መቼም ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ብዙ ተብሏል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ
የስፖርት ተከታታይ አገራችን ስሟን በክብር ከሚያስጠራት አትሌቲክስ በበለጠ ለእግር ኳስ ከፍ ያለ ፍቅር ቢኖረውም፣ በውጤታማነት
ግን አርኪ የሆነ ነገር ጠብ ሳይልለት ዓመታትን ገፍቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የስፖርቱ ደረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በኢንተርናሽናል
ደረጃ ከዓመት ዓመት እየወረደ ብቻ ሳይሆን እየወደቀ መሄዱ ለስፖርቱ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን አፍቃሪና ተከታታይ ላልሆነው ሕዝብ
ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሐቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እኛም በአገራችን እግር ኳስ ውጤት-አልባነት መናደዳችን እየቀረ መሳለቅ ከጀመርን ቆየን፡፡
ዘንድሮም ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ትናንት ማምሻውን በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ከሚገኘው የቻን ውድድር
በጊዜ ተሰናብተናል፡፡ ያው የተለመደ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ከሚዲያዎች በስተቀር ማንም ምንም ሲል አልሰማሁም፡፡ ሚዲያዎቹም ቢሆኑ
ስለችግሩ ብዙ ስላሉበትና አዲስ ነገር ስላልመጣ እንደቀደመው ጊዜ ብዙ ነገር አልተናገሩም፡፡ ይልቁንስ፣ ”ካለፈው የቻን ተሳትፏችን
የተሻለው ነገር አንድ ጎልና አንድ ነጥብ ማግኘታችን ነው” የሚል ማጽናኛ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ አይፈረድባቸውም! ማለት የሚችሉት
ይህንኑ ብቻ ስለሆነ፡፡
በሚዲያዎቹ ከተነገረው ጥቂት ነገር ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዐቢይ ነጥብ ”ከዚህ በኋላስ ምን ይደረግ?” የሚለው
ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ያዳመጥኳቸው ሁለት የኤፍ.ኤም ሬዲዮ የስፖርት ፕሮግራሞች ስለዚህ ጥያቄ ከሰጧቸው ምላሾች ውስጥ አንደኛውና
እኔም በግሌ የተስማማሁበት ”ምን መደረግ እንዳለበት ብዙ ተነግሯል፣ ከዚህ በኋላ ይህንን ደጋግሞ ማንሳት አሰልቺ ነው” የሚለውን
ነበር፡፡ እውነት ነው! ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ስለዚህ ጉዳይ ስንቴ አወራን? ስንቴ ተናደድን? ስንቴ ተከራከርን? በጣም ብዙ
ጊዜ! ግን ምንም ለውጥ የለም፡፡
የፕሮግራሞቹ አቅራቢዎች ይህንን ቢሉም፣ ”አሰልቺ ነው” በማለት ብቻ ነገሩን አልተውትም፡፡ ግዴታቸው ነውና ከዚህ
በኋላም ”ቢሆን ጥሩ ነው” ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተዋል፡፡ እኔ የወደድኩት ሐሳብ በብሥራት ኤፍ.ኤም 101.1 የ”ብሥራት ስፖርት”
አዘጋጁ መንሱር አብዱልቀኒ ያቀረበውን ሐሳብ ነው፡፡ የመንሱር ሐሳብ በጥቅሉ ”ብዙውን ጊዜ በታዳጊዎች ላይ ስለመሥራትና ለውጡን
ከታች ስለመጀመር ተወርቷል፣ ይህም ለሰሚው አሰልቺ ሆኗል፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ለውጡን ከላይ ስለመጀመር እናስብ” የሚል ነበር፡፡
ይህ በእውነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኖቻችንና ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል መድረኮችም ሆነ በውስጥ ውድድሮች
አንገት አስደፊ ውጤት ባስመዘገቡ ቁጥር የሚሰጠው ምክንያት ”የተጫዋቾቹ የአካል ብቃት ዝቅተኛ መሆን፣ የአየሩ መክበድ፣ የዳኛ ውሳኔ፣
የመስተንግዶ ጥሩ አለመሆን፣ የአሰልጣኙ የአሰለጣጠን መንገድ፣” ወዘተ ሲባል ነው የምናየውና የምንሰማው፡፡ የስፖርቱ አመራርስ?
ስፖርቱ ዓለም በደረሰበት የሥልጠናና የውድድር ደረጃ እንዲካሄድ የሚጠበቅበትን ሥራ ያልሠራው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ለምን ዝም ይባላል?
