Tuesday, July 17, 2018

“ልንሞት ነው?!”

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየተለመዱ ከመጡ አባባሎች መካከል አንዱ ነው፤ በተለይ በአሽከርካሪዎች ዘንድ፡፡ አንድ አሽከርካሪ ከፊቱ ያሉ ሌሎች ተሸከርካሪዎችን ቀድሞ ለማለፍ በሚያደርገው ሩጫና ችኮላ ያለመጠን ሲንቀዠቀዥ እና ጥሩምባ በጣም እያሰማ ሽብር ሲፈጥር፣ በግርግሩ የሚረበሸው ከፊት ያለው መኪና አሽከርካሪ “ልትሞት ነው?” ይለዋል፡፡ አሪፍ አባባል አይደል? በተለይ ለሁሉ ነገር ጥድፊያና ችኮላ ያበዛ በአብዛኛው ከፊቱ ምን እንዳለ የማያስተውል ስለሆነ በጥድፊያ መሃል ሞትም እንዳለ ማስታወሱ የተገባ ነው፡፡
በኢትዮጵያችን በየዘመናቱ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን ነገር ስንመለከት፣ ለአብዛኛዎቹ ነገሮቻችን መበላሸት ወይም አለመሳካት ምክንያት ከሆኑት ችግሮቻችን መካከል አንደኛው ችኮላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የምንፈልገው ነገር ዛሬውኑ ካልተደረገልን ኩርፊያችን፣ ቁጣችን፣ ስድባችን እና እርግማናችን “እግዚኦ!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አዲስ ነገር፣ አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ መሪ፣ አዲስ ክስተት፣… ሲመጣ አካሄዱን በጥሞና ከመመልከት ይልቅ ውጤቱን “ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ” ባዮች ብዙ ነን፡፡ ይህ ክፉ አመላችን፣ በእውነትም “ልትሞት ነው?” የሚያሰኝ ነው፡፡
የትናንት፣ የትናንት-በስቲያውን ትተን፣ የዛሬውን ሁኔታችንን እንኳን ብናይ፣ ትናንት በችኮላችን ካመለጡን ወርቃማ ዕድሎችና አጋጣሚዎች ምንም አለመማራችንን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን የሚያሳዩ ብዙ አስረጂዎች ቢኖሩም፣ በዚህ ጽሑፍ እኔ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ብቻ በመውሰድ ሐሳቤን  ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
ዛሬ በአገራችን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ተጀምሯል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ፣ ካገኘነው ይልቅ ያጣነው፣ ካለማነው ይልቅ ያጠፋነው እንደበዛ በተጨባጭ የታየበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝቡ ምሬት ጫፍ ደርሶ እና የግፉ ጽዋ ሞልቶ “በቃኝ!” ወደሚልበት ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ የዚህ ምሬት ውጤትም ሕዝቡን ወደ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን እንዲያሰማ ከማድረግ ባለፈ፣ ግጭትና የኃይል አማራጭን አክሎ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይታያል ተብሎ እምብዛም ያልተጠበቀ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል፡፡
ይህ ለውጥ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ እና ለነገም የተስፋ ስንቅ ያስቋጠረ ታሪካዊ ክስተት፣ ብሎም ዕድል ነው፡፡ “ለውጥ ያስፈልጋል!” የሚለውን የሕዝብ ድምጽ ሰምተው “አዎን፣ ለውጥ ያስፈልጋል” ያሉና ለዚህም የተጉ ተራማጆች ከገዢው ድርጅት ውስጥ ብቅ ብለው ወደ መሪነቱ አድገዋል፡፡ በእነዚህ መሪዎች በየዕለቱ እየተነገሩና እየተተገበሩ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ሚዲያዎቻችንን በ“ሰበር ዜናዎች” ከማጨናነቅም አልፈው ሰዎቹንም “እስከዛሬ ድረስ የት ነበራችሁ?” ብለን እንድንጠይቅ ያደረጉን ሆነዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ያየነው የለውጥ ጉዞ የአብዛኛውን ሕዝብ ይሁንታ የማግኘቱን ያህል አልጋ-በአልጋም አልነበረም፡፡ ብዙ ባይባልም ጉርምርምታ፣ ቅሬታ፣ ተቃውሞ፣… አላጣውም፡፡  ይህ በራሱ ችግር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም፣ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁሉንም ማስደሰት የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም፣ በዓለም ታሪክ ተደጋግሞ እንዳየነው፣ አዲስ ነገር ሁሉንም አያስደስትም፣ በዚህም ተግዳሮት መኖሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ ተግዳሮቶች ከየት፣ ለምን፣ እና እንዴት እንደመጡ መመርመር ለጉዞው መቃናት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
የተግዳሮቶቹን የት-መጣ'ነት ስንመረምር፣ የዚህ የለውጥ ጉዞ ፈተናዎች “ውጫዊ ብቻ ናቸው” ብሎ ማሰብ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እንዴት? ቢባል፣ ውስጣዊ ተግዳሮቶችም አብረው ስላሉ እነሱንም ማየት የግድ ይላል፡፡ በእኔ ትዝብት፣ ውስጣዊዎቹ የዚህ የለውጥ ጉዞ ተግዳሮቶች፤ ስሜታዊነት፣ ችኩልነት፣ በተቀደደው ቦይ ያለጥያቄ መፍሰስ፣ ለውጡን በተግባር ከማገዝ ይልቅ ከትናንቱ ያልተለየና ወደ ውድቀት የሚመራ የውዳሴና የመፈክር ጋጋታ፣ ለዚህ ለውጥ ዕውን መሆን የተከፈለውን መስዕዋትነት መዘንጋት፣ ወዘተ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጣዊ ተግዳሮቶች መካከል የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ትኩረት “ችኩልነት” ነው፡፡ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት፣ “የምንፈልገው ነገር አሁኑኑ…” የሚለው ጥያቄያችን፣ በዚህ ተስፋ በሰነቅንበት ወቅት በተለያየ መልክ ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ከመጡበት ዕለት አንስቶ በተቆጠሩት ሦስት ወራት ውስጥ በርካታ “ይሆናሉ” ብለን ያልጠበቅናቸውን ሥራዎች ሠርተው አስደምመውናል፡፡ አብዛኛዎቻችን ለእነዚህ ስኬቶቻቸው እርሳቸውንና ባልደረቦቻቸውን እያመሰገንን፣ “ቀጥሎስ ምን ይሠሩ ይሆን?” እያልን በጉጉት፣ ቀድሞ የማንከታተላቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች መከታተል ጀምረናል፡፡ አንዳንዶቻችን ግን፣ ከጉጉትም አልፈን እየተቻኮልን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እያቻኮልናቸው ነው፡፡ ጉጉት እና ችኮላ ይለያያሉ፡፡ ስንጓጓ፣ የጓጓንለት ነገር የሚሆንበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን፡፡ ስንቸኩል ግን፣ የጊዜን ዑደት፣ የሁኔታዎችን ባሕርይ፣ የሰዎችን አቅምና ሌሎች መሥፈርቶችን ለማየት ዐይንም፣ ጊዜም የለንም፡፡ ሂደቱን ዘልለን ውጤቱ ላይ ማረፍ ነው የምንፈልገው፡፡ ሲዘሉ ደግሞ መሰበርም አለ፡፡ “በሬ ሆይ፣ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንደሚባለው፡፡
በዚህ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከችኮላ የመነጩ በርካታ ድምፆችን ሰምተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዜጎችን ጨምሮ የፈለግነውን ነገር ዛሬ ላይ አሟልተው ስላልሰጡን የተቸናቸው፣ አለፍ ሲልም የሰደብንና የዘለፍናቸው አልታጣንም፡፡ እስቲ እኔ የታዘብኳቸውን በጥቂቱ ላስቀምጥ፡፡
