Wednesday, April 20, 2016

አንዳንድ ሐሳቦች- ስለኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ሚዲያ (ክፍል ፩)

እንደ መንደርደሪያ
ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለግል ቴሌቪዥን ፈቃድ መስጠት በመጪው ዓመት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ መናገራቸውን የሚገልጽ ዜና አነበብኩ፡፡ የታሰበው ዕውን መሆኑ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ቢሆንም፣ ሐሳቡ መነሳቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነውና አቶ ልዑልንና አዲስ አድማስን ”ቸር ወሬ ያሰማችሁ!” ልላቸው እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የግል ቴሌቪዥን መኖር ጉዳይ ላለፉት 24 ዓመታት ተደጋግሞ ሲነሳ የቆየ ነው፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በፊት በአገሪቱ የነበሩት አንድ ብሔራዊ ቴሌቪዥንና አንድ የትምህርት ቴሌቪዥን ብቻ መሆናቸው የቴሌቪዥን አገልግሎትን ውስን ይዘት ያለው እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ሐሳብን በነፃነት እና በተለያዩ መንገዶች መግለጽ በመርህና በሕግ የተረጋገጡ መብቶች መሆናቸውን ተከትሎ ከመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ በሆነው የብሮድካስት ሚዲያ ዘርፍ የኅትመት ሚዲያውን ያህል እርምጃ ያለመታየቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ ዋነኛው ጥያቄ የአማራጭ ሚዲያ መኖር ሲሆን፣ በተያያዥነትም በአሁኑ ወቅት በሥርጭት ላይ ያሉት የቴሌቪዥን ሚዲያዎች የአገልግሎት ጥራት፣ የጊዜ ርዝማኔ፣ እና የሥርጭት ተደራሽነት አብረው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የብሮድካስት ሚዲያን ለማስፋፋት የተለያዩ እርምጃዎች ባለፉት ዓመታት ተወስደዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ከመፍጠር አንስቶ የብሮድካስት ሚዲያዎች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ በሕግ ደረጃ በ1991 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. የወጡት የብሮድካስት አዋጆች ለዘርፉ መስፋፋት በመንግሥት በኩል ያለው ፈቃደኝነት ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ሲሆኑ፣ አዋጁን ተከትለው በቁጥር በርከት ያሉ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ ተቋቁመው መንቀሳቀሳቸው ለዘርፉ ማደግ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ሊታይ የሚችል እርምጃ ነው፡፡
አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው የብሮድካስት አዋጅ ቁጥር 533/1999 አንቀጽ 2(2) መሠረት የብሮድካስት አገልግሎት ማለት ”ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ፣ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት” ነው፡፡ ከዚህ ትርጉም አንፃር በአገራችን በአሁኑ ወቅት በብዛት በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ በቴሌቪዥን ዘርፍ ግን ከመንግሥታዊው ኢቢሲ፣ ከተወሰኑ የክልል ቴሌቪዥኖች እና መሠረታቸውን በውጪ አገራት አድርገው በሳተላይት ከሚሠራጩ የግል ቴሌቪዥኖች በስተቀር በቁጥርም ሆነ በጥራት በቂ የሆኑ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች የሉም፡፡
ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች እጥረትና የጥራት ውሱንነት የአገራችንን የቴሌቪዥን ተመልካች አማራጭ በማሳጣቱ የተነሳ በርካታ ሕዝብ ወደውጪ ሚዲያዎች ፊቱን እንዲያዞር ተገዷል፡፡ በተለይም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በነፃ የሚሠራጩ የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻናሎች (free-to-air TV channels) በአብዛኛው የቴሌቪዥን ተመልካቾች ዘንድ በአማራጭነት ተወስደዋል፡፡ እነዚህ ቻናሎች ደግሞ በአመዛኙ በአረብኛ ቋንቋ የሚቀርቡ በመሆናቸው ተመልካቹ በማይገባው ቋንቋ ፕሮግራሞችን ለመከታተል መገደዱ ቻናሎቹን ከመማሪያና መዝናኛነት ይልቅ የጊዜ ማሳለፊያ ብቻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች በመነሳት በአገራችን አማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ በስፋት መኖር አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ጸሐፊ ያምናል፡፡
በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጥቅምት 6 ዕትም፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለ22 የመንግሥትና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን ይገልጻል፡፡  የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለጋዜጣው እንደተናገሩት፣ በዚህ ዓመት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር ሲጠናቀቅ ከሚኖሩት 22 ቻናሎች መካከል ለእያንዳንዱ ክልልና ለኢቢሲ ቻናሎች የሚሰጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ቻናሎች ደግሞ ለግል ድርጅቶች በጨረታ ይሰጣሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው የቻናሎች ክፍፍል መሠረት፣ ሦስት ቻናሎች ለግል ብሮድካስተሮች ተመድበዋል፡፡ ቀሪዎቹ 19 ቻናሎች ደግሞ ለመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያዎች የሚሰጡ ይሆናል፡፡
ሦስት የግል ቻናሎች ካለው ፍላጎት አንፃር አነስተኛ ቢሆኑም፣ የግል ብሮድካስተሮችን ወቅታዊ አቅም ከግምት ስናስገባ ለጊዜው በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁም ነገሩ ግን ብዛታቸው ሳይሆን ጥራትና ብቃት ነው ባይ ነኝ፡፡ ልናተኩርበትም የሚገባው ይኸው የጥራትና ብቃት ጉዳይ ነው፡፡ ደጋግሜ ያነሳሁት የአማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ አስፈላጊነት መነሻው እስካሁን ያሉን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚፈለገው የጥራትና የብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው መሆኑን ስንመለከት፣ ስለእነዚህ ጉዳዮች የማሰብና የመወያየትን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ  ይመስለኛል፡፡ ይህ የጥራት ጉዳይ አሁን በሥርጭት ላይ ያሉትንም ሆነ ወደፊት ሥራ ይጀምራሉ የሚባሉትን ጣቢያዎች በእኩል የሚመለከት በመሆኑ፣ በእኔ በኩል ያሉኝን ዕይታዎችና ተያያዥ ሐሳቦች በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡


