Tuesday, July 21, 2015

ቴሌቪዥን፣ ልጆችና ወላጆች- ፩


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት ከምንሰማቸው ጉዳዮች መካከል ”ፊልም፣ ቴሌቪዥን፣ እና ሕጻናት” አንደኛው ነው፡፡ የዚህ ጉዳይ ዋነኛ መነሻ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች እና ፊልሞች በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ይመስለኛል፡፡ ወቅቱ ክረምት ነውና ሕጻናት እና ታዳጊዎች ከእነዚህ ፊልሞች እና ፕሮግራሞች ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፋቸው (በአብዛኛው ካለወላጅ እና አሳዳጊ ክትትል) አሳሳቢነቱ አያጠያይቅም፡፡
መወያየቱ፣ መመካከሩ፣ እና መፍትሄ መፈለጉ የሚደገፍ ነው፤ ሆኖም የውይይቱና የክርክሩ ተሳታፊዎች ብዙውን ጊዜ ሲያነሱት የማልሰማው አንድ ጉዳይ ቢኖር የወላጅ/አሳዳጊ ኃላፊነት ነው፡፡ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ስለሚመለከቷቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ምን ያህል ያውቃሉ?  የሚመለከቱትን ፕሮግራም እንዴት መቆጣጠር ይችላሉ? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን አንስቶ የሚወያይና የሚያወያይ፣ የሚያጠናና የሚመራመር አካል (ባለሙያ ወይም ተቋም) እስካሁን ድረስ አላጋጠመኝም፡፡ በአብዛኛው ተወቃሽ ተደርገው የሚነሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ናቸው፡፡ ስለወላጆችና አሳዳጊዎች ድርሻ ግን ምንም ነገር ሲነገር አልሰማሁም፣ የተጻፈም ነገር እስካሁን ድረስ አላገኘሁም፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ከጀመርኩ ከአሥር ዓመታት በላይ አልፏል፣ ይህ ጽሑፍ ከተጀመረ ደግሞ ሁለት ዓመት ሊሆን ነው፡፡ ነገር ግን ርዕሰ-ጉዳዩ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ጊዜ ወስዶ ማሰብ ስላስፈለገኝና መጠነኛ ስንፍናም ተጨምሮበት ጽሑፉ እስካሁን ድረስ ከአንድ አንቀጽ በላይ ሳይሄድ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ እንደአዲስ ይህንን ጉዳይ እንድመለስበት ያደረገኝ በልጆች አስተዳደግ ላይ በቅርባችን የማያቸው ነገሮች የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ሆነው ስላገኘኋቸው ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት ”ቴሌቪዥን፣ ልጆች፣ እና የወላጅ ኃላፊነት” ስለሚለው ጉዳይ ማሰብ ከጀመርኩ ቆይቷል (በትክክል ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነው)፡፡ የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት በአገር ውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ”ቲቪ አፍሪካ” የተባለ ቻናል ታስታውሱታላችሁ፡፡ በወቅቱ ይህ ቻናል ለብዙ ተመልካቾች የመረጃና የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ የተወዳጅነቱን ያህል ብዙ ትችቶችንም አስተናግዷል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ”ቲቪ አፍሪካ ልጆቻችንን እያበላሸ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱት ይሰማ ነበር- በጊዜው፡፡
