚያሞግሱ በርካታ ሙዚቃዎች ከወጡ በኋላ የቴዲ ”መሬት ሲመታ” መምጣቱ ስህተት ነው” የሚል ነው፡፡ እኔ እንደማምነው ግን የጥበብ ሥራ ሰፊ ጊዜን፣ ትኩረትን፣ እና ጥሞናን ይፈልጋል፡፡ ቴዲም ያለውን ሁኔታ በጥሞና ከተመለከተ በኋላ ‘ለሁላችንም ያስፈልገናል’ ብሎ ያመነበትን ሐሳብ ተገቢ ነው ባለው ጊዜ በሙዚቃ አቀረበልን፡፡ ይህ መዘግየት አይመስለኝም፡፡ ወቅታዊነትን መጠበቅ፣ ያላየነውን ጎን ማሳየት፣ እና ማበረታታት እንጂ፡፡
2.     ቴዲ ራስ ወዳድ ነው፡ ”ራስ ወዳድነት” ምንድን ነው? ራስ ወዳድነት ከራስ አልፎ ማየት አለመቻል፣ ”እኔን ከተመቸኝ ሌላው ምናባቱ” ማለት፣ ወዘተ ይመስለኛል፡፡ የቴዲ ታሪክ ይህ አለመሆኑን ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ቴዲ በሙያው ያገኘውን ዕውቅና ለመልካም ሲያውለው በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የቅርቡን እንኳን ብንወስድ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ካቀረበው የመጀመሪያ ኮንሰርት አንዲት ሳንቲም ለራሱ ሳይወስድ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መስጠቱ፣ ከራሱ ኪስም አውጥቶ ሌላ የበጎ አድራጎት ድርጅትን መርዳቱ፣ በእጁ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው እንኳ ራሱን ባለዕዳ አድርጎ በሶማሌላንድ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን ወገናችንን የደም ዋጋ ከፍሎ ከሰይፍ ማስጣሉ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ታዲያ የት ላይ ነው የቴዲ ራስ ወዳድነት?
3.     ቴዲ ገንዘብ አፍቃሪ ነው፡ የዚህኛው ትችት መነሻ ደግሞ ”ቴዲ የሙዚቃ ዝግጅቶችን የሚያቀርበው ገበያውን እና የሚከፈለውን ገንዘብ እያየ ነው” የሚል ይመስለኛል፡፡ እንዴ?! ሁላችንስ ብንሆን በየሥራ ዘርፋችን የተሻለ ክፍያ የምናገኝበትን አይደል እንዴ የምንመርጠው? ታዲያ ይህ የሁላችንም ፍላጎት ቴዲ ጋር ሲደርስ ሀጢያት የሚሆነው ለምንድን ነው? የተሻለ ክፍያ የምንጠይቀው እኮ የሚከፈለን ክፍያ ሥራችንን የሚመጥን መሆን ስላለበት ነው፡፡ ቴዲም እኛ ዛሬ እንድናደንቀው እና መነጋገሪያ እንዲሆነን ያስቻሉትን ሥራዎቹን በሚመጥን ክፍያ ማቅረቡ የሰው ፍላጎት፣ የንግድ አሠራር መንገድም ነው እንጂ ወንጀል አይደለም፡፡
4.     ቴዲ  ሳንቲም ለቃሚ ነው፡ አንድ ሰው በሚሠራው ሥራ ፈላጊ ያለበትን ቦታና ጊዜ መምረጥ አለበት፡፡ የዚህኛው ትችት አቅራቢዎች እንደ ማጠናከሪያ የሚያቀርቡት አምና በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው እና አገራችን ከ31 ዓመታት በኋላ በተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ ዋዜማ በጆሐንስበርግ ኮንሰርት ማቅረቡን ነው፡፡ ካዋጣው ለምን አያደርገውም? ሥራው እስከሆነ ድረስ እና ወቅቱም አመቺ ሆኖ ከተገኘ በዚያ የሚገኙ ወገኖቹን አዝናንቶ ለሥራው ቢከፈለው ነውሩ ምንድን ነው? ”ሳንቲም መልቀም” እኮ ለ”ሳንቲሟ” ሲባል ”ከፍራሹም፣ ከጭቃውም ላይ መውደቅ”  ነው፡፡ ቴዲ ደግሞ ይህንን ሲያደርግ እስካሁን አላየንም፡፡
5.     ቴዲ ስግብግብ ነው፡ ይህኛው ምንም ማብራሪያ የማያስፈልገው ”ባዶ እና ተራ ዘለፋ” ነው እላለሁ፡፡ ሥራን ሠርቶ ገንዘብ  ማግኘት፣ ካገኙት ገንዘብ ላይ ለመልካም ተግባር መስጠት ”ስግብግብነት” ነው  የሚል ካለ፣ አዕምሮውን መመርመር አለበት፡፡ የቴዲን ”ስግብግብነት” በማስረጃ ያቀረበ አንድም የፌስቡክ ተቺ የለም፡፡ ለዚህ ነው ”ባዶ እና ተራ ዘለፋ” ነው ያልኩት፡፡ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የቴዲንም ሆነ የማንኛውንም የሙዚቃ ባለሙያ ሥራ ሳናዳምጥ እና መልዕክቱን ሳንረዳ፣ ጫፍ ይዘን መሮጥ አላዋቂነት ነው ባይ ነኝ፡፡ በተጨማሪም የአንድን ሰው ግላዊ ማንነት ከሙያዊ ማንነቱ ጋር አደባልቆ ማየትም ፍርደ-ገምድልነትን ያመጣል እላለሁ፡፡ አንድ ምሳሌ እንይ፡፡ ጥላሁን ገሠሠን የአገራችን የሙዚቃ ንጉሥ አድርገን የሾምነው፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ያደነቅነው፣ የወደድነው፣ እና ያከበርነው፣ በሞቱም ጊዜ አደባባይ ወጥተን፣ በጸሐይ እየተጠበስን በታላቅ ለቅሶ የሸኘነው እና በብሔራዊ ጀግና ክብር የቀበርነው በሥራዎቹ ጥራት እና ታላቅነት ነው እንጂ የግልና የቤተሰብ ሕይወቱማ ለአርአያነት እንደማይበቃ ጠፍቶን አይደለም፡፡ ቴዲም እንደግለሰብ ድክመቶች ሊኖሩበት እንደሚችል ሳንረሳ ያንን ለራሱ ትተን ሥራዎቹን በማስተዋል ብንመዝን ከስህተት እንድናለን፡፡