ማስታወሻ-   ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ ስድስት ወራት ያለፉት ቢሆንም፣ በጊዜው በጋዜጣ እንዲወጣ ተልኮ ሳይወጣ የቀረ  ጽሑፍ ነው፡፡  አሁን ግን ከርዕሰ-ጉዳዩ ወቅታዊነት አንፃር በዚህ ብሎግ ላይ ቀርቧል፡፡

Saturday, April 16, 2016

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ "ቃና" ወይስ ...?

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት ”ቃና” የተባለው የሳተላይት ቴሌቪዥን እያቀረበ ባለው የፕሮግራም ይዘት ላይ ”አለን” ያሉትን ሥጋትና ተቃውሞ የሚገልጽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በመግለጫው ላይ የተነሱት ሐሳቦች በሁለት ነጥቦች ተጠቃለው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነርሱም፡-
1.      የቃና ቲቪ አካሄድ የአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋል፣
2.     በቃና ቲቪ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ለባሕል ወረራ ያጋልጣሉ
የሚሉ  ናቸው፡፡
በመሠረቱ፣ እነዚህ ማኅበራት የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብና ባሕልን አስመልክቶ የተቆርቋሪነት ሥጋታቸውን መግለጻቸው ከምንም በፊትና በላይ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ነገር ግን፣  የእስከዛሬ ልምዳችንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችንን እንቅስቃሴ ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ ”የማኅበራቱ እውነተኛ ሥጋት ምንድን ነው?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም አብረው ይመጣሉ፡፡ እኔም በመግለጫውና ከመግለጫው በኋላ በተሰሙትና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተገለጹት ሐሳቦች በመነሳት አስተያየቴን ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
የሥጋቱ ምንጭ ምንድን ነው?
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራቱ በመግለጫቸው የቃና ቲቪ አካሄድ ”ያስከትላቸዋል” ያሏቸውን ”ጉዳቶች” ከላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች አንፃር በሚከተለው መልኩ አስቀምጠዋቸዋል፡፡
·         ”ጣቢያው አጭር ዕድሜ ያለውን የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችንን በማቀጨጭ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚያሰናክል በመሆኑ ፕሮግራሙን በድጋሚ ሊከልስ ይገባዋል፡፡”
·         ”በጣቢያው የሚቀርቡት የውጭ አገር ፊልሞች ንግድ-ተኮር በመሆናቸው ምንም ዓይነት ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት የላቸውም፡፡”
እነዚህ የማኅበራቱ ”ሥጋቶች” ”መነሻቸው ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ፣ በይፋ የምናገኘው መልስ ”ከዘርፉ ሕልውና ከመጨነቅና የኢትዮጵያን ባሕል ከወረራና ከመበረዝ ለመከላከል ከማሰብ” የሚል ነው፡፡ የተሸፈነውና ትክክለኛው ምላሽ ግን አሁን ያሉት የዘርፉ ተዋንያን ”የእንጀራ ገመድ መበጠስ” ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በኪነ-ጥበቡ (በፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽኖች) ዘርፍ የሚሠሩ 10‚000 ያህል ”ባለሙያዎች” አሉ (”ባለሙያዎች” የሚለውን ቃል በትዕምርተ-ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት በዕውቀት የተደገፈ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ቁጥር ይህን ያህል ደርሷል ብዬ ለማመን ስለሚከብደኝ ነው)፡፡ የእነርሱ ሥጋት ”እነዚህ ሁሉ ”ባለሙያዎች” በቃና ቲቪ አካሄድ ምክንያት ሥራ-አጥ ይሆናሉ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛውና ከባሕል ወረራ ጋር የሚገናኘው ሐሳብ የመጀመሪያውን ሐሳብ ለመደገፍና ለማኅበራቱ አቋም ጉልበት ለመስጠት የመጣ እንጂ በእውነት ማኅበራቱ ዛሬ ላይ ተቆርቁረውበት የሚያነሱት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቴን ወደፊት እመለስበታለሁ፡፡
የሥጋቶቹ የተጨባጭነት ልክ
