Tuesday, September 9, 2014

ደጋፊ! ደጋፊ! ደጋፊ!

ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ ያለሁት ብዙ ጊዜ ኳስ ከማይበት የመዝናኛ ሥፍራ ቁጭ ብዬ ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ ባለው ቴሌቪዥን ላይ ባለፈው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመት በሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች (ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ) መካከል በኢትሃድ ስታዲየም (የማንቸስተር ሲቲ ሜዳ) ላይ የተካሄደው ጨዋታ እየተላለፈ ነበር፡፡ የዚህ ጨዋታ ውጤት ለዩናይትዶች አሸማቃቂና አሳፋሪ ነበር፡፡ አራት ለ አንድ!
ይህ ጨዋታ ከተካሄደ ዓመት ሊሆነው ስለተቃረበና ውጤቱንም የማውቀው ስለሆነ ትኩረቴ ጨዋታው ላይ አልነበረም፣ ከዚህ ይልቅ ትኩረቴበስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን እየተከታተሉ በነበሩት ተመልካቾች ላይ ነበር፡፡ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ቡድናቸው እንደዛ እየተቀጠቀጠ ባለበት ወቅት አኩርፈው ከመቀመጥ ይልቅ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ተጫዋቸቻቸውን ከማበረታታት አልቦዘኑም ነበር፡፡ ብስጭታቸው ፊታቸው ላይ እየተነበበ ቢሆንም፣ እዚያ ቦታ የተገኙበትን ምክንያትና ዓላማ አልዘነጉምና ማድረግ ያለባቸውን አድርገው ጨዋታውን እንደምንም ጨረሱት፡፡
ይህንን ለተመለከትሁ በኋላ፣ እኛስ እንዴት ነው የምንደግፈውን ቡድን የምናበረታታው? የሚለውን ጥያቄ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ለዚህ ሐሳቤ ደግሞ ተጨማሪ መነሻ ነበረኝ፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሲካሄዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከአልጄሪያ አቻው ጋር ተጋጥሞ ነበር፣ በውጤቱም 2-1 ተሸንፏል፡፡ ታዲያ በዚህ ጨዋታ ላይ እንደቀደሙት ጊዜያት ሁሉ በስታዲየሙ የታደሙ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ተመልካች ብቻ ሆነው መገኘታቸው ቅር አሰኝቶኝ ስለነበረም ጭምር ነው ይህ ጥያቄ የተፈጠረብኝ፡፡
"ደጋፊነት" ምን ማለት ነው? እኔ እንደሚገባኝ አንድ ሰው የአንድ ግለሰብ፣ ተቋም ወይም ስብስብ ደጋፊ ሲሆን፣ ለሚደግፈው አካል ዓላማና ተግባር መሳካት በበኩሉ ማድረግ የሚገባውን ነገር (ማበረታታት፣ በገንዘብ ወይም በጉልበት ወይም በሐሳብ እገዛ ማድረግ፣ በተደጋፊው አካል በሚደረግለት ጥሪ መሠረት መሳተፍ፣ ወዘተ) ማድረግ ነው፡፡ በዚህ የደጋፊነት ሚና ውስጥ ታዲያ፣ ተደጋፊው አካል በጉዞው ላይ አስፓልትም ሆነ ኮረኮንች መንገድ ቢያጋጥመው፣ ሜዳማ ወይም ተራራማ ቦታ ላይ ቢደርስ፣ የተራራው አናት ላይ ቢወጣ ወይም በሸለቆው ውስጥ ቢገባ፣ ዓላማውን እስካመነበት ድረስ ደጋፊው “አይዞህ! አለሁልህ! በርታ!” ሊለው ግድ ይላል፡፡ ይህንን ማድረግ ተስኖት፣ ሲወድቅ  “ይድፋህ!” የሚለው ከሆነ፣ አንድም ደጋፊ አይደለም፣ አንድም ደጋፊነትን አያውቀውም፡፡
ከዚህ ተነስተን የቅዳሜውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ድባብ ስንመለከት፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያኑ ታዳሚዎች “ደጋፊዎች” ሳይሆኑ “ተመልካቾች” ነበሩ ማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ አዲስ ሳይሆን፣ ለዓመታት ስናየው የኖረ ነው፡፡ ዛሬ ግን በደንብ ልናስብበት የሚያስፈልገውድጋፍ ከጭብጨባና ፉጨት ባለፈ ትልቅ ጉልበት ያለው መሣሪያ መሆኑን መረዳት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ በተለይ በእግር ኳሳችን ላይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየታየ ካለው አንጻራዊ መሻሻል አንጻር በሜዳላይ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች የምንሰጠው ድጋፍ ለዕድገቱ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ደጋፊ ሆነን የምናሰማው ዝማሬ፣ ጭብጨባ፣ ፉጨት፣ ወይም ጩኸት ለተጫዋቾቻችን የሞራል ስንቅና የሥነ-ልቦና ጉልበት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ የሚመቱት ኳስ ዒላማውን ባያገኝ ወይም የተጋጣሚ ቡድን ጎል ቢያገባ እንደተቆጡት ሕጻን እጅን ከንፈር ላይ አድርጎ መቀመጥ ለምንደግፈው ብድን እንደማይጠቅም ካላወቅንና የጨዋታውን እንቅስቃሴ ብቻ በመከታተል ጊዜውን የምናሳልፍ ከሆነ ገንዘብ ከፍለን ስታዲየም ከምንገባ በየቤታችን ቁጭ ብለን በነጻ በቴሌቪዥን ብንመለከት ይሻላል፡፡ ኧረ እንዲያውም ሰው ሰብሰብ ባለበት ቦታ ከሆነ ድጋፉም ከስታዲየሙም ይበልጣል! እኔ ጨዋታውን በተመለከትኩበት ቦታ (ይህ ጽሑፍ የተጻፈበት ቦታ ነው) ዝማሬውና ሆታው ሁለተኛው የአልጄሪያ ጎል ከተቆጠረ በኋላም አልተቋረጠም ነበር፡፡

ስለዚህ ጎበዝ! ደጋፊ እንጂ ተመልካች አንሁን፡፡ መመልከት ለመዝናናት መጥቀሙ ባይካድም፣ ስታዲየም ስንገባ የምንደግፈውን ቡድን ለማበረታታት መሆኑንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ተጫዋቾቻችን የእኛን ድጋፍ በእጅጉ ይፈልጋሉና ዝም አንበላቸው፡፡ በአውሮፓው እግር ኳስ እኮ የጨዋታው ውበት የሜዳው ላይ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የደጋፊዎቹ የማያቋርጥ ዝማሬና ጩኸትም እንደሆነ በቴሌቪዥንም እናያለንና፣ ከኮረጅን አይቀር እንደቴክኒኩ ሁሉ አደጋገፉንም አብረን ብንኮርጅ ምን ይለናል?