ቴዲን አለመውደድ መብት ነው፣ ሥራውን አለማድነቅም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ስንተች ስድብ እና ዘለፋን አስወግደን ለመማማርና ለመተራረም ልናውለው ይገባል፡፡ ”በፌስቡክ ላይ የሚሰጡ በቁጥር ቀላል የማይባሉ አስተያየቶች በስድብ መታጀባቸው ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችን የት ገባ?” የሚያሰኝ ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ ምን ነካን?

Monday, July 29, 2013

Fixing the Blurry Glasses

The afternoon of Friday, July 12, saw a somewhat "bizzare" incident at London's Heathrow Airport. A smoke was seen on the tail of an Ethiopian Airlines Boeing 787 Dreamliner. The international media made the incident their headline story since late Friday (at least for 24 hours). The amazing thing was, the smoke (probably caused by a fire ignited by "transmission problem", as concluded by investigators) was triggered eight hours after the aircraft was parked at the airport.
I think the Heathrow incident made the headlines not for the fact that the plane is an Ethiopian property. Rather, it was for two other reasons; One: the incident happened on British soil, and two: it happened on a plane that is "equipped with the latest technology." For whatever reason, the incident turned people's heads to our country one more time.
What moved me to write this post wasn't the Heathrow incident. It is rather the comments and responses that came after the news broke out. A considerable number of people, mainly from the western world, were amazed by the fact that Ethiopia actually owns a Dreamliner, even has an airliner. Some even went further to express their disbelief that Ethiopians manage to "eat at all," let alone having their own flag carrier. 
It makes me sick to hear and see people from the so-called "First World" to disregard the "Third World" in an uncivilized way. They sometimes claim to know the nature, behavior, and fate of the people of Africa, Latin America, and Asia as the palm of their hands. In the case of Ethiopia, they think the entire nation became a bare-land after the 1984/85 drought, they were the only ones who saved the day.  They consider a skinny person an Ethiopian, and the people from Ethiopia are "good-for-nothing." They tend to believe we're doomed to live and die poor and starved. Hypocrites!
I believe it's time to tell the facts to those who do not know (or blindfold themselves not to know) the truth. Their racist and fictionally-driven "superior mentality" must be eradicated once and for all. It's time to fix the blurry eyeglasses of "the white folks!"

A lesson in History
Aircraft began to flew over Ethiopian skies long before the establishment of the Ethiopian Airlines. A French pilot, Andrẻ Maillet, flew a twin-engined Potez aircraft from Djibouti, and landed at Jan Meda in Addis Ababa on August 18, 1929. With the threat of the Fascist Italian invasion plans, according to the renowned historian, Prof. Richard Pankrust, the Ethiopian government of the day has ordered two more aircraft from Germany, even though  the delivery was delayed by the French authorities at Djibouti in order to make the French aircraft arrive first. 
After the return of the government after the Italian invasion of 1935-41, Emperor Haileselassie took up the concept of establishing a national airliner seriously, and asked the governments of the US, the UK, and France to help in this endeavor. His efforts have finally paid off, and on 8 September, 1945, the American airliner, TWA, signed an agreement with John Spencer, who was the foreign affairs advisor to the emperor, to establish a commercial airline for Ethiopia.(Historical Dictionary of Ethiopia, 2004).
Over the coming years, the airline has made tremendous developments in its activities; such as expanding its routes, replacing personnel from TWA (one such a notable appearance was the introduction of the first African jet pilot, Capt. Alemayehu Abebe), and the acquisition of some of the modern aircraft to date, including the landmark products of Boeing like the B767 (1984) and B787 Dreamliner (2012).
The success of the Ethiopian Airlines over the last 67 years have placed Ethiopia on the world map, as one of Africa's modern nations. Unlike some 'ferenjis,' who are ignorant of such developments, this airline has exhibited strength, dedication, and commitment as the springboards of its success. It is a success that hasn't been interrupted by the succession of governments, famine, wars, or any other mishaps in the country over the years.   
I was pretty much amazed and inspired by the long success story of Ethiopian Airlines for so long, especially by the time I was doing a research on the passenger transport services of the airline about 11 years ago when I was a student at the Addis Ababa University. The success, came with tireless efforts by the staff and management of the company, and even with sacrifices made by the loss of lives, are exemplary for all of the "Third World" nations in showing the way to success without the so-called "Superpowers" breathing at their necks. And Ethiopians are always proud of their national carrier.
Africa's First Dreamliner, "Queen of Sheba". Photo: from Wikipedia
There has been a lot to tell those who doubt Ethiopia can achive so much in the airline industry. But I think it is better to leave that to themselves to find out, since a lot can be found from the archives, and the internet. Their comments, which might come just out of jealousy of the fact that we have the Dreamliner before the Europeans and the Americans, or just of ignorance, are baseless. And so they need to learn history, and redeem themselves for their racist views.