በኪነ-ጥበብ ማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች ትክክለኛ ሥጋት መሆናቸውን ለመፈተሽ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የቴሌቪዥንና የፊልም ዘርፍ ሁኔታ መቃኘት የሚያስፈልግ  ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ቻናሎች ቁጥር (በሳተላይት ከውጭ የሚተላለፉትን ጨምሮ) ወደ 20 ገደማ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ቻናሎች መካከል ቀዳሚ የሚባሉት ብሔራዊና የክልል ቴሌቪዥኖች እንዲሁም የግል ቻናሎች ለቴሌቪዥን ድራማዎችና የአገር ውስጥ ፊልሞች ሰፊ የአየር ሰዓት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንደ ማሳያ ኢቢሲ እና ኢቢኤስን ብንወስድ፣ ኢቢሲ አምስት ድራማዎችን (አራት ሲሪያል እና አንድ ሲትኮም) ሳምንቱን በሙሉ በሁለት ቻናሎች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢቢኤስ በበኩሉ አራት ድራማዎችን (ሁለት ሲሪያል እና ሁለት ሲትኮም) ያቀርባል፡፡ በፊልም በኩልም ሁለቱም ቻናሎች ሳምንታዊ የታላቅ ፊልም (feature films) ፕሮግራሞች አሏቸው፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም ድራማዎችና ፊልሞች ከመደበኛ ቀናቸው በተጨማሪ በድጋሚ የሚቀርቡ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ከዚህ አንፃር ዛሬ ላይ በተለይ ለቴሌቪዥን ድራማዎች ቀን ወጥቶላቸዋል ማለት እንችላለን፡፡ ሚዲያዎቹም ተጨማሪ ድራማዎችን እንደሚፈልጉ እየሰማን ነውና በብዛት ደረጃ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ዕድሉ ሰፍቷል ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ”ጥራት ላይ እንዴት ናቸው?” የሚለው ይሆናል፡፡ ምናልባትም የአሁኑ የማኅበራቱ ሥጋት እውነተኛ መነሻ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፡፡
የጥራትን ጉዳይ ከይዘት ጋር አጣምሮ መመልከት የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይዘት ሐሳብን፣ መልዕክትንና አቀራረብን የሚወስን በመሆኑ፡፡ ይዘት (content) ለተደራሲው ልናቀርብ የፈለግናቸውን ጉዳዮችና የምናነሳቸውን ጥያቄዎች በአንድነት ሰብስቦ የሚይዝ ቋት እንደመሆኑ፣ የይዘት ምርጫና ውሳኔ በሚተላለፈው ሐሳብና መልዕክት ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ይዘት በሚዲያዎቹ ምርጫ የሚወሰኑ ከሆነ፣ የደራሲዎችና የሐሳብ አመንጪዎች ምናብ በሚዲያው ምርጫ፣ አለፍ ሲልም ጫና ምክንያት ሊገደብ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ቢያዳግተኝም፣ የጊዜያችን የቴሌቪዥን ድራማዎች የዚህ አካሄድ ሰለባ መሆናቸውን በተባራሪ ከምንሰማቸው ሁነቶችና እንደተመልካችም ከምናስተውላቸው የሐሳብ መሳሳቶች በመነሳት መናገር እችላለሁ፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመለከትናቸውንና እየተመለከትናቸው ያሉትን የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማዎች ከይዘትና ጥራት አንፃር ስገመግማቸው፣ የሚያነሷቸውን ርዕሰ-ጉዳዮች በአጠቃላይ ”በጣም ጥሩ” የሚል ደረጃ እሰጣቸዋለሁ፡፡ የአብዛኞቹ መነሻ ታሪክ ትኩረትን የሚስብ፣ አንዳንዴም የሚያመራምርና የሚያወያይ ነው፡፡ የሚያነሱት ጭብጥ በአብዛኛው ለኢትዮጵያዊያን ቅርብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ድራማዎቻችን ከፍተኛ የተከታታይ ቁጥር አስመዝግበዋል ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ግን፣ ድራማዎቻችን ቀላል የማይባሉ ቴክኒካዊ ግድፈቶችን የተሸከሙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ድራማዎች መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን የማያውቁ፣ ሌሎቹ በአንድ ድራማ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን አጭቀው ሁሉንም ለማሳየት የሚውተረተሩና ያልተሳካላቸው፣ ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም ደግሞ ድርሰቶቻቸውን በበቂ ጥናትና መረጃዎች ያላስደገፉ፣ በተለይም ደግሞ ሙያ-ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ የተአማኒነት ጉድለት ያለባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ በእኔ አመለካከት፣ በወረቀት ላይ ተስተካክለው ሊቀርቡ የሚችሉ እንጂ፣ አሁን በቃና ቲቪ ጉዳይ ላይ እንደሚነሳው ከገንዘብ አቅም ማነስ፣ ከግብዓቶች ውድነት፣ ወዘተ፣ ጋር የሚያያዙ አይደሉም፡፡ ይህንን እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው ባለሙያዎቻችን ናቸው እንግዲህ አዲስ አቅጣጫ ይዞ የመጣውን ሚዲያ በገና-ለገና ”ከገበያ ያስወጣናል” በሚል ሥጋት እርምጃ እንዲወሰድበት እየወተወቱ ያሉት፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጉድለቶች በጥቅሉ ያስቀመጥኩት፣ አሁን በማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች በተወሰነ ደረጃ መሠረት ያላቸው ቢሆኑም፣ ዋነኛው ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የቃና መምጣት አይደለም ለማለት ነው፡፡ በቀጣይ ይህን ሐሳቤን በዝርዝር ለማቅረብና የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማ ወቅታዊ ሁኔታ ከቃና ቲቪ አካሄድ አንፃር ለመገምገም እሞክራለሁ፤ እግረ-መንገድም ”ቃና” ያስተዋወቀውን አቀራረብ በሂሳዊ ዓይን ለመመልከት፡፡ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ምን ቢያደርግ የተሻለ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የምሰጠው አስተያየት ይኖረኛል፡፡

(ይህ ጽሑፍ በሚያዚያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡)

