እንደ መንደርደሪያ
ጥቅምት 6 ቀን 2008 ዓ.ም.
በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለግል ቴሌቪዥን ፈቃድ መስጠት በመጪው ዓመት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል
ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ መናገራቸውን የሚገልጽ ዜና አነበብኩ፡፡ የታሰበው ዕውን መሆኑ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ቢሆንም፣
ሐሳቡ መነሳቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነውና አቶ ልዑልንና አዲስ አድማስን ”ቸር ወሬ ያሰማችሁ!” ልላቸው እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የግል ቴሌቪዥን መኖር ጉዳይ ላለፉት 24 ዓመታት ተደጋግሞ
ሲነሳ የቆየ ነው፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በፊት በአገሪቱ የነበሩት አንድ ብሔራዊ ቴሌቪዥንና አንድ የትምህርት ቴሌቪዥን ብቻ መሆናቸው
የቴሌቪዥን አገልግሎትን ውስን ይዘት ያለው እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ሐሳብን በነፃነት
እና በተለያዩ መንገዶች መግለጽ በመርህና በሕግ የተረጋገጡ መብቶች መሆናቸውን ተከትሎ ከመገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ በሆነው የብሮድካስት
ሚዲያ ዘርፍ የኅትመት ሚዲያውን ያህል እርምጃ ያለመታየቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ ዋነኛው ጥያቄ የአማራጭ ሚዲያ መኖር
ሲሆን፣ በተያያዥነትም በአሁኑ ወቅት በሥርጭት ላይ ያሉት የቴሌቪዥን ሚዲያዎች የአገልግሎት ጥራት፣ የጊዜ ርዝማኔ፣ እና የሥርጭት
ተደራሽነት አብረው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የብሮድካስት ሚዲያን ለማስፋፋት የተለያዩ
እርምጃዎች ባለፉት ዓመታት ተወስደዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፍ ከመፍጠር አንስቶ የብሮድካስት ሚዲያዎች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ በሕግ
ደረጃ በ1991 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. የወጡት የብሮድካስት አዋጆች ለዘርፉ መስፋፋት በመንግሥት በኩል ያለው ፈቃደኝነት
ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ሲሆኑ፣ አዋጁን ተከትለው በቁጥር በርከት ያሉ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግሥትና የግል ድርጅቶች
እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ ተቋቁመው መንቀሳቀሳቸው ለዘርፉ ማደግ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ሊታይ የሚችል እርምጃ ነው፡፡
አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው የብሮድካስት አዋጅ ቁጥር 533/1999
አንቀጽ 2(2) መሠረት የብሮድካስት አገልግሎት ማለት ”ሕዝብን
ለማስተማር፣ ለማሳወቅ፣ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት” ነው፡፡ ከዚህ ትርጉም አንፃር
በአገራችን በአሁኑ ወቅት በብዛት በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ በቴሌቪዥን ዘርፍ ግን ከመንግሥታዊው ኢቢሲ፣
ከተወሰኑ የክልል ቴሌቪዥኖች እና መሠረታቸውን በውጪ አገራት አድርገው በሳተላይት ከሚሠራጩ የግል ቴሌቪዥኖች በስተቀር በቁጥርም
ሆነ በጥራት በቂ የሆኑ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች የሉም፡፡
ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች እጥረትና የጥራት ውሱንነት የአገራችንን
የቴሌቪዥን ተመልካች አማራጭ በማሳጣቱ የተነሳ በርካታ ሕዝብ ወደውጪ ሚዲያዎች ፊቱን እንዲያዞር ተገዷል፡፡ በተለይም ከመካከለኛው
ምሥራቅ አገሮች በነፃ የሚሠራጩ የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻናሎች (free-to-air TV channels) በአብዛኛው የቴሌቪዥን ተመልካቾች
ዘንድ በአማራጭነት ተወስደዋል፡፡ እነዚህ ቻናሎች ደግሞ በአመዛኙ በአረብኛ ቋንቋ የሚቀርቡ በመሆናቸው ተመልካቹ በማይገባው ቋንቋ
ፕሮግራሞችን ለመከታተል መገደዱ ቻናሎቹን ከመማሪያና መዝናኛነት ይልቅ የጊዜ ማሳለፊያ ብቻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ
ችግሮች በመነሳት በአገራችን አማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ በስፋት መኖር አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ጸሐፊ ያምናል፡፡
በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጥቅምት 6 ዕትም፣
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለ22 የመንግሥትና የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት መታቀዱን ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለጋዜጣው
እንደተናገሩት፣ በዚህ ዓመት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር ሲጠናቀቅ ከሚኖሩት 22 ቻናሎች መካከል ለእያንዳንዱ ክልልና
ለኢቢሲ ቻናሎች የሚሰጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ቻናሎች ደግሞ ለግል ድርጅቶች በጨረታ ይሰጣሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው የቻናሎች ክፍፍል
መሠረት፣ ሦስት ቻናሎች ለግል ብሮድካስተሮች ተመድበዋል፡፡ ቀሪዎቹ 19 ቻናሎች ደግሞ ለመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያዎች የሚሰጡ ይሆናል፡፡
ሦስት የግል ቻናሎች ካለው ፍላጎት አንፃር አነስተኛ ቢሆኑም፣ የግል
ብሮድካስተሮችን ወቅታዊ አቅም ከግምት ስናስገባ ለጊዜው በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቁም ነገሩ ግን ብዛታቸው ሳይሆን ጥራትና ብቃት ነው
ባይ ነኝ፡፡ ልናተኩርበትም የሚገባው ይኸው የጥራትና ብቃት ጉዳይ ነው፡፡ ደጋግሜ ያነሳሁት የአማራጭ የቴሌቪዥን ሚዲያ አስፈላጊነት
መነሻው እስካሁን ያሉን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚፈለገው የጥራትና የብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው መሆኑን ስንመለከት፣ ስለእነዚህ
ጉዳዮች የማሰብና የመወያየትን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ይህ የጥራት ጉዳይ አሁን በሥርጭት ላይ ያሉትንም ሆነ ወደፊት ሥራ ይጀምራሉ የሚባሉትን ጣቢያዎች በእኩል የሚመለከት በመሆኑ፣ በእኔ
በኩል ያሉኝን ዕይታዎችና ተያያዥ ሐሳቦች በተከታታይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ ስድስት ወራት ያለፉት ቢሆንም፣ በጊዜው በጋዜጣ እንዲወጣ ተልኮ ሳይወጣ የቀረ ጽሑፍ ነው፡፡ አሁን ግን ከርዕሰ-ጉዳዩ ወቅታዊነት አንፃር በዚህ ብሎግ ላይ ቀርቧል፡፡