Friday, July 6, 2018

ይድረስ፡- “መ'ደመር” “መ'ደበር”* ለሆነባቸው ወገኖቻችን!

መቼም ይህ የሰሞኑ የለውጥ እና የአንድነት መንፈስ ብዙ ነገር እያሳየን ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለው) ለተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ልባዊ ድጋፉን፣ እንዲሁም ለዚህ ለውጥ መሪዎች አክብሮቱንና ምስጋናውን በከፍተኛ ስሜት እየገለጸ  ይገኛል፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት “ኢትዮጵያዊያን” ደግሞ የለውጡ ማዕበል እጅጉን አስደንግጧቸው፣ እነርሱም ስሜታቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ ናቸው፡፡
ለለውጡ አዎንታዊ አመለካከት ስላለው ሕዝብ ብዙ ስለተባለ ለአሁኑ እንለፈውና፣ ለውጡን በበጎ ስላልተመለከቱት ወገኖቻችን አንዳንድ ሐሳቦችን ላንሳ፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ከአገራዊ ስሜት ይልቅ ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ተቀንቅኗል፣ ተሰብኳልም፡፡ በዚህም፣ በተለይ በዘመነ-ኢሕአዴግ የተወለደው እና ነፍስ ያወቀው ቁጥሩ ቀላል የማይባል ትውልድ “ከአገር በላይ ብሔር” በሚል አስተሳሰብ ተቀርፆ ካለማው በላይ ያጠፋው በዝቷል፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የታነፀ ትውልድ ደግሞ፣ በዕውቀት የማይመራ፣ “ጃስ” ሲሉት ዘሎ የሚናከስ፣ ለታሪክ፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ እና እምነት ቦታ የሌለው መሆኑን ባለፉት ጊዜያት በዓይናችን ያየነው መራር እውነታ ነው፡፡
ከእስከዛሬ ልምዳችን ተነስተን ስናየው፣ የዚህ ዓይነት ትውልድ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በዕውቀት አይመራም፡፡ ለጠራው “አቤት”፣ ለላከው “ወዴት” እንጂ፣ “ለምን?”፣ “እንዴት?”፣… የሚባሉ የማጣሪያ ጥያቄዎችን አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ በአገራችን እየታየ ያለው አስደናቂ ለውጥ ያስደነገጣቸው እና ከለውጡ ጋር አብረው መጓዝ የከበዳቸው ወገኖች ይህንን ትውልድ እኩይ ለሆነው እና ለውጡን ለማሰናከል ለታለመው የክፋት ተግባራቸው ፈጻሚ እንዲሆን ሌት-ተቀን “ተግተው በመሥራት” ላይ መሆናቸው ለማንም ድብቅ አይደለም፡፡
ይህ ትውልድ፣ በተለይ “የዘመኑ ትውልድ”፣ ይህንን እኩይ ተግባር በተለያየ መንገድ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዋናነት ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም መርዛማ ቅስቀሳዎችን እንደሚያካሂድ የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎችም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፀረ-ለውጥ ኃይሎች በተቀነባበሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች ላይ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ያየናቸውን ዘግናኝ እና አሳፋሪ ጥቃቶች የሚፈጽመውም ይኸው ትውልድ ነው፡፡
ይህንን በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘ ያለ ትውልድ ከጥፋት መንገዱ ለመመለስ በእኔ እምነት መደረግ ያለበት ዋናው ነገር የዚህ እኩይ ሥራ መሐንዲሶችን አደብ ማስገዛት ነው፡፡ ምንም ማስተባበል በማያስፈልገው መልኩ፣ የዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት አቀነባባሪዎች በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ነባር ተዋንያን የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ግልጽ ማሳያዎችን አይተናል፤ በስብሰባ፣ በኮንፈረንስ፣ እና በመግለጫ ሲነገሩ የከረሙትን ለውጡን የሚቃወሙ ንግግሮች ሰምተንና ተገርመን ሳናበቃ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጭምር ከጦርነት አዋጅ የማይተናነስ ዛቻና ቀረርቶም አድምጠናል፡፡ በተቃውሞ፣ ዛቻ እና ፉከራ ብቻ ሳይወሰንም ተግባራዊ የጥቃት እርምጃዎችም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጽመዋል፡፡ አገር ለማተራመስ ከቦንብ ፍንዳታ እስከ ባንክና ድርጅት ዘረፋ፣ ከደረቅ ወንጀል እስከ ብሔር ግጭት፣ ከሰው-ሠራሽ የኑሮ ውድነት እስከተደራጀ የኢኮኖሚ አሻጥር ብዙ ተሠርቷል፡፡ ይህ ሁሉ እኩይ ተግባር ነገም፣ ከነገ ወዲያም ይቀጥላል፡፡ ሰዎቹ ዓላማቸው እስኪሳካ (የማይሳካ ቢሆንም) እንቅልፍ እንደማይወስዳቸውም በቃልም፣ በተግባርም እያሳዩን ነው፡፡