Tuesday, April 12, 2016

የማለዳ ትዝብቴ

ዛሬ ማለዳ በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የስፖርት ዜና ላይ ያዳመጥኩት ዜና በጣም አስገርሞኛል፡፡ ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ ሲጫወቱ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች አሉላ ግርማ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ተጫዋቹ ሕክምና እንዲደረግለት ከሜዳ መውጣት ነበረበት፣ ነገር ግን ለዚህ የሚያገለግለው ቃሬዛም ሆነ አምቡላንስ በስታዲየሙ አልነበረም፡፡ አምቡላንሱ በሥፍራው የተገኘው በሁለተኛው ግማሽ ላይ ነበር፡፡ አሉላም በዚህ ምክንያት ከሜዳ በቡድን ጓደኞቹ ተሸካሚነት ለመውጣት ተገደደ፡፡
እንዴት እግር ኳስን የመሰለ፣ ለጉዳት ሊዳርግ የሚችል አካላዊ ንክኪ ያለበት ጨዋታ ቢያንስ ያለቃሬዛ ይካሄዳል? የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ”ጉዳዩን ተመልክቼ እርምጃ እወስዳለሁ” ብሏል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሸገር ስፖርት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ኃላፊው በዚህ ጉዳይ ከአምቡላንስ አቅራቢው ተቋም በተጨማሪ የጨዋታው ኮሚሽነርም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲገልጹ፣ የኮሚሽነሩን ማንነት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ”በሰዓቱ ስብሰባ ላይ ስለነበርን ኮሚሽነሩ ማን እንደነበሩ አላወቅንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በጣም ያሳፍራል! እንዴት አንድ አወዳዳሪ አካል፣ ራሱ የመደበውን የጨዋታ ታዛቢ ማንነት ”አላውቅም” ይላል? መቼም የጨዋታ መረጃ በጽሑፍ ሳይመዘገብ አይቀርም፡፡ ”እነ እከሌ ዳኞች፣ እከሌ ኮሚሽነር” ብሎ ለሁሉም ወገን የሚያሳውቅ ይመስለኛል፡፡ እና፣ ፋይል አገላብጦ እንኳን ኮሚሽነሩ እገሌ ነው ማለት ይቸግራል? እንዲህ ዓይነቱ ቀልድ የሚያበቃው መቼ ይሆን?!

Friday, February 12, 2016

Art vs Business: Probable Cause for the Oscars Controversy?

The recently-reopened issue of race and color in the United States (though hasn’t been closed in the first place) has taken a new course, and continues on a new battlefield. The new destination: Hollywood!
It all began on January 16, when actress Jada Pinkett-Smith expressed outrage over the nominations of this year’s Academy Awards, which were announced on January 14. She tweeted, “At the Oscars … people of color are always welcomed to give out awards … even entertain, but we are rarely recognized for our artistic accomplishments. Should people of color refrain from participating all together?”
Since then, big names, from Spike Lee to Whoopi Goldberg, from Janet Hubert to Tyrese, from Helen Mirren to George Clooney…, all weighed in on the issue, adding their voices both for and against the apparent “Boycott Oscars” movement. Even Donald Trump, the GOP presidential hopeful, spoke about it. This unprecedented wave of anger from the “colored population” has finally forced Academy president, Cheryl Boone Isaacs, to officially announce on January 19, of the changes that the AMPAS is planning to do in the future with the aim of ensuring diversity.
My take on the issue, well, my first response to the news was “What’s new about it?” It’s no wonder the “colored” people have received less attention in the US, regardless of their achievements in their respective fields, and the film industry is of no exception. What triggered this discourse now is the fact that no colored nominees are included for the second consecutive year. And with the recent cases of abuses on the black people of America, I believe some folks have become sensitive over this issue.
Then I thought, “Why did Mrs. Smith get so upset about it?” Well, it’s obvious she might get upset over the fact that her husband, Will Smith, who starred in the medical biopic “Concussion,” wasn’t in the nomination for “Actor in a Leading Role” category. I, for one, agree that Will should get nominated for his performance in the film, since his acting skills are truly convincing. But, the Academy had its say on it.
After watching “Concussion” earlier this week, however, I feel that the Academy’s snub of the film has got nothing to do with artistic appraisals. Rather, I've got a hunch it’s more of a “corporate influence.” Will’s character, Dr. Bennett Omalu, a Nigerian-American physician [and more], was brave enough to expose the effects of head injuries inflicted in American Football games. His findings on Chronic Traumatic Encephalopathy (CTE) have sparked anger at the corridors of the National Football League (NFL) and loyal fans were furious at him. He was literally stoned for saying “Football killed the players!” It was seen as a defying act to “crucify” America’s greatest game. Almost no one was willing to listen to him until 2009, when the NFL finally forced to acknowledge his findings.
The NFL clubs are owned by billionaires who’ve got long arms in business. And it wouldn’t be somewhat silly for one to suspect they’ve got something to do in “convincing the Academy members not to give their nods” to the film, in order to keep their interest. Even if they don’t, I suspect many die-hard fans of American football (I don’t understand why they call it “football,” when the players use their feet on the ball only on penalties) had a hand on it. So I believe, “Business takes the upper hand on Art!”


Citations: Oscars 2016 Boycott: A Timeline of the Controversy, US Weekly, January 20, 2016

Tuesday, January 26, 2016

ከማፍረስ እንጀምር!

