Monday, October 12, 2015

ማሳሰቢያ፤ ለባለሙያዎች

ሰሞኑን የአውሮፓ የፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በጁቬንቱስ ክለብ፣ በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ፣ በጎተ ኢንስትቲዩት፣ እና በብሪትሽ ካውንስል ከአሥራ ሰባት አገራት የተውጣጡ ፊልሞች ለዕይታ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ከሃያ አምስት ዓመታት ያላነሰ ጊዜን ያስቆጠረው ይህ ፌስቲቫል ከዓመት ዓመት የተመልካች ብዛቱ እየጨመረ ያለና ከከተማችን ዐበይት ጥበባዊ ክንውኖች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እኔም ከአሥር ዓመታት በላይ በዘለቀው የዚህ ፌስቲቫል ታዳሚነቴ ብዙ ነገሮችን ለመማር የቻልኩበትና የምዝናናበትም መድረክ በመሆኑ በየዓመቱ በካሌንደሬ ውስጥ በቋሚነት ከምመዘግባቸው ፕሮግራሞች መካከል አንደኛው ነው፡፡ ዘንድሮም አብዛኞቹን ፊልሞች ተመልክቻለሁ፣ በዕውቀትም ሆነ በመዝናናት ጥሩ ጥቅም እያገኘሁበት እገኛለሁ፡፡
አሁን ላነሳው የፈለግሁት ሐሳብ በቀጥታ ፌስቲቫሉን የሚመለከት አይደለም፡፡ ሐሳቤ በአጠቃላይ በከተማችን የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ ያለንን ተሳትፎ፣ በተለይም በመድረኮቹ የሚነሳው ሐሳብ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በመድረኮቹ ላይ ለመገኘት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚጠይቅ ነው፡፡
ይህንን ሐሳብ ከላይ በጠቀስኩት የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል አብሮኝ ከሚታደመውና ከፌስቲቫሉ ጋር ካስተዋወቀኝ ወዳጄ ጋር ስንወያይበት ነበር፡፡ አምና በተካሄደው መሰል ዝግጅት ላይ ካገኘሁት አንድ የፊልም ባለሙያ ጋርም በሰፊው ተነጋግረንበት ነበር፡፡ ከወዳጄ ጋር በዘንድሮው ፌስቲቫል ላይ እስከትናንትናው ምሽት ድረስ ያየናቸው የፊልምና የትወና ባለሙያዎች ሦስት ብቻ ናቸው (በአደባባይ  የማይታወቁ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳንረሳ)፡፡ በተለያዩ የቴአትር፣ የቴሌቪዥን፣ እና የፊልም ሥራዎች ላይ የምናውቃቸው አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች ግን (ቢያንስ እኔ በተገኘሁባቸው ቀናት) የሉም፡፡ እንደውም እኔ ሳስበው፣ እነዚህ ባለሙያዎች ስለፌስቲቫሉ መኖር ጨርሰው የሚያውቁም  አይመስለኝም፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ነገር በሌሎችም ዘርፎች ላይ ብዙ ጊዜ ይገጥመኛል፡፡ እኔ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ጊዜዬ አንስቶ ባመቸኝ ጊዜ ሁሉ የማልገኝበት መድረክ የለም፤ የፓናል ውይይት፣ ሌክቸር፣ ኤግዚቢሽን፣ የመጽሐፍ ምረቃ፣ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ ወዘተ፡፡ ርዕሰ-ጉዳዩ ተመለከተኝም አልተመለከተኝ፣ ዘርፌ ሆነ አልሆነ መገኘት ከቻልኩና ፍላጎቴ ከሆነ እታደማለሁ፡፡ ታዲያ የሚገርመኝ ነገር፣ የምገኝበት መድረክ ርዕሰ-ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከታቸው (ሥራቸው ከሆኑት) ሰዎች መካከል በመድረኩ ላይ የሚገኙት በጣት የሚቆጠሩት መሆናቸው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በዘርፋቸው ተተኪዎችን ማፍራት እንጀራቸው የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን [አብዛኛዎቹ] አይገኙም፡፡
ባለሙያዎቹ በእነዚህ መድረኮች ስላለመገኘታቸው ቢጠየቁ የሚሰጧቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አንዳንዶቹ መረጃ ባለማግኘት፣ ሌሎቹ ”ቢዚ በመሆን…፣”  የቀሩትም በሌሎች ምክንያቶች ”መገኘት አልቻልንም” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ”ቢዚ” መሆን (በተለይ ማታ ለሚያስተምሩ መምህራን) ልቀበለው የምችለው ምክንያት ቢሆንም፣ ሌሎቹ ምክንያቶች ግን አያሳምኑኝም፡፡ ለምን ቢባል፣ መረጃ አለማግኘትም ሆነ መሰል ሰበቦች ለእኔ መነሻቸው ”ስንፍና” ስለሆነ፡፡
አንድ የተማረ ሰው ሙያውን አስመልክቶ ስለሚደረግ ስብሰባ፣ ውይይት፣ ወይም መሰል ክንውን ለማወቅ መረጃው ቢሮው ወይም ቤቱ ድረስ እስኪመጣለት መጠበቅ የለበትም፡፡ ”ምን አዲስ ነገር አለ?” ብሎ መጠየቅ፣ ሚዲያ መከታተል፣ በተለይም ደግሞ በዚህ የኢንተርኔት ዘመን መረጃውን ጎልጉሎ ማውጣት በቀላሉ ሊያደርጋቸው የሚችሉ ነገሮች ይመስሉኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀለም-ቀመስ የሆነ ሰው ራሱን በተማረው ነገር ብቻ አጥሮ መቀመጥ አይገባውም ባይ ነኝ፡፡ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች እርስ በርስ ሊደጋገፉ ይችላሉ፣ በትምህርት ቤት ከምናገኘው ሙያዊ ዕውቀት በተጨማሪ በውይይቶች የምናገኛቸው በርካታ ጠቃሚ ዕውቀቶችና መረጃዎች አሉ፣ ከእኛ ዕውቀትና ሙያ ውጭ ያሉ ሌሎች ዘርፎች አስደሳችና አመራማሪ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሌሎችም ብዙ ጠቀሜታዎች ከእነዚህ መድረኮች ይገኛሉ፡፡ ደግሞም እነዚህ መድረኮች ከሥራ በኋላ ማምሻውን ለድራፍት የምናወጣውን ወጪ የግማሹን ግማሽ እንኳን የማያስወጡ (በአብዛኛው ከ12 ሰዓት በኋላ የሚካሄዱና ከክፍያ ነፃ) በመሆናቸው ብዙ የምናተርፍባቸው ዕድሎች እንደሆኑም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ሁሉ ግን ዋናው ፍላጎት ይመስለኛል፡፡ ለማወቅ የሚኖር ፍላጎት፣ ሁሉን አቀፍ ዕይታን ለማዳበር የሚኖር ፍላጎት፣ ጤናማ የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ለማግኘት የሚኖር ፍላጎት፡፡ በፍላጎት ብቻ ትምህርት ቤት ሳይገቡ ብዙ የሚያውቁ ሰዎች አንደኛው የዕውቀታቸው ምንጭ ዕውቀት የሚገኝባቸውን ቦታዎች አሳድደው በማግኘት መሳተፋቸው ነው፡፡ መማር የቻልን ሰዎች ደግሞ የበለጠው ዕድል በእጃችን ነውና ብንጠቀምበት ትርፋችን የበዛ ይሆናል፡፡