Tuesday, May 1, 2018

እግር ኳስ ይቅርብን!

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ነገር ከማሰልቸት አልፎ አስፈሪ ሆኗል፡፡ በጣም አስፈሪ! ለዓመታት ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ተነገረ፣ ተሰበከ፣ ተጮኸ…፣ ስፖርታዊ ጨዋነት ግን እንኳን ሊሻሻል በየዓመቱ እየተበላሸ ሲሄድ ነው የምናየው፡፡ ጭራሹን ዘንድሮ ደግሞ የስፖርት ሜዳዎቻችን የቦክስ እና የነፃ ትግል መድረኮች ሆነው አረፉት!
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በወልዲያ ሼህ መሐመድ አሊ አልአሙዲን ስታዲየም በተደረገ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ “አግባብ ያልሆነ የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል” ያሉ የባለሜዳው የወልዲያ ከነማ ደጋፊዎች የጨዋታውን ዳኛ ደበደቡ፤ በዚህም ክለቡ ቅጣት ተጣለበት፡፡ በዚህ አሳፋሪ ድርጊት አዝነን ሳናበቃ ባለፈው ሰኞ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም  መከላከያ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ጨዋታ ባለሜዳው መከላከያ ሁለተኛ ጎል ካስቆጠረ በኋላ የእንግዳው ቡድን ተጫዋቾች በቡድን መሪያቸው ፊት አውራሪነት የጨዋታውን ዳኛ በመደብደባቸውና ከተጋጣሚያቸው ተጫዋቾችም ጋር ቡጢ በመሰናዘራቸው ጨዋታው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡
በእርግጥ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ክለብ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወዲያውኑ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሁከቱ ዋና ተዋናይ የሆኑትን የእግር ኳስ ቡድኑን መሪ ከሥራቸው ማሰናበቱን እና በግጭቱ ለተሳተፉ የክለቡ ተጫዋቾች ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ክለቡ የበኩሉን እርምጃ በአፋጣኝ መውሰዱ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ግን ከዚህም ያለፈ እርምጃ መወሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ያውም አፋጣኝ፣ የማያወላውልና የማያዳግም እርምጃ!
ከሰኞ ምሽቱ አሳፋሪ የኳስ ሜዳ ትዕይንት በኋላ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ  ነበር፡፡ እኔ የተመለከትኳቸው አስተያየቶች በሙሉ ድርጊቱን ከማውገዝ ባለፈ ኳስ የሥጋት ምንጭ እየሆነብን መሆኑንና ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳመዘነ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድም ጭምር ይጠይቃሉ፡፡ እኔም የዚህ ሀሳብ ተጋሪ ነኝ፡፡
ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል አንዱ “እግር ኳስ ቢቀርብንስ?” የሚል ነበር፡፡ ይህንን ሀሳብ እኔ መቶ በመቶ እደግፋለሁ፡፡ አዎ! በእግር ኳስ መዝናናታችን ቀርቶ ከምንሰቃይ፣ አዎ፣ እግር ኳስ ይቅርብን!
ለምን “ይቅርብን?” ሲጀመር ኢትዮጵያ እግር ኳስ የላትም፡፡ የስፖርቱ ሳይንስ የማያውቀው ተራ “ቅሪላ ማልፋት” እና ጥለዛ ብቻ ነው ያለን፡፡ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የለንም፡፡ እንኳንስ የአገሪቱን እግር ኳስ በአግባቡ ሊመራ ራሱንም በቅጡ ማስተዳደር የተሳነው ባዶ ቤት ነው ያለን፡፡ “የተማሩ፣ ያወቁ…” የሚባሉ ሰዎች ከሕፃናት ባነሰ እንጭጭ አስተሳሰብ የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች የሆነችውን አገራችንን በዓለም ፊት ተዋርደው አዋርደዋታል፡፡ አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ፡፡ ሲቀጥል የእግር ኳስ ደጋፊም የለንም፡፡ እግር ኳስን ለመዝናኛ በላይ የሕልውና ጉዳይ ያደረጉ “ደጋፊ” ተብየዎች በብዙሃኑ ሰላማዊ የእግር ኳስ አፍቃሪ መካከል ተሰግስገው የሰላሙን መድረክ የጦር አውድማ አድርገውብናል፡፡ በ”ቡድን ታማኝነት” ይነሳ የነበረው የኳስ ደጋፊዎች ግጭት ከአምና ጀምሮ ደግሞ ብሔር እና ፖለቲካን በማከል የለየለት ቁርቋሶ ሆነ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ችግሮቻችን ምክንያት ለመዝናናት ያልነው እግር ኳሳችን አሸባሪዎች ሊያደርሱብን ከሚችሉት አደጋ በላይ አስፈሪ ሆኖብናል፡፡ እኔ በበኩሌ አሁን አሁን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ጨዋታ ካለ በስታዲየሙ በኩል ማለፍ እያስፈራኝ መጥቷል፡፡ የምናየው ነገር ከሽብር ጥቃት የማይተናነስ ሆኗላ!
እግር ኳስ እወዳለሁ፡፡ እንዳለመታደል ግን ኢትዮጵያ እግር ኳስ ስለሌላት የሌለን ነገር ልወድ አልችልምና “የኢትዮጵያን እግር ኳስ” አልወድም፡፡ በስፖርት ሳይንስ ያልተቃኘ ተራ ጥለዛ፣ ፕሮፌሽናልነት የራቀው አስተዳደር፣ እና ጨዋነት የሸሸው ደጋፊነት መገለጫው የሆነ “እግር ኳስ” ምን ያደርግልናል? ለመዝናናት ከሆነ የውጪውን ውብ እግር ኳስ በቴሌቪዥን ማየቱን አናጣውምና እርሱ ይሻለናል፡፡ “በአገራችን ምርት እንኩራ” የሚባለው ዓይነት መፈክር እግር ኳሳችን ላይ አይሠራም፡፡ የምንኮራበት ክለብም ሆነ ብሔራዊ ቡድን የለንማ! እግር ኳስን የሚያውቅ ፌዴሬሽን የለንማ! ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ያደርግላታል?

