ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ልጽፍ ነው፡፡ በሦስት
ምክንያቶች፡፡
·
አንደኛ፡- ይህንን ብሎግ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ አብሮኝ ያለውን “አንድ ቀን በአገሬ ቋንቋ እጽፋለሁ፡፡” የሚለውን ሐሳቤን
ለማሳካት፣
·
ሁለተኛ፡- የዛሬው ርዕሴ ትንሽ ከበድ ያለ እና ድርጊቱም በአገር ደረጃ አሳፋሪ እና አሰቃቂ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ቋንቋ ጽፌ
አገሬን “ሰድቦ ለሰዳቢ” ላለመስጠት፣
·
ሦስተኛውና ዋነኛው ምክንያቴ ደግሞ ፡- ስለዚህ ዘግናኝ እና አሳሳቢ
ጉዳይ ለመጻፍ ከአፍ መፍቻ ቋንቋዬ የተሻለ ቋንቋ ስላላገኘሁ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በእጅጉ የማደንቀው ጸሐፊ ዳንኤል ክብረት “እስከመቼ” በሚል ርዕስ
በብሎጉ ላይ ባወጣው ጽሑፍ በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው በሚሠሩ እና ሰርክ በሚያስቀና ፍቅራቸው በሚታወቁ ወንድም እና እህት መካከል
በተፈጠረ ጊዜያዊ አለመግባባት ምክንያት የተከሰተውን ዱላ-አከል ጠብ አስመልክቶ የተሰማውን ስሜት አስፍሮ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ
ላይ አንባቢያን የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ ድርጊቱን ሲያወግዙ፣ ጥቂቶች “እና ምን ይጠበስ?” ዓይነት አስተያየት
ነበር የሰጡት፡፡
ጉዳዩን እንዲሁ ላይ ላዩን ሲመለከቱት ቀላል ነገር ይመስላል፡፡ “ወንድም እና እህት
በሥራ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ተጋጩ፣ ወንድም እህቱን በጥፊ ወለወለ፣ በቃ፡፡ እንኳን ሰው እና ሰው እግር እና እግርስ ይጋጭ
የለ?” ብዙዎች ይህንን እንደሚሉ አይጠረጠርም፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ነገር ሰፋ አድርገን ካስተዋልነው ግን እነዚህን መሰል “ቀላል” ነገሮች ተጠራቅመው
ከባድ እና አሳሳቢ እንደሚሆኑ ማስተዋል ይቻላል፡፡
ለዚህ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ ክስተት የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ
ነበር፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለምዶ “መስቀል ፍላወር“ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ
ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከሩብ ላይ አንድ ግለሰብ የቀድሞ ባለቤቱ የምታሽከረክረውን መኪና በመኪናው መንገድ ዘግቶ ካስቆማት በኋላ በያዘው
ክላሽኒኮቭ ጠመንጃ ተኩስ ከፍቶ እርሷን በ18 ጥይቶች መትቶ ሲገድል፣ አብረዋት የነበሩትን ወላጅ እናቷን እና ሁለት በአካባቢው
የነበሩ ግለሰቦችን አቆሰለ፡፡ በመጨረሻም ራሱን ለመግደል ሲሞክር ጥይት በመጨረሱ ሳይሳካለት ቀርቶ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡
ብዙ ዓይነት የግድያ ወንጀሎችን በዕድሜዬ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይም በባል እና በሚስት
መካከል ከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጋር ተያይዞ እስከሞት ድረስ የደረሱ ጥቃቶችን አውቃለሁ፡፡ ይህኛው ግን ሲበዛ አሰቃቂ እና አስፈሪ
ሆኖብኛል፡፡ ከባለጉዳዮችም አልፎ ሌሎች ንፁሃንንም የጎዳ እና ከልክ ያለፈ አረመኔያዊ ጥቃት!