መቼም ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ብዙ ተብሏል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የስፖርት ተከታታይ አገራችን ስሟን በክብር ከሚያስጠራት አትሌቲክስ በበለጠ ለእግር ኳስ ከፍ ያለ ፍቅር ቢኖረውም፣ በውጤታማነት ግን አርኪ የሆነ ነገር ጠብ ሳይልለት ዓመታትን ገፍቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የስፖርቱ ደረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በኢንተርናሽናል ደረጃ ከዓመት ዓመት እየወረደ ብቻ ሳይሆን እየወደቀ መሄዱ ለስፖርቱ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን አፍቃሪና ተከታታይ ላልሆነው ሕዝብ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሐቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እኛም በአገራችን እግር ኳስ ውጤት-አልባነት መናደዳችን እየቀረ መሳለቅ ከጀመርን ቆየን፡፡
ዘንድሮም ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ትናንት ማምሻውን በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ከሚገኘው የቻን ውድድር በጊዜ ተሰናብተናል፡፡ ያው የተለመደ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ከሚዲያዎች በስተቀር ማንም ምንም ሲል አልሰማሁም፡፡ ሚዲያዎቹም ቢሆኑ ስለችግሩ ብዙ ስላሉበትና አዲስ ነገር ስላልመጣ እንደቀደመው ጊዜ ብዙ ነገር አልተናገሩም፡፡ ይልቁንስ፣ ”ካለፈው የቻን ተሳትፏችን የተሻለው ነገር አንድ ጎልና አንድ ነጥብ ማግኘታችን ነው” የሚል ማጽናኛ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ አይፈረድባቸውም! ማለት የሚችሉት ይህንኑ ብቻ ስለሆነ፡፡
በሚዲያዎቹ ከተነገረው ጥቂት ነገር ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዐቢይ ነጥብ ”ከዚህ በኋላስ ምን ይደረግ?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ያዳመጥኳቸው ሁለት የኤፍ.ኤም ሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞች ስለዚህ ጥያቄ ከሰጧቸው ምላሾች ውስጥ አንደኛውና እኔም በግሌ የተስማማሁበት ”ምን መደረግ እንዳለበት ብዙ ተነግሯል፣ ከዚህ በኋላ ይህንን ደጋግሞ ማንሳት አሰልቺ ነው” የሚለውን ነበር፡፡ እውነት ነው! ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ስለዚህ ጉዳይ ስንቴ አወራን? ስንቴ ተናደድን? ስንቴ ተከራከርን? በጣም ብዙ ጊዜ! ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡
የፕሮግራሞቹ አቅራቢዎች ይህንን ቢሉም፣ ”አሰልቺ ነው” በማለት ብቻ ነገሩን አልተውትም፡፡ ግዴታቸው ነውና ከዚህ በኋላም ”ቢሆን ጥሩ ነው” ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተዋል፡፡ እኔ የወደድኩት ሐሳብ በብሥራት ኤፍ.ኤም 101.1 የ”ብሥራት ስፖርት” አዘጋጁ መንሱር አብዱልቀኒ ያቀረበውን ሐሳብ ነው፡፡ የመንሱር ሐሳብ በጥቅሉ ”ብዙውን ጊዜ በታዳጊዎች ላይ ስለመሥራትና ለውጡን ከታች ስለመጀመር ተወርቷል፣ ይህም ለሰሚው አሰልቺ ሆኗል፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ለውጡን ከላይ ስለመጀመር እናስብ” የሚል ነበር፡፡
ይህ በእውነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኖቻችንና ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል መድረኮችም ሆነ በውስጥ ውድድሮች አንገት አስደፊ ውጤት ባስመዘገቡ ቁጥር የሚሰጠው ምክንያት ”የተጫዋቾቹ የአካል ብቃት ዝቅተኛ መሆን፣ የአየሩ መክበድ፣ የዳኛ ውሳኔ፣ የመስተንግዶ ጥሩ አለመሆን፣ የአሰልጣኙ የአሰለጣጠን መንገድ፣” ወዘተ ሲባል ነው የምናየውና የምንሰማው፡፡ የስፖርቱ አመራርስ? ስፖርቱ ዓለም በደረሰበት የሥልጠናና የውድድር ደረጃ እንዲካሄድ የሚጠበቅበትን ሥራ ያልሠራው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ለምን ዝም ይባላል?