“ዐቢይ ለምን የኦሮሚያና የሶማሌን ችግር አልፈታም፣” “ዐቢይ ለምን ለሙስሊሙ ችግር መፍትሄ አልሰጠም፣” “የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ለምን አልታሠሩም”፣ “የታሠሩ ሰዎች በሙሉ ለምን አልተፈቱም፣” “ስንት መስዕዋትነት የተከፈለባት ባድመን እንዴት ለኤርትራ እንሰጣለን፣” “አየር መንገድ እና ቴሌን መሸጥ ምን ያስፈልጋል፣” “የእኛ ዞን ለምን ክልል አይሆንም፣” “ለኢሳይያስ ለምን የደመቀ አቀባበል ይደረግለታል፣” “ቴዲ አፍሮ ለምን በዐቢይና በኢሳይያስ ፊት አላስጨፈረንም፣” …፡፡
እነዚህ ሁሉ ቅሬታዎች መነሻቸው ችኮላ ነው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይን ሰው መሆናቸውን ረስተው እንደ አምላክ ሁሉን ነገር “ይሁን” በሚል ቃል ብቻ የሚፈጽሙ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ሁኔታው ያልገባቸው ሰዎች መኖራቸውን ታዝበው ነው፣ ዶ/ር ዐቢይም ሀዋሳ ላይ ከኅብረተሰቡ ተወካዮች ጋር ሲወያዩ “ለእኔስ ጊዜ አያስፈልገኝም?” ብለው በሀዘኔታ የጠየቁት፡፡ አነዚህ ሰዎች፣ ባይታያቸው ነው እንጂ በሦስት ወራት ውስጥ የተሠራው ሥራ፣ በዓመታት ውስጥ ያልተሠራ ነው፡፡ ደግሞስ፣ አስተውለን ከሆነ፣ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች እኮ በሂደት መልስ አግኝተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው፡፡ የተወሰኑትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው የተብራራ መልስ ሲሰጡባቸው “ለካ ይኼም አለ” አሰኝተውናል፡፡ ካልቸኮልን ለሌሎቹም መልስ ማግኘታችን አይቀርም፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ ይህንን ሁሉ አይተንም ዛሬም ያልተማርን እና አንደበታችን ለዘለፋና ለስድብ የሰላ ሰዎች መኖራችን ነው፡፡ ልንሞት ነው እንዴ?
ጎበዝ! አንቸኩል፡፡ በሐምሌ የተዘራ ዘር ፍሬ ለመስጠት እስከ ታህሳስ ድረስ ያስጠብቃል እኮ! አብሲት እንኳን ተጥሎ የጥሩ እንጀራ ግብዓት ለመሆን ሦስት ቀን መቀመጥ አለበት እኮ! ዛሬ የተፀነሰ ጽንስ ሕፃን ሆኖ ምድርን ለመቀላቀል ዘጠኝ ወር ይፈልጋል እኮ! ተፈጥሮ መታገስን ካላስተማረችን ማን ሊያስተምረን ነው? የእውነት ግን “ልንሞት ነው?!”
እንታገስ! እግር እንጂ ክንፍ እንዳልተሰጠን አውቀን፣ መራመድና መሮጥ እንጂ መብረር እንደማንችል ተገንዝበን ረጋ እንበል! በችኮላችን መውደቅ እንዳለም አንዘንጋ፤ እንኳን ተሩጦ፣ ተራምዶም መደናቀፍ አለ፡፡ አጉል ስንጣደፍና ስንቸኩል አይቶ “ልትሞቱ ነው?” ከሚል ተቺ ይሰውረን!


Friday, July 6, 2018

ይድረስ፡- “መ'ደመር” “መ'ደበር”* ለሆነባቸው ወገኖቻችን!

መቼም ይህ የሰሞኑ የለውጥ እና የአንድነት መንፈስ ብዙ ነገር እያሳየን ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለው) ለተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ልባዊ ድጋፉን፣ እንዲሁም ለዚህ ለውጥ መሪዎች አክብሮቱንና ምስጋናውን በከፍተኛ ስሜት እየገለጸ  ይገኛል፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት “ኢትዮጵያዊያን” ደግሞ የለውጡ ማዕበል እጅጉን አስደንግጧቸው፣ እነርሱም ስሜታቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ ናቸው፡፡
ለለውጡ አዎንታዊ አመለካከት ስላለው ሕዝብ ብዙ ስለተባለ ለአሁኑ እንለፈውና፣ ለውጡን በበጎ ስላልተመለከቱት ወገኖቻችን አንዳንድ ሐሳቦችን ላንሳ፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ከአገራዊ ስሜት ይልቅ ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ ተቀንቅኗል፣ ተሰብኳልም፡፡ በዚህም፣ በተለይ በዘመነ-ኢሕአዴግ የተወለደው እና ነፍስ ያወቀው ቁጥሩ ቀላል የማይባል ትውልድ “ከአገር በላይ ብሔር” በሚል አስተሳሰብ ተቀርፆ ካለማው በላይ ያጠፋው በዝቷል፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የታነፀ ትውልድ ደግሞ፣ በዕውቀት የማይመራ፣ “ጃስ” ሲሉት ዘሎ የሚናከስ፣ ለታሪክ፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ እና እምነት ቦታ የሌለው መሆኑን ባለፉት ጊዜያት በዓይናችን ያየነው መራር እውነታ ነው፡፡
