Saturday, October 27, 2018

ቶም ከርክማን እና ዐቢይ አሕመድ


እ.ኤ.አ. በ2016 በአሜሪካው   የኤቢሲ  ቴሌቪዥን  አማካይነት ለዕይታ መብቃት የጀመረው “Designated  Survivor” ተከታታይ ድራማ፣ የአሜሪካን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ድብቅ ሴራዎችን ያሳየ ነው፡፡ በዴቪድ  ጉገንሃይም የተፈጠረውና “24” በተሰኘው የፎክስ ቴሌቪዥን ተወዳጅ ድራማ ላይ “ጃክ ባወር” የተባለውን መሪ ገጸ-ባሕርይ ሲጫወት በምናውቀው ካናዳዊው ተዋናይ ኪፈር ሱዘርላንድ መሪ ተዋናይነት የሚቀርበው ይህ ድራማ፣ ከሳምንት ሳምንት በማይጠበቁ ክስተቶቹ የበርካታ ተመልካቾችን ቀልብ እንደሳበ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተጉዟል፡፡ በዚህ ድራማ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ትርክት በአንዳንድ መልኮቹ ከአሁኑ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አይቼበታለሁ፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡
ቶማስ ከርክማን የተባሉ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለዝቅተኛ ደረጃ  የካቢኔ አባል፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለኮንግረሱና ለሴኔቱ የጋራ ስብሰባ ንግግር የሚያደርጉበት “State of the Union” ተብሎ የሚታወቀው  ዓመታዊ መንግሥታዊ ሁነት በሚከናወንበት ዕለት ማለዳ ላይ፣ ሳይጠበቅ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ከካቢኔ አባልነታቸው ይባረራሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ በልዩ ጥበቃ ክፍሉ (Secret Service) አማካይነት እዚያው ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባለ ምሥጢራዊ ሥፍራ ከባለቤታቸው ጋር እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡ ምሽት ላይ ፕሬዚዳንቱ በካፒቶል ሂል (የምክር ቤቶቹ መቀመጫ) ዓመታዊ ንግግራቸውን በማድረግ ላይ እያሉ በከባድ ፈንጂ ሕንፃው ተመትቶ ከነሙሉ ካቢኔያቸው ተገደሉ፡፡ በሕንፃው ውስጥ ንግግሩን ሲከታተሉ የነበሩ የኮንግረስ አባላት፣ ሴናተሮች፣ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም በፍንዳታው አለቁ፡፡
በምሥጢራዊ ቦታ ተቀምጠው ንግግሩን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ የነበሩት ከርክማን እና ባለቤታቸው፣ ከፍንዳታው በኋላ በፍጥነት ወደ ኋይት ሐውስ ተወሰዱ፡፡ እንደደረሱም ከርክማን ቃለ-መሐላ ፈጽመው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
ከዚህ በኋላ ባለው የድራማው ክፍል ፕሬዚዳንት ከርክማን ከጥቃቱ ማግሥት ባለመረጋጋትና በሥጋት ውስጥ ያለችውን ዩናይትድ ስቴትስን ለማረጋጋት፣ አንድነትና ሰላሟን ለማስጠበቅ፣ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያስደነገጠውን የሽብር ጥቃት አድራሽ ለማግኘት፣ እንዲሁም አዲስ መንግሥት ለማቋቋም የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ትግልና የሚያልፉባቸውን አስቸጋሪ እንዲሁም አደገኛ መንገዶች እንመለከታለን፡፡
ድራማው ልብ-ወለድ ይሁን እንጂ መነሻው እውነታን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በተለይም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በሁለቱ ታላላቅ ጎራዎች (በካፒታሊዝም እና ሶሻሊዝም) መካከል በነበረው ፍጥጫ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ በሚያይበት ዘመን፣ አሜሪካ በመንግሥታዊ አስተዳደሯ ላይ ጥቃት ቢደርስ ተተኪ መሪ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ በማመን የጀመረችው ተጠባባቂ መሪ   (Designated Survivor) የማስቀመጥ ሐሳብ ለታሪኩ ነባራዊ መነሻ ሆኗል፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በዚህ የፖለቲካ ድራማ ታሪክ እና በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ መመሳሰሎችን ተመልክቻለሁ፡፡  በተመሳስሎዎቹ ውስጥ ልዩነቶችም ይታያሉ፤ እነዚህን መመሳሰሎች (ከነልዩነታቸው) ከወቅቱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ውጣ-ውረድ ጋር አያይዞ መመልከቱ ላለንበት አስቸጋሪ ወቅት የመፍትሄ መንገዶችን ለማሰብ መነሻ እንደሚሆን በማሰብ የተወሰኑትን ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቤያቸዋለሁ፡፡
·         የአሜሪካው የ “Designated Survivor “ፕሬዚዳንት ቶማስ (ቶም) ከርክማን እና የኢትዮጵያው የአሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀውስ ጊዜ መሪዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ሰዎች፣ አገሮቻቸው በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሲገቡ የመሪነቱን ወንበር በምርጫ ሳይሆን በባለአደራነት (እስከቀጣዩ ምርጫ ድረስ) ይዘዋል፡፡ እርግጥ፣ ፕሬዚዳንት ከርክማን፣ በድንገተኛ አጋጣሚ፣ ሳይዘጋጁ ነው ፕሬዚዳንት የሆኑት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን፣ የቀድሞው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን አምባሳደር ካሣ ከበደ ለግዮን መጽሔት “ራሳቸው ነገሩኝ” ብለው እንደገለጹት፣ ለቦታው ሲዘጋጁበት ቆይተው ነው፣ ቀዳሚያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣን ሲለቁ ወንበሩን የያዙት፡፡
·         ሁለቱም መሪዎች ቤተ-መንግሥት ሲገቡ ቀዳሚ ሥራቸው አገር ማረጋጋት ነበር፡፡ አገር ለማረጋጋት ሁለቱም የተጠቀሙት በመሪነት ያደረጓቸውን የመጀመሪያ ንግግሮቻቸውን ነው፡፡  በንግግሮቻቸውም መሪዎቹ አገሮቻቸው ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታ በመግለጽ፣ ችግሮች ቢኖሩም በጽናት እንደሚወጧቸው ለሕዝቦቻቸው ቃል  ገብተዋል፡፡  በውጤት ደረጃ ግን የሁለቱ መሪዎች ንግግሮች ያመጧቸው ውጤቶች ይለያያሉ፡፡ የፕሬዚዳንት ከርክማን ንግግር፣ ከዚያ ጊዜ በፊት  አይተውት በማያውቁት ምስቅልቅል ውስጥ ለገቡት አሜሪካዊያን ብዙም ማጽናኛ አልሰጠም፣ በአንጻሩ፣ ለ27 ዓመታት አንድ ዓይነት ሥርዓት፣ ፖለቲካዊ መሥመር እና ተመሳሳይ የፖለቲካ ቋንቋ ሲያይና ሲሰማ ለኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር የተስፋ እና የለውጥ ብልጭታ ያሳየ ነበር፡፡
·         ፕሬዚዳንት ከርክማን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከንግግሮቻቸው በኋላ ያደረጉት፣ ችግር ወዳለባቸው ቦታዎች መሄድና ጉብኝት ማድረግ ነበር፡፡ እዚህ ላይ፣  ሁለቱ መሪዎች በጉብኝታቸው ባከናወኑት ተግባር ይለያያሉ፤ ፕሬዚዳንት ከርክማን፣ በፈንጂ በወደመው “ካፒቶል ሂል” በመገኘት በነፍስ-አድንና በምርመራ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችን አበረታተዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደግሞ ጅግጅጋ ከተማ በመገኘት በእርስ-በርስ ግጭት ውስጥ የነበሩትን የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች አንድ ላይ አስቀምጠው ከሶማሌ የሕዝብ ተወካዮች ጋር በመነጋገር የማረጋጋት ሥራ ሠርተዋል፡፡
