እኔ የምለው፣ ትችትን ወይም ተቃውሞን ያለስድብ
መግለጽ አይቻልም እንዴ? በፌስቡክ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል
ብዙዎቹ ስድብና ዘለፋን ያዘሉ መሆናቸው በግሌ በጣም ያሳስበኛል፡፡ ያልተስማማንበትን ነገር ሲሆን በምክንያት፣ ካልሆነም እንዲሁ
”አልተስማማሁበትም” ብሎ መቃወም ሲቻል፣ በተራ የመንደር ስድቦች እና ጸያፍ ቃላት መዝለፍ ”ምን እየሆንን ነው? ”የሚያሰኝ ነው፡፡
ይህንን ለመረዳት በፌስቡክ ላይ ከወጡ በርካታ ዜናዎች ሥር የሚጻፉ አስተያየቶችን ማየት ይቻላል፡፡ እኔ ግን በተለይ ትኩረቴን የሳበውን
አንድ ጉዳይ ብቻ አንስቼ የታየኝን ልል ወደድኩ፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቴዲ አፍሮ ”መሬት ሲመታ” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ
ቡድን ማበረታቻ አንድ ነጠላ ዜማ ለቀቀ፡፡ ይህም በፌስቡክ ላይ ተገለጸ፡፡ እንደተለመደውም ብዙ አስተያየቶች ተሰጡ፡፡ ከአስተያየቶቹ
ውስጥ በርከት ያሉ አሉታዊ ትችቶች ባልተለመደ ሁኔታ ነበሩበት፡፡ ትችቱ ባልከፋ ፣ ግን፣ሁሉም ትችቶች በተራ ስድብ እና ዘለፋ የተሞሉ፣
ምክንያታዊ ያልሆኑ መሆናቸው ነው ችግሩ፡፡ ቴዲ ዋሊያዎችን ለማበረታታት፣ እኛን ደጋፊዎቻቸውንም ለማጠንከር በሙያው አንድ አስተዋጽኦ ሲያደርግ፣ ማመስገኑ
እና ማድነቁ ቢቀር እንዴት ሰብዕናን በሚያዋርድ መልኩ፣ያውም ሥራውን
ሳናደምጥ፣ ለዘለፋ እንቸኩላለን? አያይ! በጣም ችግር አለብን፡፡
አንዳንዶች ”ቴዲ ዘገየ ” ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ ”ቴዲ ራስ ወዳድ፣ ገንዘብ አፍቃሪ፣
ሳንቲም ለቃሚ፣ እና ስግብግብ ነው” ሲሉ ይሰማል (ይነበባል)፡፡ ሁሉም አሉታዊ ትችቶች መሠረት የሌላቸው እና ”ውሃ የማያነሱ”
ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ከሙያዊ ማንነቱም ሆነ ከግላዊ ሰብዕናው ጋር የማይገናኙ እና፣ ምናልባትም፣ የቅናት የሚመስሉ፡፡ ከላይ ያነሳሁዋቸውን
”አስተያየቶች” እስቲ ተራ በተራ እንመልከት፡፡
1.
ቴዲ ዘግይቷል፡ ይህንን አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች መነሻቸው (በእኔ
ግምት) ”ብሔራዊ ቡድናችን በኢንተርናሽናል መድረኮች ረዥም ርቀት ከተጓዘ እና ቡድኑን የሚያሞግሱ በርካታ ሙዚቃዎች ከወጡ በኋላ
የቴዲ ”መሬት ሲመታ” መምጣቱ ስህተት ነው” የሚል ነው፡፡ እኔ እንደማምነው ግን የጥበብ ሥራ ሰፊ ጊዜን፣ ትኩረትን፣ እና ጥሞናን
ይፈልጋል፡፡ ቴዲም ያለውን ሁኔታ በጥሞና ከተመለከተ በኋላ ‘ለሁላችንም ያስፈልገናል’ ብሎ ያመነበትን ሐሳብ ተገቢ ነው ባለው ጊዜ
በሙዚቃ አቀረበልን፡፡ ይህ መዘግየት አይመስለኝም፡፡ ወቅታዊነትን መጠበቅ፣ ያላየነውን ጎን ማሳየት፣ እና ማበረታታት እንጂ፡፡
2.
ቴዲ ራስ ወዳድ ነው፡ ”ራስ ወዳድነት” ምንድን ነው? ራስ ወዳድነት
ከራስ አልፎ ማየት አለመቻል፣ ”እኔን ከተመቸኝ ሌላው ምናባቱ” ማለት፣ ወዘተ ይመስለኛል፡፡ የቴዲ ታሪክ ይህ አለመሆኑን ሁላችንም
እናውቀዋለን፡፡ ቴዲ በሙያው ያገኘውን ዕውቅና ለመልካም ሲያውለው በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የቅርቡን እንኳን ብንወስድ፣ ከእስር ከተፈታ
በኋላ ካቀረበው የመጀመሪያ ኮንሰርት አንዲት ሳንቲም ለራሱ ሳይወስድ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መስጠቱ፣ ከራሱ ኪስም አውጥቶ ሌላ
የበጎ አድራጎት ድርጅትን መርዳቱ፣ በእጁ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው እንኳ ራሱን ባለዕዳ አድርጎ በሶማሌላንድ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን
ወገናችንን የደም ዋጋ ከፍሎ ከሰይፍ ማስጣሉ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ታዲያ የት ላይ ነው የቴዲ ራስ ወዳድነት?
