ባለፈው ዓርብ ምሽት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሦስት ሥፍራዎች በተፈጸመው
የተቀናጀ የሽብር ጥቃት እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ መሠረት የ129 ሰዎች ሕይወት
ሲጠፋ፣ 352 ሰዎች መቁሰላቸው የሰሞኑ ዐቢይ ዜና ሆኗል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት መላውን ዓለም አስደንግጧል፣ አሳዝኗልም፡፡ ጥቃቱን
በማውገዝ የዓለም ማኅበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ከጥቃቱ ሰለባዎችና ከፈረንሳይ ጎን መቆሙን እየገለጸ ይገኛል፡፡ የዚህ አካል በመሆንም
ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ የገጽ መለያ ፎቶዋቸውን (profile picture) በፈረንሳይ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በመሸፈን ሐዘናቸውን የሚገልጹበትን ዘዴ
ከትናንት ጀምሮ ይፋ አድርጓል፡፡
በመሠረቱ ሽብርተኝነት በየትኛውም መነሾ ይምጣ፣ ምንም ዓይነት አመክንዮ ይሰጠው፣ ሊወገዝ የሚገባው እኩይ ድርጊት
ነው፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚፈጸም የሽብር ድርጊት ሐዘኑና ሕመሙ የመላው ዓለም መሆኑ አይካድም፡፡ ከዚህ አንጻር ፌስቡክም
ሆነ ሌሎች አካላት የፓሪሱን የሽብር ጥቃት ማውገዛቸውና ለተጎጂዎች ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸው የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን፣
ይህ ሽብርተኝነትን የማውገዝ እንቅስቃሴ ”ለሁሉም በእኩል የሚደረግ ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄ፣ ብዙ የሚያነጋግር ይመስለኛል፡፡
በዘመናችን በርካታ አገራት የሽብር ጥቃት ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ዓይነቱ ቢለያይም፣ በየአገራቱ በሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች
የንፁሃን ሕይወት መጥፋቱ ፣ በተለይ በዚህ ወቅት፣ በጣም እየበዛ መጥቷል፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት፣ ሽብርተኝነት በየትኛውም መለኪያ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ከአገር አገር የሚለያይ ደረጃ እየወጣለት
ለአንደኛው አገር ማልቀስ፣ ለሌላኛው ደግሞ ጀርባ መስጠት አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሽብርተኝነት፣ የትም ሆነ የት፣ ሽብርተኝነት
ነውና፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት በግብጽ የሲናይ በረሃ ላይ በአየር ላይ ፈንድቶ የተከሰከሰው የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን
የአደጋ መነሾ በአውሮፕላኑ ውስጥ በሻንጣ ተደብቆ የገባ ቦንብ መሆኑ ተገልጾአል፡፡ በዚህም መነሻነት አውሮፕላኑ የሽብር ጥቃት ሰለባ
እንደሆነ በስፋት ታምኗል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ዘመን የዓለማችን ቁጥር አንድ አሸባሪ የሆነው አይሲል እና የግብጽ አጋሩ አውሮፕላኑን
ማጋየታቸውን በይፋ ገልፀው ኃላፊነቱን ወስደዋል፡፡ በዚህ ጥቃት 224 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ይህን ተከትሎ ግን ፌስቡክም
ሆነ ሌሎች፣ እንዲሁም መላው ዓለም፣ ለፈረንሳይ ያዘኑትን ሐዘን ያህል ለሩሲያ ሐዘናቸውን አልገለጹም፡፡ በተለይ ፌስቡክ፣ ተጠቃሚዎቹ
ፎቶዋቸውን በሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት እንዲሸፍኑ ዕድሉን አልሰጠም፡፡ ለምን?
ይህን ጥያቄ የምጠይቀው ምክንያቱ የፖለቲካ ጎራ አሰላለፍ ልዩነት መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ይልቁን፣ ምዕራባዊያን
የሐዘን መግለጫ የኢንተርኔት ገጽ ሲያዘጋጁልን፣ የሐዘናቸው ሚዛን-አልባነት ቢከነክነኝ ያነሳሁት ጥያቄ ነው፡፡ ከፈረንሳይ የበለጠ
ቁጥር ያላቸው ዜጎቿን ያጣችውን ሩሲያን ”እግዜር ያጥናሽ” የምንልበት ዕድል ያልሰጠን ፌስቡክ ለፈረንሳይ ሐዘን፣ እንደሰፈር ዕድር
”ድንኳን ተካይ፣ ንፍሮ ቀቃይ” ልሁን ማለቱ በበኩሌ ሊዋጥልኝ አልቻለም፡፡ እንዲህ ያለው መንታ ሚዛን (double
standard) የዓለማችንን ዋነኛ ስጋት ምክንያታዊ በሆነ ዕይታ እንዳናወግዝና እንዳንዋጋ እንቅፋት ይሆንብናል ብዬ አስባለሁ፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያንም፣ የሐዘኑ ተካፋይ ብንሆንም፣ እኛም በአይሲል ወገኖቻችንን በአሰቃቂ ሁኔታ ባጣን ጊዜ ሐዘናችንን ብቻችንን እንዳዘንን
በማስታወስ፣ ይህንን የፌስቡክ የሐዘን መግለጫ መንገድ ተጠቅመን ሐዘናቸንን ስንገልጽ፣ ”ሚዛናዊነት ሆይ! ከወዴት አለህ?” ብለን
መጠየቅ ይገባናል፡፡