በእርግጥ በቅርቡ ሚዲያዎቻችንም ሆነ ሌሎች የስፖርቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ለውጤት መጥፋት ፌዴሬሽኑን ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ወቀሳው ጠንከር ብሎና ቁርጠኛ የመፍትሄ ሐሳቦችን አዝሎ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ወቀሳው ጠንከር ይበል ስል ግለሰብ የፌዴሬሽን አመራሮችን መውቀስ ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሥርዓቱንና አሠራሩን ”ትክክል አይደለም፣ ኋላ-ቀር ነው ” ብለን ማውገዝና እንዲቀየር መጠየቅ አለብን እያልኩ ነው፡፡
በእኔ እምነት የእግር ኳሱም ሆነ የአጠቃላዩ ስፖርት ውጤት-አልባነት መነሻ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አደረጃጀትና አሠራር አለመኖር ነው፡፡ የስፖርት ፌዴሬሽኖቻችን በሙሉ በአማተር አገልጋዮች የሚመራ ነው፡፡ እነዚህ አማተር አገልጋዮች ደግሞ አብዛኛው ጊዜያቸውን በመደበኛ ሥራቸው ላይ የሚያውሉና የስፖርቱን ውሎና አዳር በሙሉ ትኩረት የሚከታተሉ አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ለስፖርቱ ባላቸው ፍቅር ብቻ የሚሠሩ እንጂ የስፖርቱ ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው፣ በስፖርቱ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ ከተመልካችነት በዘለለ ያልተሳተፉ ስለሆኑ ስፖርቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ የሚሳናቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ዛሬ፣ ስፖርት ሳይንስ በሆነበት ዘመን አገራችንን ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር አያስችሉም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህም ተቋማዊ አደረጃጀትና ለውጥ በፍጥነት ያስፈልገናል፡፡
ምን ዓይነት ለውጥ? የአመራር ለውጥ? የአሰልጣኝ ለውጥ? የተጫዋች ለውጥ? የእነዚህ ሁሉ ለውጥ ውጤት አያመጣም፡፡ የሚፈለገው የሥርዓት (system) ለውጥ ነው፡፡ ሰዎችን በመቀያየር ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ሰዎቹ ሥራቸውን በዕውቀትና በነፃነት መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሥርዓት፣ አቅም ያላቸው ባለድርሻዎች ተለምነው ሳይሆን ለምነው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የሚያበረታታ ሥርዓት፣ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ እምነት ሊጣልበት የሚችል ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት ስፖርት በዕውቀት እንጂ በፍቅርና በወኔ ብቻ የማይመራበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የስፖርቱ አመራር የዕለት ተዕለት ሥራቸው የሆነ ባለሙያዎች በደመወዝተኝነት የሚሠሩት ሥራ መሆን አለበት፡፡ በቀላል ቋንቋ ስፖርታችን ፕሮፌሽናል አመራር ያስፈልገዋል፡፡
”ፕሮፌሽናል አመራር ያስፈልገናል” ሲባል አሁን ያለው አማተር አመራርና አሠራር መወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ አማተሪዝም ይብቃን! አማተሪዝም በአንድ ወቅድ ጠቅሞን ሊሆን ይችላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ግን አይሠራም፡፡ አማተሮች ስፖርቱን እስከመሩ ድረስ በስፖርቱ መንደር ሰላም አይሰፍንም፡፡ ምክንያቱም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በስፖርታዊ ቋንቋ መነጋገር እስካልቻሉ ድረስ ውዝግብ፣ ጭቅጭቅ፣ ጥቅም ፍለጋ፣ ሙስና፣ ወዘተ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ (ነፍሱን ይማረውና) ብዙ ጊዜ ይል እንደነበረው ”በስፖርት ቋንቋ መነጋገር የሚችሉ አመራሮች ወደስፖርቱ አምባ መምጣት አለባቸው፡፡”
ይህንን ለማድረግ ”ከምን ይጀመር?” ከተባለ የኔ መልስ ”ከማፍረስ ” የሚል ነው፡፡ ”ማፍረስ” ሲባል አሉታዊ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ አሮጌ ቤታችንን ባለበት ቦታ ላይ በአዲስ ቤት ለመተካት ካሰብን ያለን አማራጭ አሮጌውን ቤት ማፍረስ ብቻ ነው፡፡ እናም፣ ዘመናትን ያስቆጠረው፣ አሮጌው የአማተር የስፖርት ሥርዓት፣ መፍረስ አለበት፡፡ አሮጌውን አማተሪዝምን አፍርሰን፣ አዲሱን ፕሮፌሽናሊዝምን እንገንባ፡፡ ፌዴሬሽኖቻችንን እናፍርስ፣ አፍርሰንም በፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ ላይ እንገንባቸው፡፡ ያኔ፣ ጊዜው ቢረዝምም፣ ውጤታማ እንደምንሆንበት በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡ እናም ከማፍረስ እንጀምር!