ይህ ሁሉ መፍጨርጨር ለምን? መልሱ ቀላል ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ ፍጥነቱንና ኃይሉን እየጨመረ በሄደ ቁጥር እየገላለጣቸው የሚሄዱ በጣም ብዙ ጉዶች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዶች ደግሞ በዋነኛነት የእነዚሁ ፀረ-ለውጥ ኃይሎች የአዕምሮ እና የእጅ ሥራዎች በመሆናቸው ተጠያቂነቱን በእጅጉ ይፈሩታል፡፡ እናም፣ ይህ ተጠያቂነት ወደእነርሱ እንዳይመጣ ያላቸው አማራጭ ለውጡን ማጨናገፍ ነው፡፡ ለውጡ እንዲጨናገፍ ደግሞ፣ አሁን እያየን እንዳለነው፣ በጥፍራቸው እና በጥርሳቸውም ጭምር እየተፋለሙ ናቸው፡፡
እነዚህ የፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴ መሐንዲሶች እና አስፈፃሚዎች በአሁኑ በኢትዮጵያ ገዢ ሀሳብ የሆነው “መደመር” ሲበዛ ደብሯቸዋል፡፡ የድብርታቸው መነሾም፣ “ኢትዮጵያዊያን ከተደመሩ፣ የእኛ ፕሮጀክት ይከሽፋል” የሚል ፍርሃታቸው ነው፡፡ ፍርሃታቸው አሁን ላይ እውን እየሆነ ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አቧራውን አራግፎ ተነስቷልና፡፡ ነገር ግን፣ ይህ “መደመር” እነርሱንም እንደሚያካትት እነዚህ ወገኖቻችን ሊያውቁ ይገባል፡፡
እናንተ ወገኖቻችን፣ አይዟችሁ “መደመር” “መጨፍለቅ” አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉትም አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት ማለት አይደለም። አሁን ላይ በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት ካለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተለየ ሀሳብ መያዝና ማራመድ ምንም ወንጀል አይደለም፡፡ ቁም-ነገሩ፣ የተለያዩ ሀሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ፣ በሰለጠነ መንገድ መወያየት እና መከራከር፣ ቢቻል ወደጋራ ሀሳብ መምጣት፣ ካልተቻለም ላለመስማማት መስማማት መቻል ነው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በንድፈ-ሐሳብ (theory) ብቻ የሚታወቅ፣ ተሞክሮም ሥልጣን ላይ ላለው ኃይል የማይመች ሲሆን ደግሞ ለግጭት እና ደም መፋሰስ ያደረሰን ይህንን ልምምድ አለማድረጋችን ነው፡፡ “የኔ ሀሳብ ብቻ ልክ ነው” የሚል ግትር አቋም በሥልጣን ተደግፎ ኢትዮጵያን ለመከራ፣ ዜጎቿን ለችግር እና እርስ በርስ ላለመተማመን ዳርጓቸዋል፡፡ አሁን ይህንን መጥፎ ሥዕል መቀየሪያ ጊዜያችን ነው፡፡ “እኔ ያላጠንኩበት ቅዳሴ መንግሥተ-ሰማያት አይደርስም” ከሚል የጉልበተኛ አስተሳሰብ እንውጣ፡፡ ከእነሐሳብ ልዩነታችን እንደመር፣ እንወያይ፣ ከስድብ ወጥተን በቀናነት እንከራከር፡፡ ግድ የላችሁም፣ ያንን ማድረግ ስንችል በረከቱ ለሁላችንም ነው፡፡ ደግሞም ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያይል በተለያዩ አገራት ታሪክ ያየነው ነውና እባካችሁ ከጀመራችሁት የሴራ እና የሽብር መንገድ ተመልሳችሁ በለውጡ ባቡር ተሳፈሩ!
በመጨረሻም፣ ይህ ከፍቅር እና ከትህትና የመነጨ የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ የሰላም ጥሪ እንጂ ከፍርሃት የመጣ ተማጽኖ እንዳልሆነ ልታውቁ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋሽ እንጂ ፈሪ አይደለም፡፡ በየዘመናቱ ጉልበተኞች በኃይል እና በማስገደድ ግፍ ሲፈጽሙበት፣ አንድም “ ነገ ከዛሬ ይሻላል፣ በጊዜ ይለወጣሉ” በሚል ተስፋ፣ አንድም “ቅዝምዝም እና ክፉ ቀንን ማሳለፍ ዝቅ ብሎ ነው” ብሎ አንገቱን በመድፋት በጥንቃቄ ሲጠብቅ የኖረ ነው፡፡ አይቶ አይቶ ሲበቃውና የግፉ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ ግን “በቃኝ” ብሎ መነሳትን ያውቅበታል፤ ይህንንም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሚገባ አሳይቷል፡፡ ሕዝቡ እኮ “ሒሳብ እናወራርድ” ቢል ጉዳችሁ ነው የሚፈላው፡፡ እናም እባካችሁ፣ ይህንን ሕዝብ አጉል አትፈታተኑት! የኋላ ኋላ ጉዳቱ እና ጸጸቱ ለእናንተ ነው የሚሆነው፡፡
እናም እላችኋለሁ፤ ተደመሩ እንጂ አትደበሩ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ይባርክ!




*ሁለቱም “ደ” ጠብቆ ይነበብ፡፡

No comments:

Post a Comment