ከእነዚህ ትችቶች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን የሳበውንና ስለወላጅ ኃላፊነት እንዳስብ ያደረገኝን ሐሳብ የሰማሁት በ1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ በአንድ ስብሰባ ላይ አንድ ዕውቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የትውልዱን ሥነ-ምግባር አስመልክተው  ሲናገሩ ”አኔ እኮ ዛሬ ልጆቼን አላሳድግም፣ ልጆቼን የሚያሳድግልኝ ቲቪ አፍሪካ ነው” ብለው ነበር፡፡ ይህ አባባል የስብሰባውን ተሳታፊዎች ፈገግ አሰኝቶ ነበር፣ እኔንም አስቆኛል፣ ከሳቁ በኋላ ግን ቀደም ብሎ ከሰማኋቸው ትችቶችና ወቀሳዎች ጋር ተዳምሮ ነገሩ ከነከነኝ፡፡ ”የቴሌቪዥናቸውን አንቴናና የቲቪ አፍሪካን ፍሪኩዌንሲ አስተካክለው ቤታቸው ያስገቡት እራሳቸው ወላጆች ሆነው ሳለ ቻናሉን ለምን ይተቻሉ? ስለሚተላለፉት ፕሮግራሞች የሚሰጠውን ማሳሰቢያስ ለምን አይከታተሉም?” ብዬም ጠየቅሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቲቪ አፍሪካ ፕሮግራሞች ይዘትና የስርጭት መርሐ-ግብር ምን እንደሚመስል ማወቅ ስለፈለግሁ የቲቪ አፍሪካን ድረ-ገጽ ጎበኘሁ፡፡  
በኢቲቪ-2 የሚተላለፈው የቲቪ አፍሪካ ስርጭት ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ እኩለ-ሌሊት ድረስ የሚዘልቅ ቢሆንም፣ ቲቪ አፍሪካ ግን ለ24 ሰዓታት የተለያዩ ፕሮግራሞችን (ዜና፣ ድራማ፣ ሶፕ ኦፔራ፣ ፊልም፣ ሙዚቃ፣…) የሚያቀርብ ነጻ ቻናል መሆኑን ከድረ-ገጹ ላይ ለመረዳት ቻልኩ፡፡ በድረ-ገጹ ላይ የተቀመጠው የፕሮግራሞች ዝርዝር የእያንዳንዱን ፕሮግራም ዓይነትና ይዘት፣ እንዲሁም የተመልካቾች የዕድሜ ገደብ የሚገልጽ አጭር መግለጫ የያዘ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የፕሮግራሞች የዕድሜ ገደብ መግለጫ በተለይ ፊልሞችና ድራማዎች በቴሌቪዥን መቅረብ ከመጀመራቸው በፊት በግልጽ ቋንቋ ለተመልካቾች ይገለጽ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የወላጆችን ኃላፊነት አስመልክቶ ማሰብ የጀመርኩት፡፡ የቴሌቪዥን ቻናሉ ”የማስተላልፈው ፕሮግራም ከዚህ ዕድሜ በላይ ላሉ ተመልካቾች የሚሆን ነው” ብሎ ካሳወቀ፣ ቀሪው ኃላፊነት የወላጅ፣ የቤተሰብ፣ የአሳዳጊ ወይም የሞግዚት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ወላጅና ቤተሰቦች፣ ቻናሉን ጥፋተኛ አድርገው ለመውቀስ የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሥራቸውን አልሰሩማ!      