Sunday, November 15, 2015

ሚዛናዊነት ሆይ! ከወዴት አለህ?

ባለፈው ዓርብ ምሽት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሦስት ሥፍራዎች በተፈጸመው የተቀናጀ የሽብር ጥቃት እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት የ129 ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ 352 ሰዎች መቁሰላቸው የሰሞኑ ዐቢይ ዜና ሆኗል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት መላውን ዓለም አስደንግጧል፣ አሳዝኗልም፡፡ ጥቃቱን በማውገዝ የዓለም ማኅበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ከጥቃቱ ሰለባዎችና ከፈረንሳይ ጎን መቆሙን እየገለጸ ይገኛል፡፡ የዚህ አካል በመሆንም ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ የገጽ መለያ ፎቶዋቸውን (profile picture) በፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በመሸፈን ሐዘናቸውን የሚገልጹበትን ዘዴ ከትናንት ጀምሮ ይፋ አድርጓል፡፡
በመሠረቱ ሽብርተኝነት በየትኛውም መነሾ ይምጣ፣ ምንም ዓይነት አመክንዮ ይሰጠው፣ ሊወገዝ የሚገባው እኩይ ድርጊት ነው፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚፈጸም የሽብር ድርጊት ሐዘኑና ሕመሙ የመላው ዓለም መሆኑ አይካድም፡፡ ከዚህ አንጻር ፌስቡክም ሆነ ሌሎች አካላት የፓሪሱን የሽብር ጥቃት ማውገዛቸውና ለተጎጂዎች ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸው የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህ ሽብርተኝነትን የማውገዝ እንቅስቃሴ ”ለሁሉም በእኩል የሚደረግ ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄ፣ ብዙ የሚያነጋግር ይመስለኛል፡፡
በዘመናችን በርካታ አገራት የሽብር ጥቃት ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ዓይነቱ ቢለያይም፣ በየአገራቱ በሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች የንፁሃን ሕይወት መጥፋቱ ፣ በተለይ በዚህ ወቅት፣ በጣም እየበዛ መጥቷል፡፡  ከላይ እንደገለጽኩት፣ ሽብርተኝነት በየትኛውም መለኪያ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ከአገር አገር የሚለያይ ደረጃ እየወጣለት ለአንደኛው አገር ማልቀስ፣ ለሌላኛው ደግሞ ጀርባ መስጠት አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሽብርተኝነት፣ የትም ሆነ የት፣ ሽብርተኝነት ነውና፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት በግብጽ የሲናይ በረሃ ላይ በአየር ላይ ፈንድቶ የተከሰከሰው የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን የአደጋ መነሾ በአውሮፕላኑ ውስጥ በሻንጣ ተደብቆ የገባ ቦንብ መሆኑ ተገልጾአል፡፡ በዚህም መነሻነት አውሮፕላኑ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንደሆነ በስፋት ታምኗል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ዘመን የዓለማችን ቁጥር አንድ አሸባሪ የሆነው አይሲል እና የግብጽ አጋሩ አውሮፕላኑን ማጋየታቸውን በይፋ ገልፀው ኃላፊነቱን ወስደዋል፡፡ በዚህ ጥቃት 224 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ይህን ተከትሎ ግን ፌስቡክም ሆነ ሌሎች፣ እንዲሁም መላው ዓለም፣ ለፈረንሳይ ያዘኑትን ሐዘን ያህል ለሩሲያ ሐዘናቸውን አልገለጹም፡፡ በተለይ ፌስቡክ፣ ተጠቃሚዎቹ ፎቶዋቸውን በሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት እንዲሸፍኑ ዕድሉን አልሰጠም፡፡ ለምን?
ይህን ጥያቄ የምጠይቀው ምክንያቱ የፖለቲካ ጎራ አሰላለፍ ልዩነት መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ይልቁን፣ ምዕራባዊያን የሐዘን መግለጫ የኢንተርኔት ገጽ ሲያዘጋጁልን፣ የሐዘናቸው ሚዛን-አልባነት ቢከነክነኝ ያነሳሁት ጥያቄ ነው፡፡ ከፈረንሳይ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿን ያጣችውን ሩሲያን ”እግዜር ያጥናሽ” የምንልበት ዕድል ያልሰጠን ፌስቡክ ለፈረንሳይ ሐዘን፣ እንደሰፈር ዕድር ”ድንኳን ተካይ፣ ንፍሮ ቀቃይ” ልሁን ማለቱ በበኩሌ ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ እንዲህ ያለው መንታ ሚዛን (double standard) የዓለማችንን ዋነኛ ስጋት ምክንያታዊ በሆነ ዕይታ እንዳናወግዝና እንዳንዋጋ እንቅፋት ይሆንብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያንም፣ የሐዘኑ ተካፋይ ብንሆንም፣ እኛም በአይሲል ወገኖቻችንን በአሰቃቂ ሁኔታ ባጣን ጊዜ ሐዘናችንን ብቻችንን እንዳዘንን በማስታወስ፣ ይህንን የፌስቡክ የሐዘን መግለጫ መንገድ ተጠቅመን ሐዘናቸንን ስንገልጽ፣ ”ሚዛናዊነት ሆይ! ከወዴት አለህ?” ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ 