So there you have it, you doubters! Believe it or not: We have an airline, and we have the Dreamliner (five of them, actually). We have pilots, flight attendants, and technicians that bring our national colors to the sky. We have the facilities to train airline personnel from all around the world, maintain aircraft from any part of the globe, and we have more than half-a-century's experience in flying under our belt. Stop being narrow minded, and start digging for history. We're not only of famine and poverty. We have so many success stories to tell, and we're a proud nation. And there's nothing you can do about it!
Long Live Ethiopia!


Wednesday, October 24, 2012

የምር “ወንድ” እንሁን!!!

ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ልጽፍ ነው፡፡ በሦስት ምክንያቶች፡፡
·         አንደኛ፡- ይህንን ብሎግ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ  አብሮኝ ያለውን “አንድ ቀን በአገሬ ቋንቋ እጽፋለሁ፡፡” የሚለውን ሐሳቤን ለማሳካት፣
·         ሁለተኛ፡- የዛሬው ርዕሴ ትንሽ ከበድ ያለ እና ድርጊቱም በአገር ደረጃ አሳፋሪ እና አሰቃቂ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ቋንቋ ጽፌ አገሬን “ሰድቦ ለሰዳቢ” ላለመስጠት፣
·         ሦስተኛውና ዋነኛው ምክንያቴ ደግሞ ፡- ስለዚህ ዘግናኝ እና አሳሳቢ ጉዳይ ለመጻፍ ከአፍ መፍቻ ቋንቋዬ የተሻለ ቋንቋ ስላላገኘሁ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በእጅጉ የማደንቀው ጸሐፊ ዳንኤል ክብረት “እስከመቼ” በሚል ርዕስ በብሎጉ ላይ ባወጣው ጽሑፍ በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው በሚሠሩ እና ሰርክ በሚያስቀና ፍቅራቸው በሚታወቁ ወንድም እና እህት መካከል በተፈጠረ ጊዜያዊ አለመግባባት ምክንያት የተከሰተውን ዱላ-አከል ጠብ አስመልክቶ የተሰማውን ስሜት አስፍሮ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ አንባቢያን የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ ድርጊቱን ሲያወግዙ፣ ጥቂቶች “እና ምን ይጠበስ?” ዓይነት አስተያየት ነበር የሰጡት፡፡
ጉዳዩን እንዲሁ ላይ ላዩን ሲመለከቱት ቀላል ነገር ይመስላል፡፡ “ወንድም እና እህት በሥራ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ተጋጩ፣ ወንድም እህቱን በጥፊ ወለወለ፣ በቃ፡፡ እንኳን ሰው እና ሰው እግር እና እግርስ ይጋጭ የለ?” ብዙዎች ይህንን እንደሚሉ አይጠረጠርም፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን  ነገር ሰፋ አድርገን ካስተዋልነው ግን እነዚህን መሰል “ቀላል” ነገሮች ተጠራቅመው ከባድ እና አሳሳቢ እንደሚሆኑ ማስተዋል ይቻላል፡፡
ለዚህ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ ክስተት የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ነበር፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለምዶ “መስቀል ፍላወር“ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከሩብ ላይ አንድ ግለሰብ የቀድሞ ባለቤቱ የምታሽከረክረውን መኪና በመኪናው መንገድ ዘግቶ ካስቆማት በኋላ በያዘው ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ተኩስ ከፍቶ እርሷን በ18 ጥይቶች መትቶ ሲገድል፣ አብረዋት የነበሩትን ወላጅ እናቷን እና ሁለት በአካባቢው የነበሩ ግለሰቦችን አቆሰለ፡፡ በመጨረሻም ራሱን ለመግደል ሲሞክር ጥይት በመጨረሱ ሳይሳካለት ቀርቶ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡     
ብዙ ዓይነት የግድያ ወንጀሎችን በዕድሜዬ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይም በባል እና በሚስት መካከል ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጋር ተያይዞ እስከሞት ድረስ የደረሱ ጥቃቶችን አውቃለሁ፡፡ ይህኛው ግን ሲበዛ አሰቃቂ እና አስፈሪ ሆኖብኛል፡፡ ከባለጉዳዮችም አልፎ ሌሎች ንፁሃንንም የጎዳ እና ከልክ ያለፈ አረመኔያዊ ጥቃት!