·         ሁለቱም መሪዎች ሥራቸውን ሲጀምሩ ጀምሮ ተቃዋሚ አላጣቸውም፣ በዚህም ብዙ ተፈትነዋል፡፡ ከርክማን፣ “ለፕሬዚዳንትነት ብቁ አይደሉም” የሚሉ ሰዎች ተነስተውባቸዋል፣ በዋናነት፣ ለደረሰው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ያላቸውን ቆራጥነት የተጠራጠሩ ሰዎች ከአስተዳደራቸው ውስጥ ነበሩ (በተለይም የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ሊቀመንበር በሆኑት ጄኔራል) ፡፡  ዶ/ር ዐቢይም፣ ባይበዛም፣ በአመራራቸው ላይ ከጅምሩ አንስቶ ጥርጣሬ ያደረባቸው ጥቂት ሰዎች ሥጋታቸውን ሲገልጹባቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል፣ ለሁለቱም መሪዎች የማይታዘዙ ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ የአሜሪካውን መሪ አንዳንድ የክፍለ-ሀገር ገዢዎችና ወታደራዊ አዛዦች፣ የኢትዮጵያውንም በተመሳሳይ የአንዳንድ ክልሎች አመራሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች  ፈትነዋቸዋል፡፡
·         ከርክማን እና ዐቢይ ጠላት የበዛባቸው ናቸው፤ ሁለቱም በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል (ዶ/ር ዐቢይ በመስቀል አደባባይ የተደረገባቸው ሙከራ በይፋ የሚታወቀው ይሁን እንጂ፣ ሌሎች ሴራዎችም እንደነበሩና እንዳሉ በቅርቡ ተናግረዋል)፡፡ ሁለቱን መሪዎች ከሥልጣን ለማውረድም የተለያዩ ሴራዎች ተጠንስሰውባቸዋል፡፡
·         የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የመሪዎቻቸውን ደህንነት በመከታተል እና ተስፋ በማድረግ በኩል ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ከርክማን የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ያሉበት ሁኔታ ይፋ እስኪሆን ድረስ አሜሪካዊያን በጭንቀት ተጠባብቀዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በተለይ ከአሜሪካ ጉብኝታቸው ከተመለሱ በኋላ ለቀናት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው በመቆየታቸውና በርካታ ሐሜቶችም በዚህ ምክንያት በመወራታቸው፣ በሚዲያ እስከሚቀርቡ ድረስ ኢትዮጵያዊያን በጭንቀትና በሥጋት ጠብቀዋል፡፡ በመጨረሻም መሪዎቹ ለሕዝብ ሲታዩ የሕዝቦቹ እፎይታ ተመሳሳይ ነበር፡፡
እነዚህን የተመሳሳይነት ነጥቦች ስዘረዝር፣ አንባቢያን “ያኛው ልብ-ወለድ፣ ይሄኛው እውነት፡፡ ምን ያገናኛቸዋል?” ብለው እንደሚጠይቁ እገምታለሁ፡፡ ትክክል ነው፣ ሁለቱ በዚህ ይለያያሉ፡፡ ዋናው ነጥብ ግን በተለይ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን እንማራለን?” የሚለው ነው፡፡
እኔን ጨምሮ፣ ኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው “ታጋሽ” እንደሆንን እንናገራለን፣ ነገር ግን፣ በእኔ ትዝብት፣ አብዛኞቻችን ትንሽ ተስፋ ስናይ (ወይም ያየን ሲመስለን)፣ የተገባው ቃል ሁሉ በአንድ ጀንበር ዕውን የሚሆን ይመስለናል፡፡ ስለሆነም፣ የተባለው ነገር ሲዘገይብን ቶሎ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይ እንደአሁኑ ዓይነት በችግር የተሞላ ጊዜ ላይ ስንደርስ፣  ችግሮቹን ለመፍታት በሚወሰዱ እርምጃዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በመመልከት፣ እርምጃ ወሳጁ አካል (መንግሥት) ሆን ብሎ እንደሚያደርገው አስበን እንደመድማለን፡፡ ወይም ደግሞ፣ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ጊዜ ከወሰደ፣ ለምን ጊዜ እንደወሰደበት ከመመርመር ይልቅ፣ መንግሥትን በዳተኝነት ለመውቀስ እንቸኩላለን፡፡ በ”Designated Survivor” ላይ የምንመለከተው የፖለቲካ ኮሪደሮቹ ውይይት፣ ክርክር፣ ጭቅጭቅ እና ፍትጊያ፣ በደንብ ካየነው፣ አገር መምራት ምን ያህል ከባድ ሥራ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ ይህንን ድራማ ስንመለከት፣ የአገራችንን ሁኔታ በድራማው ውስጥ ካለው ጡዘት ጋር እያዛመድን ብንመለከተው፣ አስተሳሰባችንን በተሻለ ለመቅረጽና እንደዜጋም የበኩላችንን ትብብር እንድናደርግ ያሳስበናል ብዬ ስለማምን ነው በንጽጽር ያቀረብኩት፡፡ በዚህ መንፈስ በመነሳት፣ በተለይ የፊልም ተከታታይ የሆናችሁ አንባቢያን፣ ይህንን ድራማ እንድትመለከቱት በአክብሮት እጋብዛለሁ፡፡


Monday, October 15, 2018

እጅግ አስፈላጊው ሰው!