ይህንን ስል ግን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ጠቃሚ ሀሳብ፣ ራዕይ እና ግብዓት ያላቸው ዜጎችና ባለሙያዎች የሉንም ማለቴ አይደለም፡፡ በሀሳባቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው ጥሩ እግር ኳስ እንዲኖረን ለሚጥሩ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ክብር አለኝ፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ በጎ አሳቢዎች የሚያደርጉትን መልካም ሥራ ሁሉ በዜሮ የሚያባዙ የአስተሳሰብ ድሆች እና በጡንቻቸው የሚያስቡ ከንቱዎች ባሉባት አገር እግር ኳስ በምኞት ብቻ መሠረት ሊይዝ አይችልም፡፡ ስለዚህ፣ የምንኮራበት፣ የምንደሰትበት እና የምንዝናናበት እግር ኳስ እንዲኖረን ቆም ብለን ማሰብ እና መሥራት ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አሁን የያዝነውን ተራ “ቅሪላ ማልፋት” ለተወሰነ ጊዜ አቁመን፣ ስታዲየሞቻችንን ዘግተን፣ የሚገነቡትን ስታዲየሞችን አጠናቅቀን፣ ክለቦቻችንን እና ፌዴሬሽናችንን አፍርሰን እንደ አዲስ በመገንባት፣ ለታዳጊዎች ሥልጠና ትኩረት ሰጥተን፣ ዋልጌዎችን ከደጋፊነት ተራ መንጥረን አውጥተን፣ የተጠና ሥራ በመሥራት ወደ ስፖርቱ መመለስ የሚሻለን ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ከዓለም እግር ኳስ መድረክ ስለምንርቅ ፊፋ ሊቀጣን ይችላል፡፡ ቅጣቱ ግን ከሰላማችን አይበልጥምና እግር ኳሳችንን ከዜሮ መጀመሩ ይሻለናል ባይ ነኝ፡፡ እስከመቼ በመዝናኛችን ስንሳቀቅ እንኑር? እናም፣ ይህንን እስክናሳካ ድረስ፣ እግር ኳስ ይቅርብን!