ባለችኝ ጥቂት የጦር መሣሪያ ዕውቀት መሠረት አንድ የክላሽኒኮቭ ጠመንጃ የጥይት ካርታ 30 ጥይቶችን ይይዛል፡፡ እንደሟች እናት ምስክርነት ሟች በ18 ጥይት ተመትታ ነው የተገደለችው (ፖሊስ ገና እያጣራ ቢሆንም)፡፡ እናት በሦስት ጥይቶች መመታታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁለት መንገደኞችም በተኩስ እሩምታው ቆስለዋል፡፡ ምናልባት እያንዳንዳቸው በሁለት ወይም በሦስት ጥይቶች ተመትተዋል ብለን እናስብ፡፡ ስንደምራቸው ወደ ቢበዛ ወደ 27 ያህል ጥይቶች በሰለባዎቹ ላይ አርፈዋል፡፡ ተጠርጣሪው ራሱን ለመግደል ሞክሮ ጥይት ስለጨረሰ ሳይሳካለት ቀርቷልና ቀሪዎቹ ሦስት ጥይቶችም ተተኩሰዋል ማለት ነው፡፡
ይህንን ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ግድያ (ርሸና ብለው ይሻላል) ቀደም ሲል የምናውቀው በምዕራቡ ዓለም ነበር፡፡ ከሥራው የተባረረ፣ ትዳሩ የፈረሰ፣ አዕምሮው የተቃወሰ እና የጦር መሣሪያ እጁ የገባ ሁሉ አገር ፈጅቶ እራሱን ሲያጠፋ ብዙ ጊዜ ሰምተናል፡፡ እኛ አገር ከጥቂት ዓመታት በፊት በግል ጠብ ምክንያት ይህን የመሰለ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሳለሁ፡፡ ትዳር-ተኮር በሆነ ምክንያት ግን… ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
እንደሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ ተጠርጣሪው የቀድሞ ባለቤቱ እና ልጆቹ “ጠልተውኛል” የሚል ስሜት አድሮበታል፡፡ ለዚህ ስሜቱ ወይም ስጋቱ መፍትሄው መግደል ነው ብሎ ማመኑ እርምጃውን ለመውሰድ እንደገፋፋው ማሰብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ በምድርም ሆነ በሰማይ የተሳሳተ፣ ወንጀልም ኃጢያትም መሆኑ አያከራክረንም፡፡ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላማዊ የሆኑ ብዙ መንገዶች ስላሉ፡፡
በፍቅርም ሆነ በትዳር ግንኙነቶች ውስጥ አለመግባባትና ግጭት ይከሰታል፡፡ እነዚህን ችግሮች ቢቻል በውይይት፣ ካልተቻለ በሽምግልና፣ ከዚያ ከከበደ ደግሞ በመለያየት መፍታት ይቻላል፡፡ እነዚህ በፍቅርና በትዳር መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በአግባቡ መያዝ እስከተቻለ ድረስ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክሩ አምናለሁ፡፡
ይህ ማለት ግን ሁልጊዜም ግጭት መኖር አለበት፣ ግጭቱ በየትኛውም መልክ የሚገለጽ ይሁን ማለት አይደለም፡፡ በግጭት ስም ዲያቢሎስ ወደቤታችን እንዲዘልቅ በፍጹም መፍቀድ አይገባንም፡፡ አበው “ሰይጣን ሰውን ሲያታልል “ስለፍቅር በስመአብ ይቅር” ይላል” ይላሉ፡፡ ዛሬ በአገራችን እያየን እና እየሰማን ያለነውና በፍቅርና በትዳር ውስጥም ሆነ ውጭ የምናየው ጭካኔ የዚህ አካሄድ ውጤት ነው፡፡ ግጭትን በሰከነ መንፈስ ለማብረድ አለመቻል፣ በስሜት መነዳት፣… ይህ ሁሉ የወንጀል ምንጭ ይሆናል፡፡
ትናንት እናያቸውና እንሰማቸው የነበሩ በፍቅርና በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የፈጠሯቸው ጥቃቶች “ቀላል ናቸው” ብለን ስናልፋቸው፣ እነሆ ዛሬ ወደከፋው ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የትናንቱ ጥፊ ዛሬ ወደቦክስ፣ ወደዱላ፣ ወደፈላ ውሃ፣ ወደአሲድ፣ቀጥሎም ወደ ጥይትና ቦምብ ተቀይሯል፡፡ ነገ ደግሞ ወደየት እንደሚሄድ ፈጣሪ ይወቅ፡፡ አሁኑኑ የማያዳግም እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር፡፡
እንደወንድነቴ፣ እነዚህ ሁሉ የጭካኔ ተግባራት በሙሉ እየተፈጸሙ ያሉት በወንዶች በመሆኑ አዝናለሁ፣ አፍራለሁም፡፡ በእኔ አመለካከት ”ወንድ” ማለት ትዕግሥተኛ፣ አመዛዛኝ፣ እና ምክንያታዊ የሆነ፣ ተፈጥሯዊ የአካል ጥንካሬ የበላይነቱን በተገቢው መልኩ የሚጠቀም ሰው ነው፡፡ ወንድነት የሱሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአዕምሮ ብስለት እንጂ፡፡ ከዚህ አኳያ የነገራችን መነሻ የሆነን ሰው የቀድሞ ሚስቱን ለመግደል ሲወስን ሌሎቹን የችግሩን መፍቻ መንገዶች በአዕምሮው ውስጥ ዘግቶ ነው ለማለት ያስችላል፡፡ ቀድሞ ፈራጅ ባልባል፣ ይህ ሰው የመግደል ሐሳቡን ያመነጨው ተኝቶ ሲነሳ አይመስለኝም፡፡ አስቦበት፣ መሣሪያ ገዝቶ ወይም ተውሶ፣ የሟችን መውጫ ሰዓት ጠብቆ የድርጊቱን ውጤት እያወቀ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህንን በጭካኔ የተሞላ ወንጀል ዛሬ እንደቀላል አይተን ካለፍነው ነገ ሌሎችም የግጭት መፍቻ መንገድ አድርገው እንደማይወስዱት ምንም ዋስትና የለንም፡፡
እናም ሕጉ ይጥበቅ፣ ተተኪውን ትውልድ ከዚህ መሰል አረመኔነት ለማዳን ትምህርትና ምክር በስፋት ይሰጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወንዶች ትዕግሥትን እንላበስ፣ የምር “ወንድ” እንሁን!!!