Monday, October 12, 2015

ማሳሰቢያ፤ ለባለሙያዎች

ሰሞኑን የአውሮፓ የፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በጁቬንቱስ ክለብ፣ በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ፣ በጎተ ኢንስትቲዩት፣ እና በብሪትሽ ካውንስል ከአሥራ ሰባት አገራት የተውጣጡ ፊልሞች ለዕይታ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከሃያ አምስት ዓመታት ያላነሰ ጊዜን ያስቆጠረው ይህ ፌስቲቫል ከዓመት ዓመት የተመልካች ብዛቱ እየጨመረ ያለና ከከተማችን ዐበይት ጥበባዊ ክንውኖች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እኔም ከአሥር ዓመታት በላይ በዘለቀው የዚህ ፌስቲቫል ታዳሚነቴ ብዙ ነገሮችን ለመማር የቻልኩበትና የምዝናናበትም መድረክ በመሆኑ በየዓመቱ በካሌንደሬ ውስጥ በቋሚነት ከምመዘግባቸው ፕሮግራሞች መካከል አንደኛው ነው፡፡ ዘንድሮም አብዛኞቹን ፊልሞች ተመልክቻለሁ፣ በዕውቀትም ሆነ በመዝናናት ጥሩ ጥቅም እያገኘሁበት እገኛለሁ፡፡
አሁን ላነሳው የፈለግሁት ሐሳብ በቀጥታ ፌስቲቫሉን የሚመለከት አይደለም፡፡ ሐሳቤ በአጠቃላይ በከተማችን የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ ያለንን ተሳትፎ፣ በተለይም በመድረኮቹ የሚነሳው ሐሳብ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በመድረኮቹ ላይ ለመገኘት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚጠይቅ ነው፡፡
ይህንን ሐሳብ ከላይ በጠቀስኩት የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል አብሮኝ ከሚታደመውና ከፌስቲቫሉ ጋር ካስተዋወቀኝ ወዳጄ ጋር ስንወያይበት ነበር፡፡ አምና በተካሄደው መሰል ዝግጅት ላይ ካገኘሁት አንድ የፊልም ባለሙያ ጋርም በሰፊው ተነጋግረንበት ነበር፡፡ ከወዳጄ ጋር በዘንድሮው ፌስቲቫል ላይ እስከትናንትናው ምሽት ድረስ ያየናቸው የፊልምና የትወና ባለሙያዎች ሦስት ብቻ ናቸው (በአደባባይ  የማይታወቁ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳንረሳ)፡፡ በተለያዩ የቴአትር፣ የቴሌቪዥን፣ እና የፊልም ሥራዎች ላይ የምናውቃቸው አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች ግን (ቢያንስ እኔ በተገኘሁባቸው ቀናት) የሉም፡፡ እንደውም እኔ ሳስበው፣ እነዚህ ባለሙያዎች ስለፌስቲቫሉ መኖር ጨርሰው የሚያውቁም  አይመስለኝም፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ነገር በሌሎችም ዘርፎች ላይ ብዙ ጊዜ ይገጥመኛል፡፡ እኔ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ጊዜዬ አንስቶ ባመቸኝ ጊዜ ሁሉ የማልገኝበት መድረክ የለም፤ የፓናል ውይይት፣ ሌክቸር፣ ኤግዚቢሽን፣ የመጽሐፍ ምረቃ፣ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ወዘተ፡፡ ርዕሰ-ጉዳዩ ተመለከተኝም አልተመለከተኝ፣ ዘርፌ ሆነ አልሆነ መገኘት ከቻልኩና ፍላጎቴ ከሆነ እታደማለሁ፡፡ ታዲያ የሚገርመኝ ነገር፣ የምገኝበት መድረክ ርዕሰ-ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከታቸው (ሥራቸው ከሆኑት) ሰዎች መካከል በመድረኩ ላይ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩት መሆናቸው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዘርፋቸው ተተኪዎችን ማፍራት እንጀራቸው የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን [አብዛኛዎቹ] አይገኙም፡፡
ባለሙያዎቹ በእነዚህ መድረኮች ስላለመገኘታቸው ቢጠየቁ የሚሰጧቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አንዳንዶቹ መረጃ ባለማግኘት፣ ሌሎቹ ”ቢዚ በመሆን…፣”  የቀሩትም በሌሎች ምክንያቶች ”መገኘት አልቻልንም” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ”ቢዚ” መሆን (በተለይ ማታ ለሚያስተምሩ መምህራን) ልቀበለው የምችለው ምክንያት ቢሆንም፣ ሌሎቹ ምክንያቶች ግን አያሳምኑኝም፡፡ ለምን ቢባል፣ መረጃ አለማግኘትም ሆነ መሰል ሰበቦች ለእኔ መነሻቸው ”ስንፍና” ስለሆነ፡፡
አንድ የተማረ ሰው ሙያውን አስመልክቶ ስለሚደረግ ስብሰባ፣ ውይይት፣ ወይም መሰል ክንውን ለማወቅ መረጃው ቢሮው ወይም ቤቱ ድረስ እስኪመጣለት መጠበቅ የለበትም፡፡ ”ምን አዲስ ነገር አለ?” ብሎ መጠየቅ፣ ሚዲያ መከታተል፣ በተለይም ደግሞ በዚህ የኢንተርኔት ዘመን መረጃውን ጎልጉሎ ማውጣት በቀላሉ ሊያደርጋቸው የሚችሉ ነገሮች ይመስሉኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀለም-ቀመስ የሆነ ሰው ራሱን በተማረው ነገር ብቻ አጥሮ መቀመጥ አይገባውም ባይ ነኝ፡፡ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች እርስ በርስ ሊደጋገፉ ይችላሉ፣ በትምህርት ቤት ከምናገኘው ሙያዊ ዕውቀት በተጨማሪ በውይይቶች የምናገኛቸው በርካታ ጠቃሚ ዕውቀቶችና መረጃዎች አሉ፣ ከእኛ ዕውቀትና ሙያ ውጭ ያሉ ሌሎች ዘርፎች አስደሳችና አመራማሪ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሌሎችም ብዙ ጠቀሜታዎች ከእነዚህ መድረኮች ይገኛሉ፡፡ ደግሞም እነዚህ መድረኮች ከሥራ በኋላ ማምሻውን ለድራፍት የምናወጣውን ወጪ የግማሹን ግማሽ እንኳን የማያስወጡ (በአብዛኛው ከ12 ሰዓት በኋላ የሚካሄዱና ከክፍያ ነፃ) በመሆናቸው ብዙ የምናተርፍባቸው ዕድሎች እንደሆኑም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ሁሉ ግን ዋናው ፍላጎት ይመስለኛል፡፡ ለማወቅ የሚኖር ፍላጎት፣ ሁሉን አቀፍ ዕይታን ለማዳበር የሚኖር ፍላጎት፣ ጤናማ የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ለማግኘት የሚኖር ፍላጎት፡፡ በፍላጎት ብቻ ትምህርት ቤት ሳይገቡ ብዙ የሚያውቁ ሰዎች አንደኛው የዕውቀታቸው ምንጭ ዕውቀት የሚገኝባቸውን ቦታዎች አሳድደው በማግኘት መሳተፋቸው ነው፡፡ መማር የቻልን ሰዎች ደግሞ የበለጠው ዕድል በእጃችን ነውና ብንጠቀምበት ትርፋችን የበዛ ይሆናል፡፡