ይህችን አጭር ጦማር ስጽፍ፣ ዕለቱ እሁድ፣ ሰኔ 13 ቀን 2013፣ ሰዓቱ ከምሽቱ 12፡30
ነው፡፡ ብዙ የተባለለትንና የተባለበትን፣ ተስፋ፣ ፍርሃት እና ስጋት የሚንጸባረቅበት እና የኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል እንደሚወስን የሚጠበቀው
አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ይቀረዋል፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት በተካሄደው የ2007 የኢትዮጵያ ምርጫ ወቅት ብዙ አስገራሚ ሁነቶችን
ታዝበን ነበር፡፡ የፈዘዘ የፓርቲዎች ቅስቀሳና ክርክር፣ በሕጸጾችና በሕገወጥ አካሄዶች የተሞላ የመራጮች ምዝገባ፣ ሕግን የተላለፈ
የቤት ለቤት የምርጫ ቅስቀሳ፣ በምርጫ ቀን ሳይቀር ያልተቋረጠ የምረጡን ጥሪ፣ እና በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የ100 ፐርሰንት
አሸናፊነት፡፡
ይህ ሁሉ ሂደት ታልፎ የተመሠረተው “መንግሥት” መንፈቅ ሳይሞላው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች
በተነሱ ተቃውሞዎች ግራ ተጋብቶ የአገሪቱም ጉዞ ግራ የተጋባ ሆኖ ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት እየተንገራገጨ የሄደው ይህ ጉዞ በተለይ
በ2010 ይበልጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ፣ ሕዝባዊው ተቃውሞም ይበልጥ ሲቀጣጠል የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት የተረዱና ለውጥ እንደሚያስፈልግ
የተረዱ የገዢው ፓርቲ አመራሮች ወደፊት መጥተው ተግባራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ አደረጉ፣ በዚህም አዲስ የለውጥ አመራር የአገሪቱን
የፖለቲካ አመራር ተረከበ፡፡
ከዚያ ወዲህ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ ክስተቶችን አስተናግዳለች፣ ኢትዮጵያ፡፡ ተግባራዊ የፖለቲካ
ለውጥ፣ አዳዲስ አሠራሮች፣ አዲስ ተስፋ፣…፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የከፉ የብሔር ግጭቶች፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የአገር
መፍረስ ስጋት፣…፡፡ ብዙዎች ወገኖቻችንን ከስደት አስመለስን፣ በደስታ አነባን፣ ፈነጠዝን፣…፡፡ ብዙዎች ወገኖቻችንን ሰምተን በማናውቀው
ጭካኔ አጣን፣ በዘመናት ልፋት የተገኘ ሀብትና ንብረት ወደመብን፣…፡፡ ብዙ ወገኖቻችን በስደትና መፈናቀል ተጎዱብን፣…፡፡
ይህንን ሁሉ ተለዋዋጭ ሁኔታ ያስተናገደችው ኢትዮጵያችን ግን ዛሬም አለች፣ ትናንትን እንዳለፈች
ሁሉ ዛሬንም አልፋ ነገንም ትኖራለች፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችንን ለማኖር የአገራችን ባለቤቶች እኛ መሆናችንን
ስናረጋግጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዕድላችንን እንጠቀምበት!
የምርጫ ካርድ ያወጣን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፣ ነገ ካርዳችንን እንጠቀምበት፡፡ ኢትዮጵያን ያሻግራል፣
ወደከፍታዋ ያደርሳል፣ የዛሬውን ጨለማ ነገ ይገፍልናል ብለን የምናምነውን እንምረጥ፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን፣ ማንም ያሸንፍ፣ ግን
ተአማኒ ምርጫ በማድረግ የአገራችንን ነገ ብሩህ ለማድረግ ድርሻችንን እንወጣ፡፡ ከተሳካልን፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሟርቱትን ሁሉ አሳፍረን
ለነገዋ የተሻለች ኢትዮጵያ መገንባት አሻራችንን እናሳርፋለን፡፡ የእኛ ድርሻ የሚስማማንን መርጠን መንግሥት እንዲሆንና አገራችንን
እንዲያረጋጋ ዕድል መስጠት ነው፡፡ ይህንን እናድርግ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ!