Friday, May 30, 2014

ካርል፣ ከኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊ!


እነሆ! ትናንት ባለውለታችንን አጣን፡፡ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ አጋር፣ ከራሱ ዝናና ክብር በላይ ለሌሎች የመኖር ጉጉት አይሎበት፣ ምቾትና ድሎቱን ለሰብአዊነት ሲል ትቶ፣ችግራችንን ተቸግሮና በደስታችን ተደስቶ 33 ዓመታትን ከኢትዮጵያዊያን በላይ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኖረው ካርልሃይንዝ ቦም በ86ኛው ዕድሜው ላይ ለሞት እጁን ሰጠ፡፡ ሰው ሆኖ ኖሮ የማይሞት አለመኖሩ የማይቀር ቢሆንም፣ እንደካርል ዓይነቱ ልበ-ብርሃን ግን ሲሞት ብዙ ያጎድላል፡፡
ይህ ካርልሃይንዝ ቦም የሚባል ሰው የበርካታ ገድሎች ባለቤት ነው፣ ታሪኩ ትልቅ መጽሐፍ የሚወጣው፡፡ ከእኔ በላይ ብዙ ሊናገሩ የሚችሉ ሰዎች አሉና ብዙ ልል አልችልም፡፡ ሰውየውን ለማስታወስ ግን ከእርሱ ጋር የሚያያዙና በጣም የሚነኩኝን ሦስት  ነገሮች ብቻ ላንሳ፡፡
1.      ካርል ለበጎ አድራጎት ሥራው ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው በ1973 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን በቀጥታ አልነበረም ወደዚህ የመጣው፡፡ ወቅቱ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የድርቅ አደጋ ያንዣበበባቸው ወቅት ነበርና፣ ካርልም የድርቁ አደጋ የከፋባቸውን የሳህል አገሮችን ለመርዳት አስቦ ነበር ወደአፍሪካ የመጣው፡፡ በመጀመሪያ ቻድ ሄደ፣ የቻድ መንግሥት አልተቀበለውም፡፡ ቀጥሎ ወደሱዳን አቀና፣ የካርቱምም ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በሦስተኛ ሙከራው ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ግን የወቅቱ መንግሥት በደስታ ነበር የተቀበለው፤ ያለቢሮክራሲያዊ ውጣ-ውረድ፣ ”እስቲ የመደብ ጀርባው ይጠና ” ሳይባል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ያሳየው ተቆርቋሪነትና የተደረገለት አቀባበል ግን በሁሉም ወገን በኩል በቀና አልታየም፡፡ በተለይ በጊዜው በስደት በምዕራብ አገሮች የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ”ይህ የምዕራብ አገር ሰው ከደርግ ጋር መሥራቱ ክህደት ነው” በሚል ከፍተኛ የተቃውሞና አለፍ ሲልም የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ካርል፣ ”ሰብአዊ አገልግሎትና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ይልቅ ሰብአዊነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” በሚል ጽኑ አቋም፣ የተከፈተበትን ዘመቻ ከቁብም ሳይቆጥር ሥራውን ቀጠለ፡፡  ኢትዮጵያም ደርሶ ከ33 ዓመታት በፊት ”ሰዎች ለሰዎች” (Menschen für Menschen) የተባለውን ምግባረ-ሰናይ ድርጅቱን በመመሥረት በጤና እክል ምክንያት ሥራውን እስካቆመበት እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ በሊቀመንበርነት መርቶታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን እንደ ድርጅቱ ሠራተኛ አንድም ጊዜ ደመወዝ ሳይወስድ በነጻ ነበር ታላላቅ ሥራዎችን የሠራው፡፡
2.     ”ሰዎች ለሰዎች” ሥራውን በጀመረበት የኤረር ሸለቆ አካባቢ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዲ አሊ ቦሩ አንዱ ነው፡፡ አብዲ፣ እንደሌሎቹ ተጠቃሚዎች ሁሉ ለካርል ከፍ ያለ ፍቅር ቢኖረውም፣ የፍቅሩ መግለጫ ግን የተለየ ነበር፡፡ ማንም ሳያዘው፣ ሳይቀጥረውና ደመወዝ ሳይከፍለው፣ ካርል ወደ ቦታው በመጣ ጊዜ ሁሉ፣ እዚያ በሚገኘው ቤቱ በር ላይ ማታ ማታ እየተኛ፣ ክፉ እንዳያገኘው ሲጠብቀው ያድራል፡፡ ካርል ጠዋት ተነስቶ በሩን ሲከፍት መጀመሪያ የሚያየው ደጃፉ ላይ ጥቅልል ብሎ የተኛውን አብዲን ነበር፡፡ ታዲያ አብዲ ይህንን ለምን እንደሚያደርግ ሲጠየቅ፣ ”ካርል ለእኔ አባቴ ነው፡፡ አባቴ ያላደረገልኝን ነገር አድርጎልኛል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው አንድ ነገር ቢሆን ምን ይውጠኛል? መጥፎ ነገር ቢመጣ እንኳ መጀመሪያ እኔን ያግኘኝ ብዬ  ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ካርልም ለአብዲ ያለው ፍቅር እጅግ የበዛ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ለድርጅቱ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጀርመን ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ሰፊ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ባገኘ ፕሮግራም ላይ  ታዲያ አዘጋጆቹ ካርልን ሰርፕራይዝ ያደረጉት በአብዲ ነበር፡፡ አብዲ ሽርጡን እንዳሸረጠ ወደመድረኩ ሲመጣ ካርል ዓይኑን አላመነም ነበር፡፡ ትልቁን ሰውዬ እንደ ሕጻን ልጅ አገላብጦ ነበር የሳመው፡፡ ”ታማኝ ወዳጄ” ሲልም አሞግሶታል፡፡ ካርል ለሠራቸው በጎ ሥራዎቹ ሁሉ ተጠቃሚዎቹ አመስግነውት አይጠግቡም፡፡ በ1995 ዓ.ም. ”ሰዎች ለሰዎች” በሰሜን ሸዋ መሐል ሜዳ ላይ ያሠራው ”ካርል ሆስፒታል” በተመረቀበት ወቅት አንድ የአካባቢው አርሶ አደር ሲናገሩ (ቃል በቃል ላይሆን ይችላል) ”በፊት ሕክምና በዚህ ባልነበረ ጊዜ በትንሽ ሕመም እንኳ ብዙ ሰው ይሞትብን ነበረ፡፡ ቃሬዛ ሠርተን ተሸክመን ወደ ከተማ እየወሰድን መከራችንን ስንበላ ኖርን፡፡ አሁን ግን ካርል ከመጣ በኋላ ሰዉ ሆዴን ቆረጠኝ፣ ራሴን ፈለጠኝ ቢል ከዚሁ ከጓሯችን ሂዶ ክኒናውን እየዋጠ ጤና ሆነ፣ እኛም ይኸው ካርልን ያኑርልን እያልን ደስ ብሎን አለን፡፡” ብለው ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ብዙ ምስጋናና ምርቃትም አግኝቷል፡፡
3.     ከዛሬ 8 ዓመት በፊት የ”ሰዎች ለሰዎች” 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጀርመን የባሕል ተቋም (ጎተ ኢንስትቲዩት) በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ በረጅም ጊዜ የተቋሙ ደንበኝነቴ አዳራሹ እንደዚያ ቀን ሞልቶ ያየሁበትን ቀን አላስታውስም ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ካርል ነበር፡፡ በዚያው ሰሞን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርብ በነበረው ”ዐውደ-ሰብ” የተባለ ፕሮግራም ካርልን የተመለከተ ሰፊ ዝግጅት ቀርቦ ስለነበር ብዙ ሰዎች ለካርልና ለ”ሰዎች ለሰዎች” ግምታቸው ከፍ ብሎ ስለነበር ይመስለኛል፡፡ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ነበረ፣ ከካርል ጋር አብረው የሠሩና ካርልን የሚያውቁ ታዋቂ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጡ፣ በመጨረሻ ላይ ካርል ንግግር አደረገ፡፡ ከንግግሩ መካከል እስከዛሬ የማይረሳኝ ”ዛሬ ኢትዮጵያ አገሬ ሆናለች፡፡ አገሬን ደግሞ ተለውጣ ላያት እመኛለሁ፡፡ አሁን የናፈቀኝ እናንተ ‘ዛሬ ራሳችንን ችለናልና ላደረጋችሁልን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ካሁን በኋላ ግን አንፈልጋችሁም ‘ የምትሉበትን ቀን ነው፡፡” ያለውን ነው፡፡ ይህንን ሕልሙን ዕውን ሆኖ ሳያየው ሞት ቀደመው፡፡

ዛሬ ካርል አርፏል፡፡ የእርሱ ዕረፍት ደግሞ ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ”እኛ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ምን አደረግን?” የሚል ጥያቄ፡፡ ይህ ሰው፣ ምኑም ያልሆነች አገር ችግር ቢያመው፣ ብዙ ሐብት ያፈራበት የነበረውን የቴአትርና የፊልም ተዋናይነቱን ትቶ፣ ያለውን ሁሉ ለዚህች አገር ሲሰጥ፣ እኛ ያገር ተወላጆቹ ”ምን ሠራን?” ብንል መልሱ ያሳፍረናል፡፡ በተለይ፣ ”ባለሐብት” የሚባሉት (ከጥቂቶች በስተቀር)፣ ያላቸውን በሙሉ ባይሰጡ እንኳን፣ ከዓመታዊ ትርፋቸው ላይ ጥቂቱን አንስተው በተደራጀ መልኩ ለበጎ አድራጎት ሥራ ሲያውሉ የማይታዩ መሆናቸው አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ ይህ ነው ”ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚያስብለው፡፡ ካርል! ከኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ኖረህ፣ ኢትዮጵያዊ ሆነህ አርፈሃል፡፡ ውለታህን ግን አንዘነጋውም፡፡ ስናመሰግንህ እንኖራለን፡፡  ምስጋናችን በሁለት ምክንያት ነው፣ አንድም፣ በችግራችን ወቅት ስለደረስክልን፣ ሁለትም፣ራሳችንን እንድንወቅስ  ስላደረከን፡፡