በእርግጥ በቅርቡ ሚዲያዎቻችንም ሆነ ሌሎች የስፖርቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ለውጤት መጥፋት ፌዴሬሽኑን ተጠያቂ
ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ወቀሳው ጠንከር ብሎና ቁርጠኛ የመፍትሄ ሐሳቦችን አዝሎ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡
ወቀሳው ጠንከር ይበል ስል ግለሰብ የፌዴሬሽን አመራሮችን መውቀስ ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሥርዓቱንና አሠራሩን ”ትክክል
አይደለም፣ ኋላ-ቀር ነው ” ብለን ማውገዝና እንዲቀየር መጠየቅ አለብን እያልኩ ነው፡፡
በእኔ እምነት የእግር ኳሱም ሆነ የአጠቃላዩ ስፖርት ውጤት-አልባነት መነሻ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አደረጃጀትና
አሠራር አለመኖር ነው፡፡ የስፖርት ፌዴሬሽኖቻችን በሙሉ በአማተር አገልጋዮች የሚመራ ነው፡፡ እነዚህ አማተር አገልጋዮች ደግሞ አብዛኛው
ጊዜያቸውን በመደበኛ ሥራቸው ላይ የሚያውሉና የስፖርቱን ውሎና አዳር በሙሉ ትኩረት የሚከታተሉ አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ለስፖርቱ
ባላቸው ፍቅር ብቻ የሚሠሩ እንጂ የስፖርቱ ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው፣ በስፖርቱ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ ከተመልካችነት በዘለለ ያልተሳተፉ
ስለሆኑ ስፖርቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ የሚሳናቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ዛሬ፣ ስፖርት ሳይንስ በሆነበት ዘመን አገራችንን
ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር አያስችሉም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህም ተቋማዊ አደረጃጀትና ለውጥ በፍጥነት ያስፈልገናል፡፡
ምን ዓይነት ለውጥ? የአመራር ለውጥ? የአሰልጣኝ ለውጥ? የተጫዋች ለውጥ? የእነዚህ ሁሉ ለውጥ ውጤት አያመጣም፡፡
የሚፈለገው የሥርዓት (system) ለውጥ ነው፡፡ ሰዎችን በመቀያየር ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ሰዎቹ ሥራቸውን በዕውቀትና በነፃነት
መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሥርዓት፣ አቅም ያላቸው ባለድርሻዎች ተለምነው ሳይሆን ለምነው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የሚያበረታታ
ሥርዓት፣ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ እምነት ሊጣልበት የሚችል ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት ስፖርት በዕውቀት እንጂ በፍቅርና
በወኔ ብቻ የማይመራበት ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የስፖርቱ አመራር የዕለት ተዕለት ሥራቸው የሆነ ባለሙያዎች በደመወዝተኝነት
የሚሠሩት ሥራ መሆን አለበት፡፡ በቀላል ቋንቋ ስፖርታችን ፕሮፌሽናል
አመራር ያስፈልገዋል፡፡
”ፕሮፌሽናል አመራር ያስፈልገናል” ሲባል አሁን ያለው አማተር አመራርና አሠራር መወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ አማተሪዝም
ይብቃን! አማተሪዝም በአንድ ወቅድ ጠቅሞን ሊሆን ይችላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ግን አይሠራም፡፡ አማተሮች ስፖርቱን እስከመሩ
ድረስ በስፖርቱ መንደር ሰላም አይሰፍንም፡፡ ምክንያቱም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በስፖርታዊ ቋንቋ መነጋገር እስካልቻሉ ድረስ
ውዝግብ፣ ጭቅጭቅ፣ ጥቅም ፍለጋ፣ ሙስና፣ ወዘተ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ (ነፍሱን ይማረውና)
ብዙ ጊዜ ይል እንደነበረው ”በስፖርት ቋንቋ መነጋገር የሚችሉ አመራሮች ወደስፖርቱ አምባ መምጣት አለባቸው፡፡”
ይህንን ለማድረግ ”ከምን ይጀመር?” ከተባለ የኔ መልስ ”ከማፍረስ ” የሚል ነው፡፡ ”ማፍረስ” ሲባል አሉታዊ መልክ
ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ አሮጌ ቤታችንን ባለበት ቦታ ላይ በአዲስ ቤት ለመተካት ካሰብን ያለን አማራጭ አሮጌውን ቤት ማፍረስ
ብቻ ነው፡፡ እናም፣ ዘመናትን ያስቆጠረው፣ አሮጌው የአማተር የስፖርት ሥርዓት፣ መፍረስ አለበት፡፡ አሮጌውን አማተሪዝምን አፍርሰን፣
አዲሱን ፕሮፌሽናሊዝምን እንገንባ፡፡ ፌዴሬሽኖቻችንን እናፍርስ፣ አፍርሰንም በፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ ላይ እንገንባቸው፡፡ ያኔ፣
ጊዜው ቢረዝምም፣ ውጤታማ እንደምንሆንበት በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡ እናም ከማፍረስ እንጀምር!