አብዱ አሊ ሂጂራ፤ ይህ ሰው በቀደመው ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይቀርብ በነበረው “እርስዎም ይሞክሩት” የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላይ ሕግ-ነክ ለሆኑ ጥያቄዎች ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠት የሚታወቅ፣ በዳኝነት እና በሬጅስትራርነት ለበርካታ ዓመታት አገሩን ያገለገለ አንጋፋ የሕግ ባለሙያ ነው፡፡ በሬዲዮ ያዳበረውን የሚዲያ ልምድ ይዞ በሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ ከዚያ በኋላም በሸገር ኤፍ ኤም “ረ በሕግ” የተባለውን ፕሮግራም አዘጋጅቶ በማቅረብ ሕግን ለማንኛውም ዜጋ በሚገባ መንገድ አስተምሯል፡፡ አሁን ደግሞ ከበሳሏ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር በመሆን በ”ሸገር ካፌ” ፕሮግራም ላይ ወቅታዊ የአገራችንና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በሕግ ዓይን በመተንተን ድንቅ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡
ከለውጡ ወዲህ የአገራችንን ወቅታዊ ዜናና መረጃ መከታተል የጀመሩ አንዳንድ ሰዎች አብዱ በጠንካራ አገላለጽ የሚያነሳቸውን የሕግ ሕጸጾች ሲተች ሲሰሙ “እስከዛሬ የት ቆይቶ ነው ዛሬ የሚያወራው?” ይላሉ፡፡ ሰውየው ግን፣ አቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ሳይቀር ከፓርላማው የሕግ አወጣጥ ሥርዓት አንስቶ እስከ ካቢኔው የመመሪያዎች መጣረስ ድረስ ሕግና ታሪክን እያጣቀሰ የሞገተ የሙያው ሰው መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ፍትሐ-ነገሥት፣ ከ1948ቱ ሕገ-መንግሥት እስከ 1987ቱ እና የተለያዩ ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች፣… ድረስ፣ አብጠርጥሮ በመመርመር መንግሥትንና ሕዝብን  ሲመክር የኖረ ደፋር ባለሙያ እንደሆነ የምናውቀው ሁሉ እንመሠክራለን፡፡ የዶ/ር ዐቢይን አስተዳደር መልካም ጎኖች በማወደስ ብቻ ሳይወሰን ስህተቶቹንም ጭምር ሕግና ሕግን ብቻ ተከትሎ እየነቀሰ ማስተካከያ እንዲያደርግ መክሯል (በነገራችን ላይ፣ መዓዛም ብትሆን “ዶ/ር ዐቢይ አሞግሰውኛል፣ የቦርድ አባል አድርገውኛል” በሚል ሳትደለል ስህተቶችን በመንቀስና በመጠቆም የምታደርገው ተግባር ሊደነቅ ይገባዋል)፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ሊጠቀሙባቸው ከሚገቡ ሰዎች መካከል አብዱ አሊ ሂጂራ አንደኛው ነው!