ከእስከዛሬ ልምዳችን ተነስተን ስናየው፣ የዚህ ዓይነት ትውልድ ከላይ እንደገለጽኩት፣ በዕውቀት አይመራም፡፡ ለጠራው “አቤት”፣ ለላከው “ወዴት” እንጂ፣ “ለምን?”፣ “እንዴት?”፣… የሚባሉ የማጣሪያ ጥያቄዎችን አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ በአገራችን እየታየ ያለው አስደናቂ ለውጥ ያስደነገጣቸው እና ከለውጡ ጋር አብረው መጓዝ የከበዳቸው ወገኖች ይህንን ትውልድ እኩይ ለሆነው እና ለውጡን ለማሰናከል ለታለመው የክፋት ተግባራቸው ፈጻሚ እንዲሆን ሌት-ተቀን “ተግተው በመሥራት” ላይ መሆናቸው ለማንም ድብቅ አይደለም፡፡
ይህ ትውልድ፣ በተለይ “የዘመኑ ትውልድ”፣ ይህንን እኩይ ተግባር በተለያየ መንገድ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዋናነት ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም መርዛማ ቅስቀሳዎችን እንደሚያካሂድ የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎችም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፀረ-ለውጥ ኃይሎች በተቀነባበሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች ላይ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ያየናቸውን ዘግናኝ እና አሳፋሪ ጥቃቶች የሚፈጽመውም ይኸው ትውልድ ነው፡፡
ይህንን በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘ ያለ ትውልድ ከጥፋት መንገዱ ለመመለስ በእኔ እምነት መደረግ ያለበት ዋናው ነገር የዚህ እኩይ ሥራ መሐንዲሶችን አደብ ማስገዛት ነው፡፡ ምንም ማስተባበል በማያስፈልገው መልኩ፣ የዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት አቀነባባሪዎች በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ነባር ተዋንያን የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ግልጽ ማሳያዎችን አይተናል፤ በስብሰባ፣ በኮንፈረንስ፣ እና በመግለጫ ሲነገሩ የከረሙትን ለውጡን የሚቃወሙ ንግግሮች ሰምተንና ተገርመን ሳናበቃ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጭምር ከጦርነት አዋጅ የማይተናነስ ዛቻና ቀረርቶም አድምጠናል፡፡ በተቃውሞ፣ ዛቻ እና ፉከራ ብቻ ሳይወሰንም ተግባራዊ የጥቃት እርምጃዎችም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጽመዋል፡፡ አገር ለማተራመስ ከቦንብ ፍንዳታ እስከ ባንክና ድርጅት ዘረፋ፣ ከደረቅ ወንጀል እስከ ብሔር ግጭት፣ ከሰው-ሠራሽ የኑሮ ውድነት እስከተደራጀ የኢኮኖሚ አሻጥር ብዙ ተሠርቷል፡፡ ይህ ሁሉ እኩይ ተግባር ነገም፣ ከነገ ወዲያም ይቀጥላል፡፡ ሰዎቹ ዓላማቸው እስኪሳካ (የማይሳካ ቢሆንም) እንቅልፍ እንደማይወስዳቸውም በቃልም፣ በተግባርም እያሳዩን ነው፡፡
ይህ ሁሉ መፍጨርጨር ለምን? መልሱ ቀላል ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ እየነፈሰ ያለው የለውጥ ንፋስ ፍጥነቱንና ኃይሉን እየጨመረ በሄደ ቁጥር እየገላለጣቸው የሚሄዱ በጣም ብዙ ጉዶች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዶች ደግሞ በዋነኛነት የእነዚሁ ፀረ-ለውጥ ኃይሎች የአዕምሮ እና የእጅ ሥራዎች በመሆናቸው ተጠያቂነቱን በእጅጉ ይፈሩታል፡፡ እናም፣ ይህ ተጠያቂነት ወደእነርሱ እንዳይመጣ ያላቸው አማራጭ ለውጡን ማጨናገፍ ነው፡፡ ለውጡ እንዲጨናገፍ ደግሞ፣ አሁን እያየን እንዳለነው፣ በጥፍራቸው እና በጥርሳቸውም ጭምር እየተፋለሙ ናቸው፡፡