ባለችኝ ጥቂት የጦር መሣሪያ ዕውቀት መሠረት አንድ የክላሽኒኮቭ ጠመንጃ የጥይት
ካርታ 30 ጥይቶችን ይይዛል፡፡ እንደሟች እናት ምስክርነት ሟች በ18 ጥይት ተመትታ ነው የተገደለችው (ፖሊስ ገና እያጣራ ቢሆንም)፡፡
እናት በሦስት ጥይቶች መመታታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁለት መንገደኞችም በተኩስ እሩምታው ቆስለዋል፡፡ ምናልባት እያንዳንዳቸው በሁለት
ወይም በሦስት ጥይቶች ተመትተዋል ብለን እናስብ፡፡ ስንደምራቸው ወደ ቢበዛ ወደ 27 ያህል ጥይቶች በሰለባዎቹ ላይ አርፈዋል፡፡
ተጠርጣሪው ራሱን ለመግደል ሞክሮ ጥይት ስለጨረሰ ሳይሳካለት ቀርቷልና ቀሪዎቹ ሦስት ጥይቶችም ተተኩሰዋል ማለት ነው፡፡
ይህንን ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ግድያ (ርሸና ብለው ይሻላል) ቀደም ሲል የምናውቀው
በምዕራቡ ዓለም ነበር፡፡ ከሥራው የተባረረ፣ ትዳሩ የፈረሰ፣ አዕምሮው የተቃወሰ እና የጦር መሣሪያ እጁ የገባ ሁሉ አገር ፈጅቶ
እራሱን ሲያጠፋ ብዙ ጊዜ ሰምተናል፡፡ እኛ አገር ከጥቂት ዓመታት በፊት በግል ጠብ ምክንያት ይህን የመሰለ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሳለሁ፡፡
ትዳር-ተኮር በሆነ ምክንያት ግን… ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
እንደሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ ተጠርጣሪው የቀድሞ ባለቤቱ እና ልጆቹ “ጠልተውኛል”
የሚል ስሜት አድሮበታል፡፡ ለዚህ ስሜቱ ወይም ስጋቱ መፍትሄው መግደል ነው ብሎ ማመኑ እርምጃውን ለመውሰድ እንደገፋፋው ማሰብ ይቻላል፡፡
ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ በምድርም ሆነ በሰማይ የተሳሳተ፣ ወንጀልም ኃጢያትም መሆኑ አያከራክረንም፡፡ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን
ለመፍታት ሰላማዊ የሆኑ ብዙ መንገዶች ስላሉ፡፡
በፍቅርም ሆነ በትዳር ግንኙነቶች ውስጥ አለመግባባትና ግጭት ይከሰታል፡፡ እነዚህን
ችግሮች ቢቻል በውይይት፣ ካልተቻለ በሽምግልና፣ ከዚያ ከከበደ ደግሞ በመለያየት መፍታት ይቻላል፡፡ እነዚህ በፍቅርና በትዳር መካከል
የሚፈጠሩ ግጭቶች በአግባቡ መያዝ እስከተቻለ ድረስ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክሩ አምናለሁ፡፡
ይህ ማለት ግን ሁልጊዜም ግጭት መኖር አለበት፣ ግጭቱ በየትኛውም መልክ የሚገለጽ
ይሁን ማለት አይደለም፡፡ በግጭት ስም ዲያቢሎስ ወደቤታችን እንዲዘልቅ በፍጹም መፍቀድ አይገባንም፡፡ አበው “ሰይጣን ሰውን ሲያታልል
“ስለፍቅር በስመአብ ይቅር” ይላል” ይላሉ፡፡ ዛሬ በአገራችን እያየን እና እየሰማን ያለነውና በፍቅርና በትዳር ውስጥም ሆነ ውጭ
የምናየው ጭካኔ የዚህ አካሄድ ውጤት ነው፡፡ ግጭትን በሰከነ መንፈስ ለማብረድ አለመቻል፣ በስሜት መነዳት፣… ይህ ሁሉ የወንጀል
ምንጭ ይሆናል፡፡
ትናንት እናያቸውና እንሰማቸው የነበሩ በፍቅርና በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች
የፈጠሯቸው ጥቃቶች “ቀላል ናቸው” ብለን ስናልፋቸው፣ እነሆ ዛሬ ወደከፋው ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የትናንቱ ጥፊ ዛሬ ወደቦክስ፣ ወደዱላ፣
ወደፈላ ውሃ፣ ወደአሲድ፣ቀጥሎም ወደ ጥይትና ቦምብ ተቀይሯል፡፡ ነገ ደግሞ ወደየት እንደሚሄድ ፈጣሪ ይወቅ፡፡ አሁኑኑ የማያዳግም
እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር፡፡
እንደወንድነቴ፣ እነዚህ ሁሉ የጭካኔ ተግባራት በሙሉ እየተፈጸሙ ያሉት በወንዶች
በመሆኑ አዝናለሁ፣ አፍራለሁም፡፡ በእኔ አመለካከት ”ወንድ” ማለት ትዕግሥተኛ፣ አመዛዛኝ፣ እና ምክንያታዊ የሆነ፣ ተፈጥሯዊ የአካል
ጥንካሬ የበላይነቱን በተገቢው መልኩ የሚጠቀም ሰው ነው፡፡ ወንድነት የሱሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአዕምሮ ብስለት እንጂ፡፡ ከዚህ
አኳያ የነገራችን መነሻ የሆነን ሰው የቀድሞ ሚስቱን ለመግደል ሲወስን ሌሎቹን የችግሩን መፍቻ መንገዶች በአዕምሮው ውስጥ ዘግቶ
ነው ለማለት ያስችላል፡፡ ቀድሞ ፈራጅ ባልባል፣ ይህ ሰው የመግደል ሐሳቡን ያመነጨው ተኝቶ ሲነሳ አይመስለኝም፡፡ አስቦበት፣ መሣሪያ
ገዝቶ ወይም ተውሶ፣ የሟችን መውጫ ሰዓት ጠብቆ የድርጊቱን ውጤት እያወቀ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህንን በጭካኔ የተሞላ
ወንጀል ዛሬ እንደቀላል አይተን ካለፍነው ነገ ሌሎችም የግጭት መፍቻ መንገድ አድርገው እንደማይወስዱት ምንም ዋስትና የለንም፡፡
እናም ሕጉ ይጥበቅ፣ ተተኪውን ትውልድ ከዚህ መሰል አረመኔነት ለማዳን ትምህርትና
ምክር በስፋት ይሰጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወንዶች ትዕግሥትን እንላበስ፣ የምር “ወንድ” እንሁን!!!