(ይቀጥላል)                                              

Sunday, July 12, 2015

ኃላፊነትን አለመውሰድ- አደገኛው ገዳይ!

ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የሸገር ኤፍ.ኤም. 102.1 ”የዓርብ ልዩ ወሬዎች” ላይ ከቀረቡት ዜናዎች መካከል አንዱ ታላላቅ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኢንተርኔት አገልግሎት እየተቋረጠባቸው መቸገራቸውን የሚያትት ነበር፡፡ በተለይም ከሰኞ ሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ ለአሥር ቀናት ያህል በከተማዋ በሚስተናገደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ የአንዲት አፍሪካዊት አገር ፕሬዚዳንት ባረፉበት ሆቴል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ ከሹሞቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ በእፍረት መግለጻቸው የወሬው መነሻ ነበር፡፡ በዘገባው ላይ የሆቴሎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት የኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ የችግሩን ስፋትና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ መሆናቸውን እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ሆቴል የደረሰውን ችግር በማሳያነት አቅርበው በምሬት ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡
መቼም በእኛ አገር አንድ ችግር ሲያጋጥም ለችግሩ ፈጣን ምላሽ ማግኘት (በተለይ አሁን አሁን) ብርቅ እየሆነብን ነው፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ችግሩን እንዲፈታ የሚጠበቀው አካል ለችግሩ መፈጠር ወይም ለመፍትሄው በቶሎ አለመምጣት የሚደረድረው ሰበብና ምክንያት ዓይነት ነው፡፡ ስለተፈጠረው ችግር መንስኤውን አጣርቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠትና ለችግሩም መፈጠር ይቅርታ መጠየቅን የማይደፍሩ አገልግሎት ሰጪዎች በዝተዋል፡፡ እንዲያውም የችግሩን መነሻ ወደሌላ አካል ማላከክ ይቀናቸዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ላይ አገልግሎት ሰጪው የሰጠው ምላሽም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ይህ ዜና በቀረበ በማግሥቱ (ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን) ኢትዮ ቴሌኮም በሰጠው ምላሽ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የተፈጠረው የኢንተርኔት መቋረጥ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት የተፈጠረ መሆኑንና የሆቴሉ ጄኔሬተር በራሱ አለመነሳቱን ባለሙያዎቹ አረጋግጠው ጄኔሬተሩ ሲስተካከል ኢንተርኔቱም ሥራውን መቀጠሉን አስረድቷል፡፡ አያይዞም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ባለስም ሆቴሎች መካከል አብዛኞቹ የኢንተርኔት አግልግሎት እንደሌላቸው በጥናት በመረጋገጡ እንዲያስገቡ በተገለጸላቸው መሠረት አራቱ ብቻ እስካሁን ድረስ ማስገባታቸውን በመግለጽ ችግሩ የሆቴሎቹ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ እኔን ፈጽሞ አላሳመነኝም፡፡ እስቲ አስቡት! ኢንተርኮንቲኔንታልን የሚያክል ትልቅ ሆቴል ኤሌክትሪክ ሲቋረጥበት ሳያውቅ ሲቀር፡፡ መብራቶች ሲጠፉ፣ ሊፍቶች ሥራ ሲያቆሙ፣ ኤሌክትሪክ ጠፍቶ ጄኔሬተሩ እንዳልተነሳ ሲያይ ጄኔሬተሩን የማይፈትሽ የሆቴል አስተዳደር አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ እንኳን ሆቴልን ያህል ተቋም በየቤታችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሲቋረጥ ቀድመን የምናየው ቆጣሪውን ነው፡፡ ምናልባት ከቆጣሪው ጠፍቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት ያለኤሌክትሪክ እንደማይሠራ ማንም የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚስተው አይመስለኝም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ሆቴሉ ይህንን ሁሉ ”አያውቅም ነበር” እያለን ነው፡፡ እንዲያውም ”ችግሩን እኔ ስለደረስኩበት ልመሰገን እንጂ ልወቀስ አይገባኝም” ዓይነት ምላሽ ይመስላል የሰጠው፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ የገመድ-አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት (wi-fi service) በሚቋረጥበት ጊዜ መልሶ ለማስጀመር የሚደረገው የኢንተርኔት ማገናኛ መሣሪያውን (router) አጥፍቶ እንደገና ማብራት ነው፡፡ ሆቴሉ መብራት ጠፍቶበት እንደገና ሲመጣ ይህንን ማድረግ እንዳለበት አያውቅም ለማለት ይከብደኛል፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ እንደተረዳሁት ችግሩ ከአንድ ቀን በላይ የቆየ እንደሆነ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ችግር እንዴት አድርጎ ነው ከኤሌክትሪክ መቋረጥ ጋር ብቻ ሊያያዝ የሚችለው?
ጉዳዩ ቴክኒካዊ ስለሆነ ምናልባት እኔን ያልገባኝ ሙያዊ ነገር ካለ እታረማለሁ፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በትልልቅ ሆቴሎች ብቻ ሳይሆን የዋይ-ፋይ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አነስተኛ ካፌዎች እና ቢሮዎችም ጭምር በዚህ ሰሞን እያጋጠመ ያለ ችግር ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ይህንን ሁሉን አቀፍ ችግር ከግምት አስገብቶ የተሰጠ አይደለም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ኩባንያው ችግሩን ወደሌላ አካል የመግፋት ዓይነት አካሄድ ተከትሏል ባይ ነኝ፡፡ በሌላ አነጋገር ከተጠያቂነት ሽሽት ነው፡፡

መቼ ይሆን ስህተትንና ጥፋትን አምኖ ኃላፊነትን መውሰድ የምንለምደው? እርግጥ ነው! በግለሰብ ደረጃ ይህ ዓይነት ችግር የብዙዎቻችን ባሕርይ ነው (እኔም አንዱ የዚህ ባሕርይ ተሸካሚ መሆኔን እዚህ ላይ ማመን ይኖርብኛል)፡፡ ተቋማት ይህንን ግለሰባዊ ባሕርይ ወርሰው ግትር ሲሆኑ ግን ደስ አይልም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት የሚወስድ በጠፋ ቁጥር ለመፍትሄ መትጋት አይኖርም፡፡ ለመፍትሄ ካልተጋን ደግሞ መሻሻል እንደናፈቀን ይቀራል፡፡ ኃላፊነትን አለመውሰድ የአገር በሽታ እየሆነብን ይመስለኛል፤ አደገኛ ገዳይ፡፡  በጊዜ እናክመው!