እነዚህ የፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴ መሐንዲሶች እና አስፈፃሚዎች በአሁኑ በኢትዮጵያ ገዢ ሀሳብ የሆነው “መደመር” ሲበዛ ደብሯቸዋል፡፡ የድብርታቸው መነሾም፣ “ኢትዮጵያዊያን ከተደመሩ፣ የእኛ ፕሮጀክት ይከሽፋል” የሚል ፍርሃታቸው ነው፡፡ ፍርሃታቸው አሁን ላይ እውን እየሆነ ነው፣ ኢትዮጵያዊነት አቧራውን አራግፎ ተነስቷልና፡፡ ነገር ግን፣ ይህ “መደመር” እነርሱንም እንደሚያካትት እነዚህ ወገኖቻችን ሊያውቁ ይገባል፡፡
እናንተ ወገኖቻችን፣ አይዟችሁ “መደመር” “መጨፍለቅ” አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉትም አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት ማለት አይደለም። አሁን ላይ በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት ካለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተለየ ሀሳብ መያዝና ማራመድ ምንም ወንጀል አይደለም፡፡ ቁም-ነገሩ፣ የተለያዩ ሀሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ፣ በሰለጠነ መንገድ መወያየት እና መከራከር፣ ቢቻል ወደጋራ ሀሳብ መምጣት፣ ካልተቻለም ላለመስማማት መስማማት መቻል ነው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በንድፈ-ሐሳብ (theory) ብቻ የሚታወቅ፣ ተሞክሮም ሥልጣን ላይ ላለው ኃይል የማይመች ሲሆን ደግሞ ለግጭት እና ደም መፋሰስ ያደረሰን ይህንን ልምምድ አለማድረጋችን ነው፡፡ “የኔ ሀሳብ ብቻ ልክ ነው” የሚል ግትር አቋም በሥልጣን ተደግፎ ኢትዮጵያን ለመከራ፣ ዜጎቿን ለችግር እና እርስ በርስ ላለመተማመን ዳርጓቸዋል፡፡ አሁን ይህንን መጥፎ ሥዕል መቀየሪያ ጊዜያችን ነው፡፡ “እኔ ያላጠንኩበት ቅዳሴ መንግሥተ-ሰማያት አይደርስም” ከሚል የጉልበተኛ አስተሳሰብ እንውጣ፡፡ ከእነሐሳብ ልዩነታችን እንደመር፣ እንወያይ፣ ከስድብ ወጥተን በቀናነት እንከራከር፡፡ ግድ የላችሁም፣ ያንን ማድረግ ስንችል በረከቱ ለሁላችንም ነው፡፡ ደግሞም ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያይል በተለያዩ አገራት ታሪክ ያየነው ነውና እባካችሁ ከጀመራችሁት የሴራ እና የሽብር መንገድ ተመልሳችሁ በለውጡ ባቡር ተሳፈሩ!
በመጨረሻም፣ ይህ ከፍቅር እና ከትህትና የመነጨ የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ የሰላም ጥሪ እንጂ ከፍርሃት የመጣ ተማጽኖ እንዳልሆነ ልታውቁ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋሽ እንጂ ፈሪ አይደለም፡፡ በየዘመናቱ ጉልበተኞች በኃይል እና በማስገደድ ግፍ ሲፈጽሙበት፣ አንድም “ ነገ ከዛሬ ይሻላል፣ በጊዜ ይለወጣሉ” በሚል ተስፋ፣ አንድም “ቅዝምዝም እና ክፉ ቀንን ማሳለፍ ዝቅ ብሎ ነው” ብሎ አንገቱን በመድፋት በጥንቃቄ ሲጠብቅ የኖረ ነው፡፡ አይቶ አይቶ ሲበቃውና የግፉ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስ ግን “በቃኝ” ብሎ መነሳትን ያውቅበታል፤ ይህንንም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሚገባ አሳይቷል፡፡ ሕዝቡ እኮ “ሒሳብ እናወራርድ” ቢል ጉዳችሁ ነው የሚፈላው፡፡ እናም እባካችሁ፣ ይህንን ሕዝብ አጉል አትፈታተኑት! የኋላ ኋላ ጉዳቱ እና ጸጸቱ ለእናንተ ነው የሚሆነው፡፡
እናም እላችኋለሁ፤ ተደመሩ እንጂ አትደበሩ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ይባርክ!




*ሁለቱም “ደ” ጠብቆ ይነበብ፡፡