3.
ቴዲ ገንዘብ አፍቃሪ ነው፡ የዚህኛው ትችት መነሻ ደግሞ ”ቴዲ የሙዚቃ
ዝግጅቶችን የሚያቀርበው ገበያውን እና የሚከፈለውን ገንዘብ እያየ ነው” የሚል ይመስለኛል፡፡ እንዴ?! ሁላችንስ ብንሆን በየሥራ
ዘርፋችን የተሻለ ክፍያ የምናገኝበትን አይደል እንዴ የምንመርጠው? ታዲያ ይህ የሁላችንም ፍላጎት ቴዲ ጋር ሲደርስ ሀጢያት የሚሆነው
ለምንድን ነው? የተሻለ ክፍያ የምንጠይቀው እኮ የሚከፈለን ክፍያ ሥራችንን የሚመጥን መሆን ስላለበት ነው፡፡ ቴዲም እኛ ዛሬ እንድናደንቀው
እና መነጋገሪያ እንዲሆነን ያስቻሉትን ሥራዎቹን በሚመጥን ክፍያ ማቅረቡ የሰው ፍላጎት፣ የንግድ አሠራር መንገድም ነው እንጂ ወንጀል
አይደለም፡፡
4.
ቴዲ ሳንቲም ለቃሚ ነው፡ አንድ ሰው በሚሠራው ሥራ ፈላጊ ያለበትን ቦታና ጊዜ መምረጥ
አለበት፡፡ የዚህኛው ትችት አቅራቢዎች እንደ ማጠናከሪያ የሚያቀርቡት አምና በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው እና አገራችን ከ31 ዓመታት
በኋላ በተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ ዋዜማ በጆሐንስበርግ ኮንሰርት ማቅረቡን ነው፡፡ ካዋጣው ለምን አያደርገውም? ሥራው እስከሆነ
ድረስ እና ወቅቱም አመቺ ሆኖ ከተገኘ በዚያ የሚገኙ ወገኖቹን አዝናንቶ ለሥራው ቢከፈለው ነውሩ ምንድን ነው? ”ሳንቲም መልቀም”
እኮ ለ”ሳንቲሟ” ሲባል ”ከፍራሹም፣ ከጭቃውም ላይ መውደቅ” ነው፡፡
ቴዲ ደግሞ ይህንን ሲያደርግ እስካሁን አላየንም፡፡
5.
ቴዲ ስግብግብ ነው፡ ይህኛው ምንም ማብራሪያ የማያስፈልገው ”ባዶ እና
ተራ ዘለፋ” ነው እላለሁ፡፡ ሥራን ሠርቶ ገንዘብ ማግኘት፣ ካገኙት
ገንዘብ ላይ ለመልካም ተግባር መስጠት ”ስግብግብነት” ነው የሚል
ካለ፣ አዕምሮውን መመርመር አለበት፡፡ የቴዲን ”ስግብግብነት” በማስረጃ ያቀረበ አንድም የፌስቡክ ተቺ የለም፡፡ ለዚህ ነው ”ባዶ
እና ተራ ዘለፋ” ነው ያልኩት፡፡ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የቴዲንም ሆነ የማንኛውንም የሙዚቃ ባለሙያ ሥራ ሳናዳምጥ እና መልዕክቱን
ሳንረዳ፣ ጫፍ ይዘን መሮጥ አላዋቂነት ነው ባይ ነኝ፡፡ በተጨማሪም የአንድን ሰው ግላዊ ማንነት ከሙያዊ ማንነቱ ጋር አደባልቆ ማየትም
ፍርደ-ገምድልነትን ያመጣል እላለሁ፡፡ አንድ ምሳሌ እንይ፡፡ ጥላሁን ገሠሠን የአገራችን የሙዚቃ ንጉሥ አድርገን የሾምነው፣ ከትውልድ
እስከ ትውልድ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ ያደነቅነው፣ የወደድነው፣ እና ያከበርነው፣ በሞቱም ጊዜ አደባባይ ወጥተን፣ በጸሐይ እየተጠበስን
በታላቅ ለቅሶ የሸኘነው እና በብሔራዊ ጀግና ክብር የቀበርነው በሥራዎቹ ጥራት እና ታላቅነት ነው እንጂ የግልና የቤተሰብ ሕይወቱማ
ለአርአያነት እንደማይበቃ ጠፍቶን አይደለም፡፡ ቴዲም እንደግለሰብ ድክመቶች ሊኖሩበት እንደሚችል ሳንረሳ ያንን ለራሱ ትተን ሥራዎቹን
በማስተዋል ብንመዝን ከስህተት እንድናለን፡፡
ቴዲን አለመውደድ መብት ነው፣ ሥራውን አለማድነቅም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ስንተች
ስድብ እና ዘለፋን አስወግደን ለመማማርና ለመተራረም ልናውለው ይገባል፡፡ ”በፌስቡክ ላይ የሚሰጡ በቁጥር ቀላል የማይባሉ አስተያየቶች
በስድብ መታጀባቸው ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችን የት ገባ?” የሚያሰኝ ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ ምን ነካን?
